ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እውነተኛ ፍቅር ልዩነትን አያስወግድም፣ ነገር ግን አንድነትን ያጠናክራል”

ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በፓናማ በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደ ሆነ መግለጻችን ይታወሳል። ይህንን 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በፓናማ ሐዋርያዊ ጉብኝት እያደርጉ መሆናቸውንም መግለጻችን ይታወሳል። በትላንትናው እለት ማለትም በጥር 17/2011 ዓ.ም በዚያው በፓናማ እርሳቸው በተገኙበት እና እርሳቸው ከወጣቱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ወቅት ቅዱስነታቸው ያደርጉትን የመክፈቻ ንግግር ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የተወደዳችሁ ወጣቶች እንደምን አመሻችሁ!
በዚህን ጊዜ በእንደዚህ ዓይነት ብርሃን እና ሞቅ ባለ ሁኔታ ከእናንተ ጋር በድጋሚ ለመገናኘት በመቻሌ እንዴት መልካም የሆነ ነገር ነው! በፓናማ መሰብሰባችን የዓለም የወጣቶች ቀን ታላቅ የሆነ በዓል መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደስታ እና ተስፋ የሚፈጥር በዓል መሆኑን በዓለም ደረጃ ደግሞ የእምነት ምስክር የሆነ ታላቅ ቀን ወይም በዓል መሆኑን ያሳያል።
በክራኮቪያ ተካሂዶ በነበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ማብቂያ ላይ ብዙ ወጣቶች “በፓናማ በሚካሄደው የወጣቶች ቀን ላይ ይገኛሉ ወይ”? ብለው ጠይቀውኝ ነበር። እናም “እኔ ይህንን አላውቅም፣ እርግጠኛ አይደለሁኝም፣ ነገር ግን በእርግጠኛነት ጴጥሮስ እዚያ ይገኛል” ብዬ መልሼላቸው ነበር። “ጴጥሮስ በዚያው ይገኛል”። ዛሬ የእናንተን እምነት እና ተስፋችሁን ለማክበር እና ለማደስ እነሆ ጴጥሮስ ከእናንተ ጋር እዚህ በመገኘቱ ዛሬ ደስተኛ ነኝ። ዛሬ ጴጥሮስና ቤተ ክርስቲያኑ ከእናንተ ጋር አብረው በመራመድ ላይ ይገኛሉ፣ በዚህም ምክንያት በዚህ አዲስ ኃይል በመሞላት ደስታችሁ እንዲጨምር በሚያደርግ መጽናኛ በመበረታታት እና ይበልጡኑ ተደራሽ በመሆን ጥሩ የቅዱስ ወንጌል መስካሪዎች በመሆን ወደ ፊት ሳትፈሩ በድፍረት መጓዝ ይኖርባችኋል። ወደ ፊት በድፍረት መጓዝ ለዚህ ለዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምስጋና ይግባውና “ቀልብን የሚስብ” እና “አዝናኝ” እናንተ ምን አልባት የምትፈልጉት እና የምታልሙት ዓይነት፣ ከቤተ ክርስቲያን ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ፣ ሌላ ቤተ ክርስቲያን መፍጠር ብቻ ማለት ግን አይደለም። የዚያ ዓይነት አስተሳሰብ ካለ ግን ያ አስተሳሰብ እናንተንም ሆነ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ በኩል የሚናገረውን ነገሮች ሁሉ ክብር ያሳጣዋል ማለት ነው።
ኧረ በጭራሽ እንዲ አይሆንም! ከእናንተ ጋር አብረን በመሆን ሁልጊዜም ለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እራሳችንን እየከፈትን እና ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ በሆነ መልኩ እንድታድግ እና ወጣት ትሆን ዘንድ በመሥራት የጴንጤቆስጤን በዓል በአዲስ መልክ ለመጎናጸፍ እንፈልጋለን። ከዚህ በፊት ተካሂዶ በነበረው ሲኖዶስ ላይ ካገኘነው ልምድ በመነሳት ይህ ነገር ገቢራዊ ሊሆን የሚችለው እኛ ስናዳመጥና ሐሳቦችን ስንጋራ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማገልገል ማዕከል ባደረገ መልኩ ጌታን ማወጅና ጌታን መመስከር እንዲቀጥሉ በማበረታታት እና ተጨባጭ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ሊሆን ይገባል። ይህ “ለታይታ” ብቻ የሚደርግ አገልግሎት ሊሆን ግን በፍጹም አይገባም፣ ነገር ግን በተጨባጭ አገልግሎት ሊገለጽ ይገባዋል።
እዚህ ድረስ መምጣት በጣም ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፣ በእዚህ ቀን ላይ ተካፋይ ለመሆን በማሰብ እዚህ ለመድረስ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደ ከፈላችሁም ይገባኛል። ለብዙ ሳምንታት ያህል በቁርጠኘነት እና በጽናት ሠርታችኋል፣ ጸሎት እና አስተንትኖም አድርጋችኋል። አንድ ደቀ-መዝሙር መሆን ማለት አንድ ቦታ ላይ መድረስ ብቻ ማለት አይደለም፣ ነገር ግን በቆራጥነት የሚሄድ፣ አደገኛ ሁኔታን ለመጋፈጥ የማይፈራ እና ወደ ፊት በጽናት የሚጓዝ ሰው ማለት ነው። እግሮቻችሁን በመንገድ ላይ ካሳረፋችሁ እናንተ ደቀ መዛሙርት ሆናችኋል ማለት ነው። ነገር ግን እዚያው ተገትራችሁ ከቆያችሁ ግን ጠፍታችኋል ማለት ነው። በእግር መጓዝ ጀምሩ፣ መራመድም ቀጥሉ ይህ ለደቀ መዝሙሩ ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ነው። አደጋን ለመጋፈጥ እና ጉዞኋሁን ለመቀጠል አትፍሩ። ዛሬ ይህንን በዓል በደስታ እናከብረዋለን፣ ምክንያቱም ይህንን በዓል ለማክበር ከብዙ ጊዜ በፊት ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት በበርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ ስለተደረገ ነው።

በዚህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ከተለያዩ አገራት፣ የተለያየ ባህል እና ህዝብ የሚወክሉ ባንዲራዎች፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ እና የተለያዩ ልብሶችን የለበሱ ብዙ ወጣቶች ይታያሉ። እያንዳንዱ ሕዝብ የተለየ ታሪክ እና በተለየ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ ነበር። እኛ በብዙ መንግድ የተለያየን ሰዎች ነን! ነገር ግን አንዳችንንም አንዱ ከሌላው ጋር መገናኘት እንዳይችል አላገደም፣ እነዚህ በርካታ ልዩነቶች እኛ አንድ ላይ እንድንሰበሰብ እና አብረን እንዳንሆን አላገደንም፣ አብረን ጊዜ ከማሳለፍ፣ አብረን ከመካፈል፣ ኢየሱስ ክርስቶስን አብረን ከመቀበል አላገደንም። ልዩነታችን ሊያግደን በፍጹም አልቻለም። የዚህ ምክንያት ደግሞ በመካከላችን የሚኖርና አንድ የሚያደርገን አንድ ነገር አለ።
እናንተ ተወዳጅ የሆናችው ወንድሞቼ! እዚህ ድረስ መጥታችሁ እርስ በእርስ ለመገናኘት ብዙ መስዋዕትነትን ከፍላችኋል፣ እናም በዚህ መንገድ እናንተ የመተዋወቅ ባህሪ እውነተኛ አስተማሪዎች እና መስራቾች ሁናችኋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህንን በማድረጋችሁ እናንተ የመገናኘት ባህል ይሰፋ ዘንድ አስተማሪዎች እና ገንቢዎች ሁናችኋል። የመገናኘት ባህል ምንም እንኳን ልዩነቶች ቢኖሩብንም አብረን በፍቅር፣ በአንድነት ተመሳሳይ የሆነውን ጉዞ ወደ ፊት አብረን እንዲንጓዝ ያደርገናል።
በእንቅስቃሴዎቻችሁ እና በአቀራረባችሁ፣ ነገሮችን በምትመለከቱበት መንገድ፣ በፍላጎቶቻችሁ እና ከሁሉም በላይ ከመጠን በላይ የሆነ ችሎታ አለን በሚል መንፈስ፣ እነዚህን ነገሮች በመዝራት መከፋፈል ላይ የሚያተኩር የንግግር ዓይነት፣ እናንተ የምትናገሩትን ዓይነት ንግግር እነሱ የማይቀበሉ ከሆነ "እንደ እኛ" አይደሉም በማለት የክፍፍል መንፈስ እንዲመጣ ያደርጋል። በተለያዩ የአሜሪካ አገራት ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደ ሚሉት “እኛን የሚመስሉ ሰዎች አይደሉም” በማለት እንናገራለን። ይህ ነገር እናንተን አይመጥናችሁም። ምንም እንኳን ሁላችንም የተለያየ ዓይነት ሰዎች ብንሆንም፣ ነገር ግን ሁላችንም አንድ ነን። ይህም የሆነበት ምክንያት ደግሞ “እውነተኛ ፍቅር ትክክለኛውን ልዩነት የማይጥስ ቢሆንም በውስጣቸው ከፍ ያለ አንድነት እንዲፈጠር ስለሚያደርግ ነው”። አሁንም ደግሜ እላችኋለሁ፡ "እውነተኛ ፍቅር ትክክለኛውን ልዩነትን አያስወግድም፣ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ አንድነት እንዲፈጠር ያደርጋል”። ይህን ማን እንደተናገረ ታውቃላችሁ? ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኔደክቶስ 16ኛ ናቸው፣ አሁን እኛን በተሌቪዢን እያዩን ስለሆነ እስቲ አንድ ጊዜ እናጨብጭብላቸው። በሌላ በኩል የውሸት አባት የሆነው ዲያቢሎስ ሁልጊዜ የተከፋፈሉ እና የሚጣሉ ሰዎችን ይመርጣል። እሱ የመከፋፈል መንፈስ ዋና ጌታ እና ጠንሳሽ ነው፣ ነገር ግን አብሮ መስራት የሚፈልጉ ሰዎችን ግን ይፈራል። ይህ ደግሞ ማን ድልድይ እንደ ሚገነባ እና ማን ደግሞ ግንብ እንደ ሚገነባ ሰዎችን ለይቶ የሚያሳዩ መስፈርት ነው። የግንብ ግድግዳ የሚገነቡ ሰዎች ፍርሃትን ይዘራሉ፣ ሰዎች እንዲፈሩ ያደርጋሉ። ነገር ግን እናንተ የድልድይ ገንቢዎች ልትሆኑ ይገባል። ታዲያ እናንተ የምን ገንቢ ለመሆን ነው የምትፈልጉት? “የድልድይ ገንቢዎች!” (በማለት ወጣቶቹ ይመልሳሉ) አዎን አሁን ጥሩ ተምራችኋል ማለት ነው።
እርስ በእርስ መገናኘት ማለት ሙሉ በመሉ መመሳሰል፣ ወይም በተመሳሳይ መልኩ ማሰብ፣ ወይም ደግሞ ተመሳሳይ ነገር መሥራት ማለት እንዳልሆነ እናተ ዛሬ አስተምራችሁናል፣ ያንን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ በቀቀኖች ብቻ ብቻ ናቸው። ግንኙነት መፍጠር ማለት አንድ የተለየ ነገር መሥራት ማወቅ ማለት ነው፣ የግንኙነት ባሕል ውስጥ መግባት ማለት ነው። እያንዳንዳችን የምንጋራቸውን ሕልሞች ሕያው እንዲሆኑ ማድረግ ማለት ነው። እኛ በጣም ብዙ የሆኑ ልዩነቶች አሉን፣ በጣም ብዙ ቋንቋዎችን ነው የምንናገረው። የተለያየ ዓይነት ልብሶችን ነው የምንለብሰው፣ ነገር ግን እባካችሁን አንድ የሆነ ሕልማችንን ለማሳከት እናስብ። ይህንን እውን ማድረግ እንችላለን። ይህ ደግሞ የእኛን ማንነት የሚያጠፋ ነገር ሳይሆን ባሕላችንን የሚያበለጽግ ነው። ታላቅ የሚባል ሕልም ማለት ለሁሉም ሰው ቦታ ያለው ሕልም ማለም ማለት ነው። ኢየሱስ ሕይወቱን በመስቀል ላይ አሳልፎ እንዲሰጥ ያስገደደው ዓይነት ሕልም፣ በጴንጤቆስጤ ቀን በእኛ ላይ የወረደውና እሳቱን በእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ልብ ውስጥ፣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ፣ በእኔ በእናንተ ልብ ውስጥ እንዲቀጣጠል ያደርገው በልባችን ውስጥ ቦታ ያገኘ እና እንድናድግ በሚያደርገን በመንፈስ ቅዱስ ሕልም መሞላት ማለት ነው። ተጨባጭ የሆነ ሕልም፣ በደም ስራችን ውስጥ፣ በልባችን ውስጥ የሚገኘውን “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” (ዮሐ. 13፡34-35) የሚለው ትዕዛዙን በምንሰማበት ወቅት ደስታ እንድናገኝ የሚረዳንን ኢየሱስን ማለም ማለት ነው። የእኛ ሕልም ምን ተብሎ ይጠራል? “ኢየሱስ ክርስቶስ” (በማለት ወጣቶች ይመልሳሉ)።
ከዚህ ምድር የተገኙ ቅዱሳን ይህንን ድምጽ ሰምተው ነበር፣ ከዚህ ምድር የተገኙ ቅዱሳን “ክርስትና ልንከተላቸው የሚገባን ድንቦች ወይም እገዳዎችን የያዘ የእውነቶች ስብስብ ማለት አይደለም። በዚያ መንገድ ክርስትናን ከተመለከትነው ግን ያጠፋናል። ክርስትና እኔን በጣም የሚወደኝ፣ የእኔን ፍቅር የሚፈልግ እና የሚጠይቀኝ ሰው ማለት ነው። ክርስትና ማለት ክርስቶስ ማለት ነው” (ቅዱስ ኦስካር ሮሜሮ፣ እ.አ.አ በታኅሳስ 6/1977 ዓ.ም ካሰሙት ስብከት የተወሰደ)። ሁላችንም በአንድነት እና በጋራ ይህንን ለመድገም እንችላለን ወይ? ወጣቶች እስኪ አንድ ላይ እንዲህ እንበል፡ ክርስትና ማለት ክርስቶስ ማለት ነው! ይህም ማለት እርሱ ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ያስገደደውን የእርሱን ሕልም መከተል ማለት ነው፣ እርሱ በወደደን መጠን እርሱን መውደድ ማለት ነው። እርሱ በግማሽ ወይም እርሱ በጥቂቱ አልነበረም የወደደን። እኛን ሙሉ በሙሉ ይወደናል፣ በፍቅሩ እና በርኅራኄው ሞልቶናል ሕይወቱንም ሰጥቶናል።
ሁላችንም አንድነት እንዲኖረን የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? ለምንድን ነው አንድ የሆነው? እርስ በራስ እንድንገናኝ የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። አንድ የሚያደርገን ነገር ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? እኛ ጥልቅ በሆነ ፍቅር እንደ ተወደድን ዝም ማለት ብንፈልግ እንኳን ዝንም እንዳንል በሚያደርገን፣ በተወደድንበት መጠን እኛም ፍቅር እንድንለግስ እና እንድንወድ ግድ በሚለን እና በሚገዳደረን፣ እርግጠኛ የሆነ ፍቅር በመወደዳችን የተነሳ ነው። ይህንንም እንድናደርግ የሚገፋፋን የክርስቶስ ፍቅር ነው (2ቆሮ 5፡14)።
አያችሁ! ፍቅር አንድነትን በፍፁም የማይከስም እና የማይጫን፣ ሰዎችን የማያገል እና ዝም እንዲሉ የማያደርግ፣ የማያዋረድ ወይም የበላይ ለመሆን የማይፈልግ ፍቅር ነው። የጌታ ፍቅር በየቀኑ ተጨባጭ እና የመከባበር ፍቅር፣ ነጻ የሆነ ፍቅር እና ነጻ የሚያደርግ ፍቅር፣ የሚፈውስ እና ከፍ የሚያደርገን ፍቅር ነው። የጌታ ፍቅር ወደ ታች ከመውረድ ይልቅ ወደ ላይ ከመነሳት ጋር ይበልጡኑ የተገናኘ፣ ከማጽናናት ጋር እንጂ ከመፈራራት ጋር ያለተገናኘ፣ ከማውገዝ ይልቅ አዲስ እንድል የሚሰጠን፣ የወደፊቱን እንጂ የኋላውን የማያይ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር በዝምታ ለማገልገል የሚዘረጋ የፍቅር እጅ ነው፣ ራሱን ለማስተዋወቅ የሚተጋ ፍቅር ዓይነት ግን አይደለም። እንዲሁ በአየር ላይ ተንሳፎ የቀረ ዓይነት ፍቅር አይደለም፣ ነገር ግን በትህትና የተሞላ ራሱን ለሌሎች አስላፎ የሚሰጥ እጁን ለሌልቾ የሚዘረጋ ፍቅር ነው። የዚህ ዓይነቱ ፍቅር ነው ታዲያ ዛሬ ሁላችንንም አንድ ላይ የሰበሰበው።
ወድ ጉዳኞቼ ጌታ ይባርካችሁ! ይህንንም በሙሉ ልቤ ለእናንተ እመኛለሁ። የአንቱጓ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሕይወት ጉዞዋችሁ ሁሉ አብራችሁ ትጓዝ፣ ትጠብቃችሁም፣ በዚህም ምክንያት እኛ ሁላችን ያለምን ፍራቻ እርሷ እንዳለችሁ “እነሆኝ የእግዚኣብሔር አገልጋይ እንዳልከኝ ይሁንልኝ” ለማለት እንችላለን።
አመስገናለሁ

 

26 January 2019, 16:13