ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቱርክ በቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ ላይ የተወሰነው ውሳኔ እንዳሳዘናቸው ገለጹ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል ለተገኙ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ከምዕመናኑ ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ ቅዱስነታቸው ለዓለም ያስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ትኩረቱን አድርጎ የነበረው ከጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1934 ዓ. ም. ጀምሮ በቤተ መዘክርነት ይታወቅ የነበረው እና በቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል የሚገኘው የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ ወደ መስጊድነት መዛወሩን የአገሪቱ ፕሬዚደንት አቶ ጣይብ ኤርዶጋን ይፋ ማደረጋቸው እንዳሳዘናቸው ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የቫቲካን ኒውስ

የቱርኩ ፕሬዚደንት ጣይብ ኤርዶጋን በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አክለው እንደ ገለጹት በመጭው ሐምሌ 17/2012 ዓ. ም. ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ሆነው በባዚሊካው ውስጥ የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚፈጽሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ባስተላለፉት መልእክት የቱርክ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን የቅድስት ሶፊያን ባዚሊካ ወደ መስጊድነት ለመለወጥ ባስተላለፉት ውሳኔ “እጅግ በጣም አዝኛለሁ” ብለዋል።

የክርስትና እምነት ተከታይ በነበሩ ንጉሠ ነገሥት ዮስጢኖስ ዘመን፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 537 ዓ. ም. የታነጸው የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ “የመለኮታዊ ጥበብ” በሚል ስያሜ የሚታወቅ መሆኑ ይታወሳል። ቀጥሎም በኦቶማን ስረው መንግሥት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1453 ዓ. ም. የኢስታንቡል ከተማ በእስላማዊ ግንባር ተዋጊዎች እጅ ሲገባ ወደ መስጊድነት ተዛውሮ እንደነበርም ይታወሳል። ቀጥሎም ከጎርጎሮሳዊያኑ 1934 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ዘመናዊ ቱርክን በመሠረቱት በክቡር ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ትዕዛዝ ወደ ሙዚዬምነት መቀየሩ ይታወሳል። አገሪቱን በፕሬዚደንትነት እየመሩ የሚገኙ አቶ ጣይብ ኤርዶጋን የመንግሥታቸው ምክር ቤት ውሳኔን ተከትለው፣ በተጨማሪም በከተማው የሚገኝ የእስልምና ተከታይ ቡድን ጥያቄን ተቀብለው የሃያ ሶፊያ ባዚሊካ እየተባለ ሲጠራ የቆየውን ጥንታዊ ሕንጻ ወደ መስጊድነት መዛወሩን ለሕዝባቸው ባሰሙት ንግግር ገልጸው በመጭው ሐምሌ 17/2012 ዓ. ም. ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ሆነው በሥፍራው የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚፈጽሙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜ ማሳሰቢያ

ለክርስቲያኖች ውህደት አጥበቀው በመሳራት ላይ የሚገኙት የቁስጥንጥንያው የውደት ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶለሜዎስ በጉዳዩ ላይ ባለፉት ቀናት በሰጡት  አስተያየት እንደገለጹት የቱርክ መንግሥት ምክር ቤት ውሳኔ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና የክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ጸብ ሊፈጥር የሚችል ጉድይ በመሆኑ የተነሳ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደ ሚገባ አክለው ገልጸዋል። የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ እንደ ቅዱስ ሥፍራ በሁለት ጎራ የተከፈለውን የዓለማችን ሕዝቦች፣ የምዕራቡን እና የምሥራቁን ዓለም ሕዝቦች ሲያስተሳስር መቆየቱን አስታውሰው፣ ሥፍራው ወደ መስጊድነት መዛወሩ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የቆየውን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የሃያ ሶፊያ ባዚሊካ ሕዝቦች በጋራ ሆነው ውበቱን ከሚያደንቁበት ሥፍራነት ታግዶ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቅራኔ እና ልዩነት እንዲስፋፋ፣ ይህም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በማለት የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቤርቶለሜዎስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

12 July 2020, 18:50