በቱርክ የሚገኝ የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ ወደ መስጊድነት መዛወሩ ተገለጸ።
ከጎርጎሮሳዊያኑ 1934 ዓ. ም. ጀምሮ በሙዚዬምነት ይታወቅ የነበረው እና በቱርክ ኢስታንቡል የሚገኝ የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ ወደ መስጊድነት መዛወሩን የአገሪቱ ፕሬዚደንት አቶ ጣይብ ኤርዶጋን የመንግሥታቸው ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ አስታውቀዋል። ፕሬዚደንት ጣይብ ኤርዶጋን አክለውም መጭው ሐምሌ 17/2012 ዓ. ም. ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ሆነው በባዚሊካው ውስጥ የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚፈጽሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የቫቲካን ዜና፤
የክርስትና እምነት ተከታይ በነበሩ ንጉሠ ነገሥት ዮስጢኖስ ዘመን፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 537 ዓ. ም. የታነጸው የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ “የመለኮታዊ ጥበብ” በሚል ስያሜ የሚታወቅ መሆኑ ይታወሳል። ቀጥሎም በኦቶማን ዘመነ መንግሥት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1453 ዓ. ም. የኢስታንቡል ከተማ በእስላማዊ ግንባር ተዋጊዎች እጅ ሲገባ ወደ መስጊድነት ተዛውሮ እንደነበርም ይታወሳል። ቀጥሎም ከጎርጎሮሳዊያኑ 1934 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ዘመናዊ ቱርክን በመሠረቱት በክቡር ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ትዕዛዝ ወደ ሙዚዬምነት መቀየሩ ይታወሳል። አገሪቱን በፕሬዚደንትነት እየመሩ የሚገኙ አቶ ጣይብ ኤርዶጋን የመንግሥታቸው ምክር ቤት ውሳኔን ተከትለው፣ በተጨማሪም በከተማው የሚገኝ የእስልምና ተከታይ ቡድን ጥያቄን ተቀብለው የሃያ ሶፊያ ባዚሊካ እየተባለ ሲጠራ የቆየውን ጥንታዊ ሕንጻ ወደ መስጊድነት መዛወሩን ለሕዝባቸው ባሰሙት ንግግር ገልጸው፣ መጭው ሐምሌ 17/2012 ዓ. ም. ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ሆነው በሥፍራው የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚፈጽሙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜ ማስጠንቀቂያ፥
የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶለሜዎስ ባለፉት ቀናት ውስጥ እንደገለጹት፣ የቱርክ መንግሥት ምክር ቤት ውሳኔ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና የክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ጸብን ሊፈጥር ይችላል በማለት ማስጠንቀቃቸው ታውቋል። የሃያ ሶፊያ ባዚሊካ እንደ ቅዱስ ሥፍራ በሁለት ጎራ የተከፈለውን የዓለማችን ሕዝቦች፣ የምዕራቡን እና የምሥራቁን ዓለም ሕዝቦች ሲያስተሳስር መቆየቱን አስታውሰው፣ ሥፍራው ወደ መስጊድነት መዛወሩ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የቆየውን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የሃያ ሶፊያ ባዚሊካ ሕዝቦች በጋራ ሆነው ውበቱን ከሚያደንቁበት ሥፍራነት ታግዶ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቅራኔ እና ልዩነት እንዲስፋፋ፣ ይህም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በማለት የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቤርቶለሜዎስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አቴን፥ "ቁጣ ቀስቃሽ ድርጊት ነው"
የግሪክ መንግሥት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ የቱርክ መንግሥት ምክር ቤት የወሰደው ውሳኔ በሲቪሉ ማኅበረሰብ መካከል ቁጣን የሚቀሰቅስ ነው ብሎ፣ በፕሬዚደንት ጣይብ ኤርዶጋን የታየው የብሔርተኝነት አቋም አገራቸውን 600 ዓመታት ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን የግሪክ መንግሥት የባሕል ሚኒስትር የሆኑኑት ወይዘሮ ሊና ሜንዶኒ አስታውቀዋል።
የሞስኮ ፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት፥ "ወሳኔው ከባድ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል"
“በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች ስሞታ ተደማጭነትን አላገኘም” ያሉት የሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ቃል አቀባይ ክቡር አቶ ቭላድሚር ሌጎይዳ፣ ኢንተርፋክስ ለተሰኘ የዜና ማዕከል ገልጸዋል። በተጨማሪም የሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት ምክትል ተጠሪ የሆኑት ሊቀ ካህን ክቡር አባ ኒኮላይ ባላሾቭ፣ የቱርክ መንግሥት ውሳኔ በመላው የሰው ልጅ ስልጣኔ ላይ ከባድ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል በማለት ገልጸዋል።
ኤርዶጋን፥ "ማንኛውም ነቀፋ በነፃነታችን ላይ የሚቃጣ ጥቃት ነው"።
ከየአቅጣጫው ለሚደርሳቸው ነቀፋ እና ትችት መልሳቸውን የሰጡት የቱርክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጣይብ ኤርዶጋን እንዳስታወቁት፣ ብሔራዊ ሉዓላዊነት ማስከበር የአገራቸው መንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለው በቱርክ ዋና ከተማ ኢሳታንቡል የሚገኝ የሃያ ሶፊያ መስጊድ በሩን ለእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች እምነቶች ተከታዮችም ክፍት ያሚያደርግ መሆኑን አስታውቀው፣ ማንኛውም ነቀፋ እና ትችት በነፃነታቸው ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ነው በማለት ገልጸዋል። ከመንግሥት ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ የደገፉት በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሃያ ሶፊያ ሙዚዬም ፊት ለፊት ተገኝተው “አላሁ አክበር” ወይም “እግዚአብሔር ታላቅ ነው” በማለት ደስታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል። በቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል የታሪካዊ ቦታዎች ጥበቃ አስተባባሪ ማኅበር ተጠሪ በበኩላቸው፣ የሃያ ሶፊያን ሕንጻ እንደ ሙዚዬምነት ማቆየቱ የሕሊና ወቀሳን ያስከትላል በማለት ገልጸዋል።
ዩኔስኮ፥ "የቅድስት ሶፊያ ባዚሊካ የጋራ ውይይት ማዕከል ሆኖ ቢቆይ መላካም ነበር"።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፣ ዩኔስኮ በበኩሉ የቱርክ መንግሥት ውሳኔ እንዳሳዘነው ገልጾ፣ ውሳኔው የማዕከሉን የጋራ ውይይት ማዕከልነት እና ታሪካዊ እሴትነቱን መሉ በሙሉ የሚቀይር መሆኑን አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መገናኛ ክፍል እንዳስታወቀው፣ በእያንዳንዱ አገር የሚገኝ እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ሥር ተመዝግበው የሚገኙ ታሪካዊ ሥፍራዎች ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግባቸው መቆየት እንዳለባቸው አስታውቆ፣ ለውጥ ቢደረግባቸው እንኳ በቅድሚያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ጉዳዩ የሚመለከተውን ክፍል ማሳወቅ ተገቢ ነበር በማለት ቅሬታውን ገልጿል።