ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚአብሔር በጭራሽ አያሳፍረንም፣ ልባችንን ሲያንኳኳ እንክፈትለት አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማከብር ዝግጅት የሚደረግበት የስብከተ ጋና ወቅት በኅዳር 20/2013 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። ስብከተ ገና ኢየሱስ በዓለም ታሪክ ውስጥ በመግባት የዓለምን የቀን አቆጣጠር ወደ ዓመተ ምሕረት እንደቀየረው ሁሉ የእኛንም ሕይወት በምሕረቱ ሊሞላት እና ልቀይራት እንደ ሚመጣ እና በእርሱ በኩል ሁሌም ዝግጁ መሆኑ የሚሰበክበት ወቅትና፣ እኛም ለእዚህ ጌታ ለምያደርግልን መንፈሳዊ ለውጥ የማምጣት ጥሪ በቃላት እና በትግባር በተደገፈ መልኩ ምላሽ የምንሰጥበት ወቅት ነው የስብከተ ገና ወቅት።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእዚህም መሰረት የእዚህ የስብከተ ገና 1ኛ ሣምንት በኅዳር 20/2013 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ ዕለት እንደ ሚያደርጉት በእለቱ  ከማርቆስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበውና “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም። ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም” (ማርቆስ 13፡33) ቀኑና ሰዓቱ አይታወቅም ተግታችሁ ጠብቁ በሚለው በኢየሱስ ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን እግዚአብሔር በጭራሽ አያሳፍረንም፣ ልባችንን ሲያንኳኳ እንክፈትለት ማለታቸው ተገልጿል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 20/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የመጀመርያ የስብከተ ገና ሳምንት እሁድ እና አዲሱ የዓመቱ የሥረዓተ አምልኮ አመት የመጀመርያ ሳምንት ይጀምራል። ቤተክርስቲያን በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና ክስተቶችን እና የመዳንን ታሪክ በማክበር በእዚህ የስብከተ ገና ውቅት ውስጥ ትጓዛለች። ይህን በማድረጓ ቤተክርስቲያን እናት እንደመሆኗ መጠን የህልውናችንን መንገድ ታበራለች ፣ በዕለት ተዕለት ሥራችን ትደግፈናለች እና ከክርስቶስ ጋር ወደ ሚደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ትመራናለች። የዛሬው ስርዓተ አምልኮ የመጀመርያውን “አስፈላጊ ወቅት” እንድንኖር ይጋብዘናል ፣ ይኸውም የስብከተ ገና ወቅት እና አሁን የተጀመረው አዲስ የሥረዓተ አምልኮ አመት የመጀመሪያ ሳምንት በተለይም ደግሞ ይህ የስብከተ ገና ወቅት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓለ የሚያዘጋጀን ወቅት ስለሆነ የእርሱን መወለድ በተስፋ የምንጠባበቅበት ወቅት ነው። በጉጉት መጠባበቅ እና ተስፋ ማደረግ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ (1 ቆሮ 1፡3-9 ይመልከቱ) የምንጠብቅበትን ዓላማ ያመለክታል። የምንጠብቀው ምንድን ነው? “የጌታን መገለጥ በጉጉት መጠባበቅ” (1ቆሮ. 1፡7)። ሐዋርያው ​​የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እና እንዲሁም እኛም ትኩረታችንን ከኢየሱስ ጋር በመገናኘታችን ላይ እንድናተኩር ይጋብዘናል። ለክርስቲያን በጣም አስፈላጊው ነገር ከጌታ ጋር በመሆን ከጌታ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት መፍጠር ነው። እናም በዚህ መንገድ ሕይወት ሰጪ ከሆነው ጌታ ጋር አብሮ የመቆየት ልምድ በማዳበር ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ለመኖር ከጌታ ጋር ለምናደርገው ግንኙነት ራሳችንን እናዘጋጃለን። እናም ይህ ወሳኝ ግንኙነት የሚፈጠረው የዓለም መጨረሻ ሲመጣ ነው። ነገር ግን ጌታ በየቀኑ ይመጣል ፣ ስለዚህ በእሱ ፀጋ በራሳችን ሕይወት እና በሌሎችም ሕይወት መልካም ነገሮችን እናከናውን ዘንድ ይጋብዘናል። አምላካችን የሚመጣ አምላክ ነው ፣ ይህንን መዘንጋት የለብንም፣ እግዚአብሔር የሚመጣ ፣ ያለማቋረጥ የሚመጣ አምላክ ነው። በጉጉት መጠባበቃችን ደግሞ አያሳፍረንም! ጌታ በጭራሽ አያሳፍረንም። እሱ እንድንጠብቅ ያደርገናል ፣ ተስፋችን እንዲበስል ለመፍቀድ በጨለማ ውስጥ ጥቂት ጊዜያትን እንድንጠብቅ ያደርገናል ፣ ነገር ግን በጭራሽ አያሳፍረንም። ጌታ ሁል ጊዜ ይመጣል ፣ እርሱ ሁል ጊዜ ከጎናችን ነው። አንዳንድ ጊዜ እሱ እራሱን እንዲታይ አያደርግም ፣ ነገር ግን እሱ ሁል ጊዜ ይመጣል።  እርሱ በታሪክ ውስጥ በትክክለኛው ጊዜ መጥቶ ኃጢአታችንን ሊሸከም የእኛን ስጋ ለብሶ ሰው ሆነ - የልደት በዓል በታሪክ ውስጥ የኢየሱስን የመጀመሪያ መምጣት ያስታውሳል፣ እርሱ በዓለም ላይ ለመፍረድ በመጨረሻው ቀን ይመጣል፣ እርሱ የሚመጣው የእርሱን የራሱ የሆኑ ሰዎችን ለመጎብኘት ፣ በቃሉ ፣ በቅዱስ ቁርባን ፣ በወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ውስጥ እርሱን የሚቀበሉትን እያንዳንዱን ወንድና ሴት ለመጎብኘት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ኢየሱስ በራችን ላይ ሆኖ ያንኳኳል። በየቀኑ ያንኳኳል። እርሱ በልባችን በር ላይ ነው። እሱ ያንኳኳል። ዛሬ ሊጎበኝዎት የመጣው ፣ ያለ እረፍት ፣ ልብዎን በሀሳብ ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የሚያንኳኳውን ጌታ እንዴት ማዳመጥ እንደሚችሉ ያውቃሉ? ወደ ቤተልሔም መጣ ፣ በዓለም መጨረሻ ይመጣል ፣ ነገር ግን በየቀኑ ወደ እኛ ይመጣል። እንጠንቀቅ፣ ጌታ ሲያንኳኳ በልብዎ ውስጥ የሚሰማዎትን ስሜት ይመልከቱ።

ሕይወት በከፍታዎች እና በዝቅታዎች ፣ በብርሃን እና በጨለማ የተዋቀረ መሆኑን በሚገባ እናውቃለን። እያንዳንዳችን የተስፋ መቁረጥ ፣ የውድቀት እና የጠፋን መስሎን በሚሰማን ስሜቶች ልምድ ሊኖረን ይችላል። በተጨማሪም ፣ በወረርሽኙ የታየው የምንኖርበት ሁኔታ በብዙ ሰዎች ላይ ጭንቀት ፣ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ይፈጥራል። መጽዕይ ጊዜ ጨለማ እንደ ሚሆን በማሰብ ወደ ተስፋቢስነት እና ወደ  ግዴለሽነት የመውደቅ አደጋ እንጋለጣለን። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ፊት ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለብን? ዛሬ የተነበበው የመዝሙረ ዳዊት ተመጽሐፍ እንደሚጠቁመው “ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና መጠጊያችን ነው። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና” (መዝ 33፡20-21) ይለናል። ይህ ማለት ደግሞ የምትጠብቀው ነፍስ ጌታን በልበ ሙሉነት በመጠባበቅ በሕይወታችን ጨለማ ጊዜያት ውስጥ መፅናናትን እና ድፍረትን እንድናገኝ ያስችለናል። እናም ይህ ድፍረት እና ይህ የታመነ ቃል ምን ያስከትላል? ከየት ነው የመጡት? በተስፋ የተወለዱ ናቸው። እናም ተስፋ አያሳፍረንም፣ ከጌታ ጋር የሚገጥመንን በመመልከት ወደ ፊት የሚወስደን ያ በጎነት እና የተስፋ መንፈስ ነው።

ስብከተ ገና ቀጣይነት ያለው የተስፋ ጥሪ ነው - ወደ መጨረሻው ግቡ እንዲወስደው እና ወደ ሙላቱ እንዲመራን እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እንዳለ ያስታውሰናል፣ እርሱም ጌታ ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ይገኛል፣ እሱ “ከእኛ ጋር የሚኖር እግዚአብሔር” ነው ፣ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የልባችንን በር እያንኳኳ ይጠባበቀናል፣ እሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። እግዚአብሔር እኛን ለመደገፍ ከጎናችን ይራመዳል። ጌታ አይተወንም፣ የጉዞውን ትርጉም የዕለት ተዕለት ሕይወት ትርጉም እንድናገኝ ይረዳናል ፣ በሕይወታችን ውስጥ በጭንቀት ውስጥ ሆነን ወይም ስንሰቃይ ድፍረትን ይሰጠናል። በህይወት ማእበል መካከል ፣ እግዚአብሔር ዘወትር እጁን ወደ እኛ ይዘረጋል እና ከስጋቶች ነፃ እንድንሆን ያደርገናል። ይህ ደግሞ መልካም ነው! በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ነቢዩ ለሕዝቡ “በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?” (ዘዳግም 4፡7) የሚል እጅግ ውብ የሆነ ምንባብ እናገኛለን። ማንም የለም ፣ እኛ ብቻ የምንቀርበው እግዚአብሔር ወደ እኛ የሚቀርብበት ጸጋ ነው። እግዚአብሔርን እንጠባበቃለን፣ እሱ እራሱን እንደሚገልጥ ተስፋ እናደርጋለን ፣ ነገር ግን እሱ ራሱ እኛ ራሳችንን ለእርሱ እንደምንገለፅ ተስፋ ያደርጋል!

በጉጉት የመጠባበቅ መንፈስ የነበራት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ የጀመርነው አዲሱ የስርዓተ አምልኮ አመት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ እርምጃችንን አጅባ በሐዋርያው ​​ጴጥሮስ የተመለከተውንና በውስጣችን ያለውን ተስፋ በማለምለም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ተግባር ለመወጣት ትረዳን ዘንድ አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

29 November 2020, 11:57

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >