ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ         ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ  

የወቅቱን የአገራችን ሁኔታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያስተላለፈችው ሐዋርያዊ መልዕክት።

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና አርአያ ተፈጥሮአል፤ ስለዚህ ክብር አለው።

የወቅቱን የአገራችን ሁኔታ በተመለከተ

“ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ 14፡27)።

 1. እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ይህንን መልእክት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለምእመኖቻችን ሁሉ ካለብን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ኃላፊነት በመነሣት ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ልናስተላልፍ እንወዳለን። ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለያዩ የአገራችን ቦታዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልልና በተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የደረሰው ሁከትና የሞት አደጋ እንዲሁም የመንገድ መዝጋትና ንብረት ማውደም ሥራ በእጅጉ አሳዝኖናል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርስ ጥቃትና ዝርፍያ ምንም ዓይነት ማብራርያ ቢሰጠው ልንቀበለው የማንችል ኢ-ሰብአዊ ወንጀል እንደሆነ በአጽንኦት ልንገልጽ እንወዳለን። በግለሰቦችም ይሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚታለለፉ መልእከቶች ምንም ዓይነት አንድምታ ቢኖራቸው ዜጎች በመቃወምም ሆነ በመደገፍ ጥያቄአቸውን በሠለጠነ እና ሌሎችን በምንም ዓይነት መልኩ በማይጎዳ መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። አንድን የፖለቲካ ቡድን ወይም አክቲቪስት መደገፍ ሌላውን መቃወም በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ያለ ሂደት ነው። ነገር ግን የዘር ሐረግ እየመዘዙ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ በፖለቲካዊ ርእዮተዓለምም ሆነ በሰብአዊነት ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው። ከኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብና እሴት ከሃይማኖታዊ መርሕም ፍጹም የወጣ ነው። ምክንያቱም ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት አልፏል፤ የዜጎችና የአገር ንብረት ወድሟል፤ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ተገድቧል። ከዚህ በተጨማሪ የሥራ አጥነት ችግር ለአገራችን እጅግ ፈታኝ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ድርጅቶች ሥራ ለማቆም በመገደዳቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ ይህ ነው የማይባል ኪሳራ ደርሷል። የጸጥታ አካላትም በቂ ዝግጅት አድርገው አመጽ ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ ሲሄድ በጊዜ በመቆጣጠር ሊያስቆሙ ባለመቻላቸው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዳልተወጡ ያመለክታል።
 2. የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና አርአያ ተፈጥሮአል፤ ስለዚህ ክብር አለው። ይህ ክቡርነት ባሕርያዊና ስለሆነ በማኅበራዊ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገለጡና የሚተገበሩ መሠረታዊ የሆኑ መብቶችና ኃላፊነቶችን ያካትታል። ማናቸውም በሰው ልጅ ላይ የምንፈጽመው በደል በእግዚአብሔር ላይ የተነጣጠረ ነው። በሃይማኖቱ፣ በዘሩ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃው፣ ወዘተ.። ዛሬ የምናየው በየቦታው እየተከሰተ ያለው መንገድ መዝጋት፣ ግለሰቦችን ማስፈራራት፣ በተጎጂው ላይ ብቻ የተነጣጠረ ሳይሆን እሱን ከፈጠረው ከሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጋር የተያዘ ግብግብ ነው “ይህ ሰው አንተ የሰጠኸን መሬት፣ ቦታ፣ የተፈጥሮ ሀብት አይገባውም፤  የእኛን ፍቅር፣ የእኛን ደስታ፣ የእኛን ሐዘን፣ የእኛን ችግር ሊጋራ የተገባ አይደለም። ተሳስተሃል” ማለት ነው።
 3. የጋራ ጥቅም ላይ በማተኰር እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱ፣ በዙርያውና በሩቅ ለሚገኙ ወገኖቹ በማሰብ በትስስር የመኖርን ምሥጢር በመቀበል መኖርን መለማመድ ይኖርበታል። ይህ ከነጠላ ግለሰቦች እርካታ ድምር የላቀ ነው። አሁንም ከጎሣና ከብሔር፣ ከራስ ሃይማኖት እርካታ በላቀ የአገርና የሰው ልጅ ሁሉ እርካታ የበለጠ መሆኑን መረዳ ያስፈልጋ። የጋራ የመሆኑ ምክንያት የማይከፈል/የማይቆራረጥ በመሆኑ ነው። የጋራ ጥቅም የሚጎለብተውና የሚያድደገው፤ ሊደረስበት/ተጨባጭ ሊሆን የሚችለው በጋራ ብቻ ነው፤ የሚጨምርውም በጋራ ብቻ ነው፤ አገልግሎቱም በመልካምነቱ ሊጠበቅና ሊያድግ የሚችለው እንዲሁም ለሁሉም ወይም ለሰፊው ኅብረተሰብ በተሳለጠ መንገድ አገልግሎት መስጠት የሚችለው በጋራ ነው። ሰላም የጋራ ጥቅም እሴት እንደመሆኑ መጠን በተጋራነውና በተካፈልነው መጠን ሥር ይሰድዳል፤ ይጎለብታል፤ ያድጋል፤ ለሁላችንም በረከት ይሆናል። ለኢኮኖሚ፣ ለባሕል፣ ለሃይማኖት፣ ለፖለቲካ፣ ለሁሉም ዘርፍ መጠንከርና ማደግ መሠረት ይሆናል።
 4. ዛሬም አበክረን የምንለው ሁከት ሁከትን ይወልዳል እንጂ ሰላምንም ሊያመጣ አይችልም። ይልቁንም ዛሬ ኃይልን፣ ጉልበትን፣ አመጽን ተጠቅሞ መልስ ያገኘ ቡድን ወይም አካል ነገ በተራው በኃይልና በጉልበት የሚመጣ ሌላ ወገን ይጠይቀዋል።  “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” (ማቴ 26፡52)። ሰላምና ዕርቅ የሚሰፍነው በመካከር፣ በመቀባበል፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ብቻ ነው። ከዚህ ጥቃትና አመጽ ጀርባ ሥር የሰደደ የሞራል ውድቀት እንዳለ አመላካች በመሆኑ እንደ እምነት ተቋም ዜጎችን በጥሩ ግብረገብ በማነጽ ብዙ መሥራትና ማገልገል እንዳለብንም ለእኛም የጥሪ ደወል ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን በመልካም ሥነምግባር ኮትኩቶ የማሳደግ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።
 5. ባለፉት ቀናት በተፈጠሩ ሁኔታዎች ምክንያት በእመት ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ የቤተክርስቲያን ሥጋት የሁላችንም ሥጋት ነው። ይልቁንም ከአመጽ እና ከጥፋት ሥራ ወጣቶች ሲታቀቡ በሥጋት ውስጥ የነበሩ ሁሉ ልባቸው ያርፋል። ስለሆነም በተለይ ወጣቶች! አገራችን የሃይማኖት አገር እንደመሆኗ መጠን ከማናቸውም አመጽ እንድትርቁ፣ በራሳችሁም ሆነ ሌሎች በሚያመልኩባቸውን የእምነት ተቋማት ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳትፈጽሙ እና ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የሚጎዳ ተግባር ላይ በመሳተፍ ኅሊናችሁን አንዳታጎድፉ አባታዊ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን።
 6. በመጨረሻም፤ ለእርስ በርስ መተማመን፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ፣ ቅሬታ እና ተቃውሞ ቢኖረን በሠለጠነ እና ምንም ዓይነት ጥፋት በማያደረስ መልኩ ሕግን ተከትሎ ማቅረብን ባሕላችን እንድናደርግ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን። አሁንም “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ 14፡27)።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

             

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል                                                                          

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ                                                                          

 

        

26 October 2019, 10:31