ፈልግ

“የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት፣ “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት፣ 

ሰብዓዊ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ኮሚቴ መዋቀሩ ተገለጸ።

የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከጥር 26/28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ በተሰበሰቡበት ወቅት የተፈረመውን “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተፈጻሚነት የሚከታተል ኮሚቴ መቋቋሙን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ቤነዴታ ካፔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ታሪካዊ ነው የተባለው ሰነድ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል አዛር ታላቁ ኢማም በሆኑት በአል ጣይብ መካከል መፈረሙ ይታውሳል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰነዱ በቀዳሚነት በሐይማኖት ተቋማት መካከል ትብብር እና መቻቻል እንዲኖር የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል። ይህን በጎ ዓላማ በተግባር ለመግለጽ የሚያግዙ ሃሳቦችን የያዘ፣ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚለውን ሰነድ ስብሰባውን የተካፈሉት የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ተስማምተው ማርቀቃቸው ይታወሳል። ሰነዱ የያዛቸውን ሃሳቦች ተግባራዊነት ተከታትሎ እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ የስምምነት ሰነዱ እንደሚጠይቀው ሁሉ፣ በዛሬውም ሆነ በመጭው ትውልድ መካከል ሰላም እንዲነግስ፣ እርስ በእርስ በመከባበር አብሮ የመኖርን መንፈስ ለማሳደግ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ በርትተው መሥራት እንዳለባቸው የኮሚቴው መግለጫ አሳስቧል።

የአንድነት ጎዳናን መከተል፣

በመግለጫው ላይ ሃሳባቸውን ያሠፈሩት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል፣ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን እንደገለጹት የኮሚቴው መዋቀር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል የስምምነት ሰነድ ላይ የተቀመጡትን ሃሳቦች፣ በተለይም ለዓለም ሰላም የሚደረገውን የጋራ ጥረት ለማጠናከር በማሰብ ነው ብለዋል። በሰነዱ ውስጥ የተካተቱ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ፣ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎችን የሚያሳትፉ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች የሚካሄዱ መሆኑ ታውቋል። የአስተባባሪው ኮሚቴ የሥራ ድርሻ በተለያዩ አገሮች ሕዝቦች መካከል የሚደረገውን የመከባበር እና አብሮ የመኖር ጥረቶችን ማስተባበር እና መከታተል እንደሚሆን ታውቋል። የኮሚቴው ተጨማሪ ተግባር፣ ከዚህ በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል አዛር ታላቁ ኢማም የሆኑት አል ጣይብ የጎበኙትን እና በአቡ ዳቢ ከተማ የሚገኘውን የአብርሃማዊ ቤተሰብ ሙዜም ግንባታን በቅርብ መከታተል እንደሚሆን ታውቋል። እነዚህን እና ሌሎች መጠነ ሰፊ የሆኑ ሥራዎችን የሚከታተል እና የሚያስፈጽም ተጨማሪ የኮሚቴ አባላት ወደ ፊት የሚመረጡ መሆናቸው ታውቋል።

የኮሚቴው አባላት፣

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል አዛር ታላቁ ኢማም በሆኑት በአል ጣይብ መካከል የተፈረመውን “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተፈጻሚነት የሚከታተሉ የኮሚቴ አባላት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በግብጽ የአል አዛር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሁሴን ማራሳዊ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የግል ጸሐፊ የሆኑት፣ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ላዚ ጋይድ፣ የታላቁ ኢማም የሕግ አማካሪ የሆኑት መሐመድ መሐሙድ አብደል ሳላም፣ የአቡ ዱቢ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ክፍል ፕሬዚዳንት የሆኑት መሐመድ ካሊፋ አል ሙባረክ፣ የሙስሊም አባቶች ጉባኤ ጠቅላይ ዋና ፀሀፊ፣ ዶክተር ሱልጣን ፋይሳል አል ሩማይቲ እና ደራሲ ክቡር ያስር ሀሬብ አል ሙሃይሪ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 August 2019, 15:43