ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ ማርያም እግዚአብሔርን እንድናገለግል የተጠራን መሆናችንን ታስታውሰናለች

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 09/2010 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ በዓል በመከበር ላይ ይገኛል።

ይህ የፍልሰታ ማሪያም በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት እና እርሳቸው በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ከስፍራው ለሬዲዮ ቫቲካን ከደረሰው ዜና ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ በእለቱ ስርዓተ አምልኮ በተነበቡት የእግዚኣብሔር ቃላት ላይ ተመርኩዘው ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ማርያም እግዚአብሔርን እንድናገለግል የተጠራን መሆናችንን ታስታውሰናለች” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 09/2010 ዓ.ም የአውሮፓዊያኒን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የፍልሰታ ማሪያም በዓል አስምልክተው ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደምከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቺሁ!

ዛሬ በተከበረው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የፍልሰታ በዓል የእግዚኣብሔር ቅዱስ የሆነ ሕዝብ ለድንግል ማሪያም ያለውን አክብሮት በደስታ ይገልጻል። ይህንንም የምያደርገው በስርዓተ አምልኮ እና እንዲሁም በብዙ የተለያዩ መንፈሳዊ ጉባሄዎችን በማድረግ ይገልጻል፣ በዚህም ምልኩ “ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይለኛል” (ሉቃስ 1፡48) የሚለው የራሷ የማሪያም ትንቢት ተፈጻሚ ይሆናል። ምክንያቱም ጌታ ትሁት የሆነች አገልጋዩን ከፍ ስላደረገ ነው። በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ማረጓ ለእመቢታችን ለቅድስት ድንግል ማሪያም የተሰጠ መልኮታዊ መብት ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት የእግዚኣብሔር ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር በፈጠረችሁ አንድነት ምክንያት ነው። ይህም አካላዊ እና መንፈሳዊ ውዕደት የተፈጠረው መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን ካበሰረበት እለት አንስቶ በእርሷ በማርያም የሕይወት ዘመን ውስጥ ሁሉ በልጇ ምሥጢራዊ ተልዕኮ ውስጥ ካደረገቺው ተሳትፎ ከጎለበተ በኋላ ነው።

በግልጽ እንደ ምታወቀው የእመቤታችን የአኗኗር ሁኔት በእርሷ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሴቶች ያደርጉት የነበረውን ሕይወት በማንጸባረቅ እንደማንኛውም በወቅቱ እንደ ነበሩ ሴቶች ትጸልያለች፣ ቤተሰብ ታስተዳድራለች፣ ቤተ ሙክራብ መሄድ ታዘወትራለች . . .ወዘተ። ነገር ግን በየቀኑ የምታከናውናቸው ተግባሮች እና ድርጊቶች ሁልጊዜ ከእርሱ ከልጇ ከኢየሱስ ጋር ሁለንተናዊ የሆነ አንድንነትን በመፍጠር ነበር የምታከናውነው። እናም ይህ ኅበረት ኢየሱስ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በመመልከት በፍቅር፣ በርኅራኄ እና በልቧ ውስጥ በሚታየው ስቃይ ምክንያት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ እግዚአብሔር ማሪያምን በኢየሱስ ትንሣኤ ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራት ያደርገው በዚሁ ምክንያት ነው። የመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ሥጋ እንደ ልጇ እንዳይፈርስ ተጠብቆ ነበር። በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የሰማነው የመግቢያ ጸሎት እንደ ሚለው “አንተ ሁሉን የምትችል እግዚኣብሔር ሕይወት ሰጪ የሆነውን ጌታ የወለደችውን ሥጋዋ በመቃብር ውስጥ ፈርሶ እንዲቀር አልፈለክም” በማለት የገለጸውም በዚሁ ምክንያት ነው።

ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ስለዚህ ምስጢር እንድናሰላስል ትጋብዘናለች፡ ይህም እግዚአብሔር የመላ ሕዝቡን ነፍሱን  እና ሰውነቱን ሊያድን እንደሚፈልግ ያሳየናል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማሪያም ከወሰደው ሥጋ ጭምር ነው፡ ከዚያም ወደ መለኮታዊነት ከተለወጠው ሰውነቱ ጋር ወደ አባቱ አረገ። የሰው ልጅ የነበረቺው የማሪያም እርገት የእኛን ታላቅ ዕጣ ፈንታ እንድናረጋግጥ ያደርገናል። የግሪክ ፈላስፎች የሰዎች ነፍስ ከሞት በኋላ ደስታን የምታገኝ መሆኑን ቀድመው ተረድተው ነበር። ነገር ግን እነርሱ አካላችንን የነብሳችን እስር ቤት አድረገው ይቆጥሩ ስለነበረ ሰውነትን ይንቁ ነበር - እግዚኣብሔር የሰው ልጅ አከላ በሰማያዊ ደስታ ከነብስ ጋር ሕብረት ፈጥሮ እንዲኖር መፈለጉን ግን አለገባቸውም ነበር። ይህ “በሥጋ ማረግ” የክርስቲያን ግልጸት የሚመለከቱ ዋነኛ የእመንታችን አካል ነው።

ማርያም ወደ ሰማይ ያረገችበት ድንቅ የሆነ ሁኔታ የሰው ልጅ አንድነት እንዳለው በማረጋገጥ እኛ የተጠራነው በነፍስ እና በሥጋ እግዚኣብሔርን ለማገለገል እና ለማክበር እንደ ሆነ ያስታውሰናል። እግዚአብሔርን በሰውነት ብቻ ማገልገል የባሪያ አገልግሎት ይሆናል፣ በነፍሳችንን ብቻ እግዚኣብሔርን ማገልገል ደግሞ ከሰብአዊነታችን ጋር መቃረን ይሆናል። የቤተ ክርስቲያን ታላቅ አባት የነበረው ቅዱስ ኤሬኒዮስ “የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጸው ሕያው በሆነ ሰው ነው፣ የሰው ሕይወትም የምመራው በእግዚአብሔር ራእይ ነው”  ማለቱ ይታወሳል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከኖርን፣ ወደ እግዚአብሔር በምያቀርበው አስደሳች አገልግሎት ውስጥ ወንድሞቻችንን በለጋስነት በምናገለግልበት ወቅት በትንሣኤ ቀን የእኛ ዕድል ከሰማያዊ እናታችን ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ "እግዚአብሔርን በሰውነታችሁ ክብሩት" (1 ቆሮ 6, 20) ብሎ እንደ ሚገስጸን እኛም በዚህ መንገድ እርሱን በሰማይ ለዘላለም  እናከብራለን።

እኛም አንድ ቀን ከሁሉም ቅዱሳን እና ውድ ከሆኑ ወንድሞቻችንን ጋር በገነት መገናኘት እንችል ዘንድ በእየዕለቱ በትጋት በመጓዝ ሕይወታችንን በአግባቡ በእየዕለቱ መኖር እንችል ዘንድ በእናትነት አማላጅነቷ  እንድትረዳን ወደ እርሷ መጸለይ ይኖርብናል።

15 August 2018, 17:49