ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “መሪዎች አስተዋዮች፣ ርህሩህ እና ይቅር ባይ መሆን ይኖርባቸዋል” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት በየካቲት 24/2011 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን?” በሚለው በሉቃስ ወንጌል 6፡39-45 ላይ በተጠቀሰው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “መሪዎች አስተዋዮች፣ ርህሩህ እና ይቅር ባዮች መሆን ይገባቸዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 24/2011 ዓ.ም በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አስናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ አጠር ያለ ምሳሌዎችን በማቅረብ የእርሱ ደቀ መዛሙርት በጥበብ መኖር የሚያስችላቸውን መንገድ ያመለክታቸዋል። “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን?” (ሉቃ 6፡39) ብሎ ጥያቄ በማንሳት አንድ መሪ ዕውር መሆን እንደ ማይገባው፣ ነገር ግን በተቃራኒው በደንብ ማየት እንዳለበት አጽኖት በመስጠት የተናገረ ሲሆን ያም ማለት ደግሞ አንድ መሪ ጥበብ ሊኖረው እንደ ሚገባው በመግለጽ አለበለዚያ ግን በአደራ በተሰጡት ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደ ሚችል ይገልጻል። ኢየሱስ የማስተማር ኃላፊነት ያላቸውን ወይም ትዕዛዝ የመስጠት ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች፡ የነፍስ ጠባቂ የሆኑ እረኞች፣ የሲቪክ ባለስልጣናትን፣ ሕግ አውጪዎችን፣ መምሕራንን፣ የቤተሰብ መሪዎች የተሰጣቸውን የኃላፊነት ድርሻ በሚገባ እንዲገነዘቡ እና ሰዎችን ለመምራት የሚያስችላቸውን  ትክክለኛውን መንገድ ሁልጊዜ እንዲያስተውሉ በጥብቅ ያሳስባል።

“ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ በደንብ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል” (ሉቃስ 6፡40) የሚለውን አገላለጽ በመጠቀም ኢየሱስ እርሱ ራሱን ሰዎች ሊከተሉት የሚገባው አብነት ያለው መምህር እና መሪ አድርጎ ራሱን ያቀርባል። እሱ የእርሱን ምሳሌ እና አስተምህሮዎች በመከተል አስተማማኝ እና ጥበበኛ መሪ እንዲሆኑ ያቀረበው ጥሪ ነው። እናም ይህ ትምህርት በተራራው ስብከት ውስጥ ከሁሉም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት የተጠቀሰውን፣ ለባለፉት ሦስት ሳምንታት ይህል ቅዱስ ወንጌል ለእኛ ያቀረበውን የትህትና እና የምሕረት ባሕሪያትን በመላበስ ሐቀኛ፣ ትሁት እና ፍትሀዊ እንድንሆን ከቀረበልን ጥሪ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ እብሪተኛ እና ግብዝ እንዳንሆን የሚያበረታታ ሌላ ጉልህ ሐረግ እናገኛለን። “በወንድምህም ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” (ሉቃስ 6፡41)። ብዙ ጊዜ የሌሎች ሰዎችን ጉድለቶች እና ኃጢአቶች ማስተዋል እና ማረም ቀላል ነው፣ የራሳችንን ባሕሪይ ግን መመልከት ከባድ ነው። ፈተናው የሚጀምረው ደግሞ ራሳችንን በአግባቡ መመልከት ሲከብደን ነው፣ የራሳችንን ስህተቶች እንደ ስህተት አድርገን አንቆጥራቸውም፣ ነገር ግን የሌሎች ሰዎችን ጉድለቶች በመመልከት ብዙን ጊዜ ሰዎች ላይ በመፍረድ ልባቸውን በሚገባ ሳንመለከት መፍረድ ይቀናናል። በጥበብ በተሞላ ምክር ሌሎችን መርዳት ሁል ጊዜ ጠቃሚ ነው፣ ነገር ግን የባልንጀሮቻችንን ጉድለት ስንመለከት እና ማስተካከያ ስንሰጥ እኛም ጉድለቶች እንዳሉብን ማወቅ አለብን። በዚህ መንገድ ከሄድን ደግሞ የምንታመን ሰዎች እንሆናለን፣ በትህትና የምንመላለስ ሰዎች እንሆናለን፣ የፍቅር መስካሪዎች እንሆናለን።

ዐይኖቻችን ነጻ መሆናቸውን ወይም ደግሞ በጉድፍ መሸፈናቸውን ወይም አለመሸፈናቸውን እንዴት ለማወቅ እንችላለን? ይህንን በተመለከተ ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ይለናል “ክፉ ፍሬ የሚያፈራ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያፈራ ክፉ ዛፍ የለም።  ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቀምም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም” (ሉቃስ 6፡43-44) ይለናል። ፍሬውም በተግባራት እና በተጨማሪም በቃላቶች ጭምር ይገለጻሉ። ከቃላቱ በመነሳት የዛፉን ጥራት ማወቅ ይቻላል። መልካም የሚናገር ሁሉ በልቡ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር አውጥቶ በአፉ ይናገራል፣ ክፉ የሆነ ሰው ደግሞ በውስጡ ያለውን ክፉ ነገር አውጥቶ ይናገራል፣ በውስጡ ያለውን ክፉ ነገር በአፉ መናገር ይለማመዳል፣ ያጉረመርማል።

በዛሬው እለተ (የካቲት 24/20111 ዓ.ም) ሰንበት የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ለእምነታችን ጉዞ ጠቃሚ የሆነ አቅጣጫ ይጠቁመናል፣ እያንዳንዱን ምርጫ እና እያንዳንዱን እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ጤናማ ውሳኔ እንድናደርግ ይጋብዘናል። ማስተዋል ከጌታ የሚሰጥ ስጦታ ነው፣ እናም በቋሚነት መጸለይ ያስፈልጋል፣ በተመሳሳይም በትህትና እና በትዕግስት ሌሎችን የማዳመጥ እና የመረዳት ችሎታ ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ ላይ ሆነን ጌታን መከተል እንችል ዘንድ እንድትረዳን የእመቤታችን የቅድስት ድምግል ማርያምን አማላጅነት መማጸን ያስፈልጋል።

 

03 March 2019, 14:47