ፈልግ

የመጠጥ ውሃ ፍለጋ፣ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ፣ 

ሁለት ቢሊዮን ሰዎችን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት ማጋጠሙ የሚያሳፍር ነው ተባለ።

ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሴቶች ውሃን ለማግኘት ብለው በአማካይ የሰላሳ ደቂቃ መንገድ በእግር እንደሚጓዙ የገለጸው የድርጅቱ ሪፖርት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን እና የመጸዳጃ አገልግሎትን የማያገኙ ከሆነ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚጋለጡ፣ ለተመጣጣኝ ምግብ እጥረት፣ ለትምህርት ዕድል ማነስ እና ለሥራ እጦት የሚጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. የውሃ አቅርቦትን በማስመልከት ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርቱ በዓለማችን ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እንደማያገኙ አስታወቀ።

ከ2002 ዓ. ም. ጀምሮ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ማግኘት ከሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ ሆኖ መጽደቁን ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በዓለማችን ለሁለት ቢሊዮን አንድ መቶ ሚሊዮን ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንደሚጎድል፣ አራት ቢሊዮን ሰዎች ደግሞ ጥራቱን እና ደህንነቱን የጠበቀ የመጸዳጃ አገልግልት እንደሌላቸው ገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ ልማትን ለማምጣት በዘረጋው እቅዱ እስከ 2022 ዓ. ም. ድረስ ለዓለም ሕዝብ በሙሉ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እና ጥራቱን የጠበቀ የመጸዳጃ አገልግሎትን ለማዳረስ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።

የውሃ አቅርቦትን ማሳካት ረጅም ጊዜን ይጠይቃል፣

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በድርጅቱ ከታቀፈው ከትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ጽሕፈት ቤት (ዩኔስኮ) ጋር ሆነው ባዘጋጁት የጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. ሪፖርት እንዳስታወቁት ለዓለማችን ሕዝብ በቂ የውሃ አቅርቦትን ተግባራዊ ለማደረግ ረጅም ጊዜን እንደሚጠይቅ ገልጸው ይህን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ላይ የሚገኙ 32 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፕሮጀክቶች፣ እንደዚሁም 41 ሌሎች ዓለም አቀፍ የግል ድርጅቶች መኖራቸው አስታውቀዋል።

ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ አስፈላጊ የመብት ጉዳይ ነው፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ኦድሪይ አዙሌይ እንደገለጹት ለዓለማችን ሕዝብ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እና ጥራቱን የጠበቀ የመጸዳጃ አገልግሎትን ለማዳረስ ከተፈለገ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የጋራ ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ አስረድተው እስካሁን በሕብረቱ ያልታቀፉ መንግሥታት መኖራቸው ለእቅዱ ተግባራዊነት እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ መጓደል የውሃ ልማትን አደጋ ላይ ጥሎታል፣

በተባበሩት መንግሥታት የእርሻ ልማት ድርጅት (ኢፋድ) በኩል ስጋታቸውን የገለጹት የድርጅቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጂልበርት ሁንግቦ በበኩላቸው፣ የአካባቢ ጥበቃ መጓደል ጠቅላላውን የዓመት የውሃ ልማት ጥይስቄን ወደ 45 በመቶ ከፍ በማድረጉ የተነሳ ወደ 40 ከመቶ ዝቅ ያለው ዓመታዊ የዓለም የምርት መጠን እስከ ጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ. ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ዓለማችን አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ያመለክታል ብለዋል።

አንድ ሚሊዮን ከግማሽ የዓለማችን ሕዝብ ንጹሕ ያልሆነ ውሃን በመጠጣት ለጉዳት ተጋልጧል፣

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሪፖርቱ እንዳስታወቀው በዓለማችን አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ሰዎች ንጹሕ ያልሆነ ውሃን በመጠጣት ሊመጣ በሚችል በሽታ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ፣ ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት መሆናቸውን ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. በኬንያ ዋና ከተማ በናይሮቢ፣ የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ በተደረገው ጉባኤ ላይ አስታውቋል።

አደጋው በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ያጠቃል፣

በቂ የሆነ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መጓደል በደሃ አገሮች የሚገኙ ሕዝቦችን እንደሚጎጋ፣ ከእነዚህም መካከል ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና አዛውንትን፣ በይበልጥም የተፈናቀሉትን እንደሚጎዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ገልጾ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን የማግኘት መብት ከሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ተነጥሎ እንደማይታይ ገልጿል። ሪፖርቱ አክሎም በከተሞች አካባቢ የሚገኙ ደሃ ቤተሰቦች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን በውድ ዋጋ ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጿል።

የአፍሪቃ ሴቶች ውሃን በአቅራቢያቸ አያገኙትም፣

ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ከሚኖር ሕዝብ መካከል ግማሹ ለጤና አስተማማኝ የሆነ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እንደማያገኝ ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ሕዝቦች መካከል 24 ከመቶ ብቻ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እንደሚያገኝ እና 28 ከመቶ የሚሆኑት የቤተሰብ ክፍሎች ደግሞ በጋራ የመጸዳጃ ቤት እንደሚገለገሉ አስታውቋል። ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሴቶች ውሃን ለማግኘት ብለው በአማካይ የሰላሳ ደቂቃ መንገድ በእግር እንደሚጓዙ የገለጸው የድርጅቱ ሪፖርት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን እና የመጸዳጃ አገልግሎትን የማያገኙ ከሆነ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚጋለጡ፣ ለተመጣጣኝ ምግብ እጥረት፣ ለትምህርት ዕድል ማነስ እና ለሥራ እጦት የሚጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ተፈናቃዮች የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፣

በትውልድ አገራቸው የሚፈናቀሉት እና የጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙበት ሁኔታ ለንጹሕ የመጠጥ ውሃ እና ለመጸዳጃ አገልግሎት ምቹ እንዳልሆነ የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት አስታውቆ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ. ም. ወደ 70 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ መገደዳቸውን ገልጿል። በየዓመቱ በአማካይ ከ25 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት እንደሚሰደዱ፣ ይህም ከሃምሳ ዓመታት በፊት ከሚሰደዱት የሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር በእጥፍ መጨመሩን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ውሃን ማግኘት በጦርነት ሆኗል፣

ከ1972 ዓ. ም. ወዲህ የውሃ ፍላጎት በየዓመት በአንድ ከመቶ እንደሚጨምር ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት የውሃ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በአገሮች መካከል ጦርነቶች መካሄዳቸውንም ገልጿል። በዚህም መሠረት ውሃ ይገባኛል በሚል ሰበብ ከ1992 ዓ. ም. እስከ 2001 ዓ. ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ 94 ጦርነቶች መካሄዳቸውን፣ ከ2002 እስከ 2010 ዓ. ም. ድረስ 263 ጦርነቶች መካሄዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ገልጾ ግጭቶቹ በሦስት እጥፍ ማደጋቸውን አስረድቷል።

በውሃ እና በጤና አገልግሎቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ያስፈልጋል፣

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በመጨረሻም በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች መዋዕለ ንዋያቸውን በውሃ እና በጤና አገልግሎት ተሻሽሎ ላይ ማፍሰስ እንደሚገባ ገልጿል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

 

 

20 March 2019, 16:17