ፈልግ

በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ 2020 ዓ.ም ደቡብ ሱዳንን እንደ ሚጎበኙ ገለጹ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በጥቅምት 30/2012 ዓ.ም. በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ መስረቱን አድርጎ የነበረ አስተንትኖ ካደረጉ በኃላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት  ደንግል ማርያም ከሚቀርቡ የመማጸኛ ጸሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነው መልአኩ ገብርኤል ማርያምን ያበሰረበትን  ወቅት በማሰብ፣ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን እንዳበሰራት እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መጸነሱን በሚዘክረው የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኃላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እንደ ገለጹት እንደ አወሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመጪው 2020 ዓ.ም ደቡብ ሱዳንን እንደ ሚጎበኙ የገለጹ ሲሆን በእዚያች አገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን የወንድማማችነት መንፈስ ይጠናከር ዘንድ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማደረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች በአለፉት አመታት በርካታ ስቆቃ እንደ ደረሰባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው መጻይ ጊዜያቸው ብርህ እና በሰላም የተሞል ይሆን ዘንድ ተስፋ በማደረግ ዘላቂ ሰላም በአገሪቷ እንዲረጋገጥ ጥንክሮ መሥራት እንደ ሚገባ ቅዱንስታቸው ጨምረው ገልጸዋል። ስለሆነም ኃላፊነት የተጣለባቸው ግለሰቦች በሙሉ በአገሪቱ መልካም ስምምነት እንዲፈጠር ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል። በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ እርቅ ለማምጣት የሚደርገውን ጥረት ገቢራዊ ለማደረግ ይችላ ዘንድ ከደቡብ ሱዳን ሕቦች ጋር አብሮ እንደ ሚጓዝ ተስፋዬ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ለተወደደው የደቡ ሱዳን ሕዝብ እንጸልይላቸው ካሉ በኋላ “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ!” የሚለውን ጸሎት በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ ምዕመናን ጋር በመሆን መጸለያቸው ተገልጹዋል። 

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት በጋራ ከሚያዚያ 2-3/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሁለት ቀን ሱባሄ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን  የሱባሄው ዋና ዓላማ ደግሞ በአገሪቷ እየተካሄደ የነበረው የእርስ በእስር ግጭት ተወግዶ ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲፈጥር የአገሪቷ ባለስልጣናት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመንፈሳዊ ሕይወት እገዛ እውን እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ እና ልዩ  ዓላማውም ደግሞ ከቤተክርስቲያን በኩል በቀረበው ሐሳብ መሠረት የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር ሆነው በጸሎት እና በአስተንትኖ የሚተባበሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር፣ በመካከላቸው የመከባበርን እና የመተማመንን መንፈስ ለማሳደግ፣ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ሰላምን እና ብልጽግና ያመጡ ዘንድ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጋራ በመሥራት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ  የሁለት ቀን ሱባሄ ነበር።

በዚህ የሁለት ቀን ሱባሄ ላይ የደቡብ ሱዳን ሪፖብሊክ ፕሬዚዳንትን የሆኑትን ክቡር ሳልቫ ኪር ጨምሮ  አራቱ የደቡብ ሱዳን ሪፖብሊክ ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ሪካ ማቻር ቴኒ ዱርጎን፣ ጄምስ ኢጋ፣ ታባን ደንግ ጋይ እና ርብቃ ኛንደንግ ደ ማቢዮር ተሳታፊ እንደ ነበሩ የተገለጸ ሲሆን የዓለም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሕብረት መሪ እና የካንተርበሪ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢይ እና  የስኮትላንድ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን መሪ ክቡር ጆን ቻልመርስ ተሳታፊ እንደ ነበሩ ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ካደረጉት አስተንትኖ በመቀጠል የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በወቅቱ በእዚያው የተገኙ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በአገሪቷ ሰላም እንዲፈጠር ቁርጠኛ ሆነው መሥራት እንደ ሚገባቸው ለመማጸን በማሰብ በእያንዳንዳቸው እግር ሥር ወድቀው ጫማዎቻቸውን መሳማቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ የቅዱስነታቸው ተግባር በአንዳንዶቹ ከዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል ስነ-ሥዓት ውጪ የሆነ ተግባር በመሆኑ የተነሳ ወቀሳ ያስከተለ ተግባር ሲሆን በሌላ ወገን የሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ቅዱስነታቸው ሰላም በደቡብ ሱዳን እንዲመጣ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት በመነጨ መልኩ በታላቅ ትህትና ተሞልተው የፈጸሙት በጎ እና በአብነት ሊጠቀስ የሚገባው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን በጸሎተ ሐሙስ ማታ የደቀ-መዛሙርቱን እግር ካጠበበት ሁኔታ ጋር በማዛመድ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሊፈጽመው የሚገባው የትህትና ተግባር እንደ ሆነ በማቅረብ ምስጋናቸውን ለቅዱስነታቸው ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 November 2019, 11:30