ፈልግ

“የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት፣ “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋሙን አወደሱ።

በሐይማኖት ተቋማት መካከል ሕብረት እና መቻቻል እንዲኖር የሚያሳስብ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ፣ በውስጡ የያዛቸውን መልካም ዓላማ ተግባራዊነት በቅርብ የሚከታተል አዲስ ኮሚቴ መሰየሙ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን ያስደሰታቸው መሆኑን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከጥር 26/28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ፣ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በተሰበሰቡበት ወቅት “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ ማርቀቃቸው የሚታወስ ነው። በሐይማኖት  መሪዎች የተረቀቀውን እና ታሪካዊ ነው የተባለው ሰነድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት አል ጣይብ ፈርመው ማጽደቃቸውም ይታውሳል።

    

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምስጋና፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ. ም. አዲስ የተሰየመውን የኮሚቴ አባላት በመልዕክታቸው አበረታተዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችንም ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በተግባር ለመግለጽ ላሳዩት ጽኑ ፍላጎት ምስጋናቸውን አቅርበው በሌሎች የዓለማችን ክፍሎችም ተመሳሳይ ፍላጎት እንደሚኖር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው “በዓለማችን ክፋት፣ ጥላቻ እና መለያየት ተጋንኖ የሚነገ ቢሆንም ተደብቀው የሚገኙ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የፍቅር፣ የወንድማማችነት እና የሕብረት ጎዳናዎች፣ በመልካም ውይይቶች ሊገኝ የሚችል የአንድነት ተስፋ፣ አንዱ ሌላውን ይበልጥ በማወቅ እና በመረዳት የወንድማማችነት መንፈስ የሚገኝበት ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት የሚያስችል መልካም ፈቃድ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ አለ” ብለዋል።

የኮሚቴው መዋቀር ትምህርታዊ አንደምታው፣

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት እና አዲስ የተመረጠው ኮሚቴ አባል የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ ከቫቲካን ሬዲዮ በኩል ለቀርበላቸው ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት የኮሚቴው መዋቀር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ገልጸው፣ በዓለም ዙሪያ ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማስተማር ሥራ ላይ የሚሰማሩ መምሕራንን በመርዳት ትልቅ እገዛን ማድረግ ይችላል ብለዋል። የኮሚቴው መዋቀር እርስ በእርስ የመገናኘት እና የመተዋወቅ፣ የወንድማማችነት እና የሰላም ባሕል፣ በትምህርት ተቋማት እና በስልጠና ማዕከላት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በአዲስ መልክ እንዲካተቱ በማድረግ ትልቅ ዕድልን ያመቻቻል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ሚገል በማከልም ይህን ዕድል ማግኘት ማለት ደግሞ ተቋማቱ በየበኩላቸው ሃላፊነትን ወስደው ሰነዱን በሁሉንም አቅጣጫዎች በሚገባ ማጥናትን እና በማስተንተንን እንዲሁም መከታተልን ይጠይቃል ብለዋል። አዲስ የተቋቋመው ከፍተኛ ኮሚቴ፣ የሰነዱ ጭብጦች አገር አቀፍን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችን፣ ምሁራንን፣ የፖለቲካ መሪዎች በተለይም ወጣቶችን ማሳተፍ የሚቻልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ለይቶ ማወቅ ይጠበቅበታል ብለዋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት እና አዲስ የተመረጠው ኮሚቴ አባል ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ በገለጻቸው፣ ኮሚቴውን ለማዋቀር በወሰዱት መልካም እርምጃ የአቡ ዳቢ ልዑል፣ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያንን ከልብ አመስግነዋቸዋል።

እምነቶችን አንድ አድርጎ የመመልከት አደጋ፣

ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ በተጨማሪም የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለውን ልዩነት በመቀነስ ወደ አንድነት እና ወደ መመሳሰል የሚያመራ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ እምነቶች በሙሉ አንድ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከት ሳይሆን የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች፣ በሚከተሉት መንገድ እግዚአብሔርን ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ፣ ሰዎች የሚገኙባቸውን የሐይማኖት ተቋማት ሳይለይ፣ ነገር ግን ወንድማማችነትን እና ፍቅርን ለማሳደግ ባላቸው በጎ ፈቃድ፣ በሰብዓዊ ማንነታቸውም እኩል መሆናቸውን በግልጽ የሚያስረዳ መሆኑን አስገንዝበዋል። ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ በማከልም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማንነቷን እሴቶች በማስታወስ፣ ሁል ጊዜም ቢሆን በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለው የጋራ ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው ታደርጋለች ብለዋል። በማሕበረሰቦቻችን ውስጥ የሚታይ ብዝሃነት በሐይማኖታዊ ተቋማትም ውስጥ የራስን ማንነት በሚገባ በማወቅ፣ ከሌሎች የሐይማኖት ወገኖች ጋር እውነተኛ ውይይት እንዲደረግ የሚጋብዝ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 August 2019, 16:19