ፈልግ

የዓለም የውሃ ቀን ተከበረ የዓለም የውሃ ቀን ተከበረ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፦ ውሃ እንደ ሸቀጥ ሊሸጥ የሚገባው ነገር ሳይሆን ለሁሉም ተደራሽ መሆን የሚገባው መሰረታዊ መብት ነው!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ መጋቢት 13/2011 ዓ.ም የተከበረውን ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት በንጹህ የመጠጥ ውኃ ችግር የሚሰቃዩ ሰዎች ሁኔታ ስንመለከት ሊገረሰሱ የማይችሉ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶችን እና የውሃ አስፈላጊነትን አያይዘን እንድንመለክት ያስገድደናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በየአመቱ በመጋቢት 13/2011 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን ዓላማውም የሰው ልጆች በተለይም ደግሞ ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የማኅበርሰብ ክፍሎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የንጹህ ውሃ እጥረት ቀውስ ለዓለም በማሳወቅ ስለሁኔታው ግንዛቤ እንዲፈጠር በማደርግ ችግሩን ከተቻለ ሙሉ በሙሉ ለመፍታት፣ ካልሆነም በከፊል ለመቀረፍ ታስቦ የሚከበር ዓለም አቀፍ ቀን ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ መጋቢት 13/2011 ዓ.ም የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት ጆዜ ግራዚኣኖ ዳ ሲልቫ ቅዱስነታቸው ባሰተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “ውሃ ለስነ-ምህዳር ሚዛን እና ለሰው ልጅ ሕይወት ሕልውና በጣም አስፈላጊ የሆነ እሴት ነው፣ እናም ውሃ እንዳይበከል ወይም ደግሞ በከንቱ እንዳይባክን በዓለም አቀፍ ደረጃ ውሃን መንከባከብ ያስፈልጋል” ብለው በተጨማሪም “ንጹሕ ውሃ ማግኘት መሰረታዊ ከሆነው የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ የተነሳ የሁሉም የሰው ልጆች መሰረታዊ መብት ጋር በተያያዘ መልኩ ንጹህ ውሃን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መትጋት ይገባል” ብለዋል።

በመጋቢት 13/2011 ዓ.ም የተከበረው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን “ማንንም ወደ ኋላ መተው አይገባም” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን መሪ ቃል በድጋሚ በመልእክታቸው በማስተጋባት “የውሃ መዋቅሮችን በመንከባከብ እና ለወደፊቱ በዚህ ዘርፋ ላይ ነዋየ መዋል ፈሰስ በማድረግ የውሃ አጠቃቀምን በማስተካከል እና ለውሃ እንክብካቤን ማድረግ እንዴት እንደ ሚቻል አዲሱን ትውልድ ማስተማርን ያካትታል" ብለዋል።

አዲሱ ትውልድ የውሃ አጠቃቀምን በሚገባ እንዲያውቅ “ውሃ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው እንዲረዳ በማድረግ” እና ውሃን እንዲንከባከብ በማስተማር ውሃን ለሁሉም የሰው ልጆች ተደራሽ ማድረግ እንደ ሚገባ ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን በተለይም ደግሞ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በውሃ እጥረት እየተሰቃዩ የሚገኙትን ሰዎች ችግር ወጣቱ ትውልድ እንዲገነዘበው ማድረግ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ውሃ አጠር የሆኑ አከባቢዎችን የውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ይችላ ዘንድ የሚከናወኑትን ጥረቶች ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በገንዘብ እንዲደግፍ በመልእክታቸው ጥሪ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው “በጣም ጠቃሚ፣ ትሁት፣ ውድ እና ንፁህ የሆነ ውሃ" እኛን እና የወደፊት ትውልድን ለመጥቀም እና ሕልውና ለመስጠት ይዋል” የሚለውን የአዚዚውን የቅዱስ ፍራንቸስኮስን አባባል በመጥቀስ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

22 March 2019, 15:28