ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘናቸውን ገለጹ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በጥቅምት 23/2012 ዓ.ም. በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ መስረቱን አድርጎ የነበረ አስተንትኖ ካደረጉ በኃላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት  ደንግል ማርያም ከሚቀርቡ የመማጸኛ ጸሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነው መልአኩ ገብርኤል ማርያምን ያበሰረበትን  ወቅት በማሰብ፣ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን እንዳበሰራት እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መጸነሱን በሚዘክረው የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኃላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እንደ ገለጹት “በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ጥቃት እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል።

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ላይ በደረሰው ጥቃት በጣም አዝኛለሁ። ለዚህች ቤተክርስቲያን እና ለፓትርያርኳ፣ ለተወደደው ወንድሜ አቡነ ማቲያስ ከሁላችሁም ጋር መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። በእዚያች ሀገር በተፈፀሙ ጥቃቶች ሰለባ ለሆኑ ሰዎች እንድትፀልዩ እማጸናችኋለሁ”።

በወቅቱ እርሳቸውና መላው ምዕመን በእዚህ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ” የሚለውን ጸሎት በጋራ መድገማቸው ከስፍራው ለቫቲካን ዜና ከደረሰው ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል። 

በሰኔ 24/2010 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተመሳሳይ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ የሚገኙ በኢትዮጲያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ለ20 ዓመታት ያህል የነበረው ፍጥጫ አብቅቶ ወደ ሰላም ጎዳና መመለሳቸው ተስፋ ሰጪ የሆነ አጋጣሚ መሆኑን ቅዱስነታቸው በአድናቆት መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጲያ እና የኤርትራ መንግሥታት ከበርካታ አመታት በኃላ በመካከላቸው ሰላም ለመፍጠር መስማማታቸው በጣም የሚያበረታታ እና መልካም የሆነ ዜና መሆኑን በወቅቱ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው

በበርካታ ግጭቶች መካከል በእውነቱ ታሪካዊ ተብሎ ሊገለጽ በሚችል መልኩ ተነሳሽነትን በመውሰድ፣ በእርግጥ ይህንን መልካም ዜና ነው ለማለት ይቻላል፣ ከሃያ አመታት በኃላ የኢትዮጲያ እና የኤርትራ መንግሥታት ስለሰላም መንጋገር መጀመራቸው መልካም የሚባል ጅምር ነው።  የእዚህ ዓይነቱ መልካም ግንኙነት በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ ሁለቱ ሀገራት በአጠቃላይ ለመላው አፍሪካ የተስፋ ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችል አጋጣሚ ነው።

ይህንን እርቀ ሰላም ተከትሎ የኢትዮጲያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ዶክር አብይ አህምድ በጥር 13/2011 ዓ.ም በቫቲካን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚንስትር በሆኑት በዶክተር አብይ መሪነት በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዲፈጠር፣ ብሎም በአጠቅላላው በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እንዲረጋገጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ እያበረከቱትት ለሚገኘው ከፍተኛ አስተዋጾ ቅዱስነታቸው ምስጋና ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጲያ ፌደራላዊ ዲሞክራስያዊ ሪፖብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጲያ በትህምርት እና በጤና ዘርፍ እያበረከተች የምትገኘውን ከፍተኛ አስተዋጾ ማድነቃቸውን መዘገባችንም ይታወሳል። 

 

03 November 2019, 14:13