ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የራሻ ፌዴረሽን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከቪላድሚር ፑቲን ጋር በቫቲካን ተገናኙ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 27/2011 ዓ.ም የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከቪላድሚር ፑቲን ጋር በቫቲካን ተገናኝተው በተለያዩ ወቅታዊ የዓለማችን ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ የራሻው ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በቫቲካን ያደረጉት ስድስተኛው ጉብኝት ሲሆን በተመሳሳይ መልኩም ይህ ጉብኝት የራሻው ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ተገናኝተው ሲወያዩ ይህ ሦስተኛው ግንኙነት መሆኑ ተገልጹዋል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 27/2011 ዓ.ም ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን በተመለከተ የቫቲካን ፕሬስ ቢሮ ባወጣው መግለጫ እንደ ገለጸው ይህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በትላናትናው እለት ማለትም በሰኔ 27/2011 ዓ.ም በቫቲካን ተገናኝተው ለአንድ ሰዓት ያህል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መመካከራቸውን መግለጫው ያፍ ያደረገ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በቫቲካን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑ ከካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና ቫቲካንን በመወከል ከሌሎች አገራት ጋር የሚደርገውን ማነኛውንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ፖውል ሪቻርድ ጋላገር ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውም ተገልጹዋል።

የተወያዩባቸው ጉዳዮች

የቫቲካን ፕሬስ ቢሮ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 27/2011 ዓ.ም በቫቲካን ተገናኝተው መወያየታቸውን በተመለከተ ባወጣው ኦፊሴሊያዊ መግለጫ እንደ ገለጸው በግንኙነቱ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ማለትም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን ያደረጉት ውይይት በመግባባት መንፈስ የተደረገ ውይይት መሆኑን የገለጹ ሲሆን በሁለቱም አገራት ማለትም በቫቲካን እና በራሻ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጸ ሲሆን በተለይም በወቅቱ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘው እና ከመላው ዓለም ለተውጣጡ በተለያየ ዓይነት በሽታ የተጠቁ ሕጻናትን ተቀብሎ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው ባቢኖ ጄዙ (ሕጻኑ ኢየሱስ) በመባል በሚታወቀው በቅድስት መንበር ሥር በሚተዳደረው የሕጻናት ሆስፒታል እና በራሻ ፌዴሬሽን ውስጥ ከሚገኘው ተመሳሳይ አገልግሎት ከሚሰጠው የሕጻንት ሆስፒታል ጋር ትስስር መፍጠር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ በመግለጫው ተገልጹዋል።

በራሻ ፌዴሬሽን ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያ ምዕመናንን ሁኔታ በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን መነጋገራቸው የተገለጸ ሲሆን በራሻ ፌዴሬሽን ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ተገቢ የሆነ መስተንግዶ ይደረግላቸው ዘንድ የሚያስችል ውይይት ማደርጋቸውም ተገልጹዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 27/2011 ዓ.ም በቫቲካን ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ባደረጉት ውይይት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ከፍተኛ አደጋ በተመለከተ ጉዳዩን አንስተው መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ፖሌቲካዊ የሆኑ ትኩሳቶችን በተመለከተ መነጋገራቸውን የቫቲካን ፕሬስ ቢሮ ባወጣው ኦፊሴላዊ መግለጫ ይፋ ያደረገ ሲሆን በተለይም ደግሞ የሶሪያ፣ የዩክሬን እና የቬንዙዌላን ወቅታዊ ሁኔታዎች በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጹዋል።

ከእዚህ ቀደም የነበሩ ግንኙነቶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን ከእዚህ ቀደም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ  እ.አ.አ. በ2013 ዓ.ም የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ቪላድሚር ፑቲን ጋር በቫቲካን መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል ደግሞ እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ላይ በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድባት በነበረው የሶሪያን እና በአጠቃላይ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ፣ እንዲሁም በዩክሬን እና በራሻ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማብረድ እና ሰላም ማስፈን የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይቻል ዘንድ ተገናኝተው መወያየታቸው ተገልጹዋል።

የራሻ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቪላድሚር ፑቲን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በፊት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከነበሩት ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ጋር እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም በቫቲካን መገናኘታቸው ይታወሳል።

ቫቲካን እና የራሻ ፌዴሬሽን የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክረው የቀጠሉት እ.አ.አ 1989 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ እና በወቅቱ የተባበሩት ሶቪዬት ሕብረት ፕሬዚዳንት በነበሩት ሚካሄል ጎርቫቾ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ግንኙነት እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ይህ ግንኙነት በአንድ የካቶሊክ ቤተክርቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና በአንድ የራሻ ፕሬዚዳንት መካከል የተደረገው የመጀምሪያው እና ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት እንደ ነበረ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል። ይህንን ታሪካዊ ግንኙነት ተከትሎ ቫቲካን እና ራሻ ይፋዊ የሆነ ኦፊሴላዊ ግንኙነት ጀምረዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የራሻ ፌዴረሽን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከቪላድሚር ፑቲን ጋር በቫቲካን ተገናኙ
04 July 2019, 11:19