ፈልግ

በአየርላንድ የኖክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ በአየርላንድ የኖክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ 

የአይርላንድ ምዕመናን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት በናፍቆት በመጠባበቅ ላይ ናቸው

በመጭዉ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወደ አይር ላንድ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ኖክ በተባለ ስፍራ ወደሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ክብረ በዓሏን ይካፈላሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጭዉ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወደ አይር ላንድ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ኖክ በተባለ ስፍራ ወደሚገኘው የእመ ቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ክብረ በዓሏን እንደሚካፈሉ ታውቋል። ይህ በእመቤታችን ስም የታነጸው ቤተ ክርስቲያን በሃገሪቱ ከሚገኙ ታላላቅ የንግደት ሥፍራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ዘንድሮ በአይር ላንድ መዲና በሆነችው ዳብሊን ከተማ፣ እምነትና ቤተ ሰብ በሚል አርዕስት ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ እንደሚካሄድ ይታወቃል።

በአይር ላንድ ኖክ በተባለ ሥፍራ፣ ከባድ ዝናብ እየዘነበ ባለበት ሰዓት ነሐሴ 16 ቀን 1871 ዓ. ም. የቁምስና ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ለነበሩ፣ እድሜአቸው ከ6-75 ዓመት ለሚሆናቸው 15 ሰዎች፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደተገለጸችላቸው ይታወቃል። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋርም ቅዱስ ዮሴፍ እና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ አብረዋት መታየታቸው ይታመናል። በስፍራው 15 ሰዎች ሜዳ ላይ ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ ለሁለት ሰዓት ያህል ይዘንብ የነበረው ዝናብ ምንም እንዳልነካቸው ተመልክቷል።

 

የቤተሰብ ጉባኤ ከ25 ዓመታት ወዲህ ሲደረግ የቆየ የቤተ ክርስቲያን ስጦታ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ ተዓምር በሁለት ሳምንታት ውስጥ በመላው አይር ላንድ በመሰማቱ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሁኔታውን የሚያረጋግጥ ምክር እንዳቋቋሙ ይነገራል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ፣ በ1971 ዓ. ም. ወደ አይር ላንድ፣ ኖክ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድረገው እንደነበር እና በዕለቱ በስፍራው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ የአይር ላንድ ሕዝብና ከሌሎችም የዓለም ክፍሎች ወደ ኖክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል። አስቀድሞም በነሐሴ ወር 1932 ዓ. ም. በቤተ ክርስቲያኗ ለዓለም ሰላም ተብሎ በተደረገው የጸሎት ስነ ስርዓት 50 ሺህ የአይር ላንድ ምዕመናን ተገኝተው እንደነበር ያውቋል። በ1946 ዓ. ም. በተከበረው የአንድ ዓመት ሙሉ የቅድስት ማርያም ዓመት ቤተ ክርስቲያኗ የመንፈሳዊ ንግደት ስፍራ እንድትሆነ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በይፋ ማወጃቸው ይታወቃል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለ15 ሰዎች ከተገለጸችላቸው ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ፣ በስፍራው ለሚታነጸው ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ድንጋይ በመባረክ በ1965 ዓ. ም. ብጹዕ ጳውሎስ 6ኛ ማስቀመጣቸው ሲታወስ ከ6 ዓመታት በኋላ በሐምሌ 11 ቀን 1971 ዓ. ም. የቤተ ክርስቲያኑ ግንባት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በ1971 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ አይር ላንድ፣ ኖክ ከተማ ሄደው ባሰሙት ንግግር፣ አንድ ሰው ወደ አይር ላንድ አገር፣ የኖክ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ንግደት በሚያደርግበትጊዜ  በቤተ  ክርስቲያኑ ውስጥ ከሌሎች መንፈሳዊ ተጓዦች ጋር በተገናኘ ቁጥር እምነቱን በማደስ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገኘውን የድነት ጸጋን ይቀበላል ማለታቸው ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ በአይር ላንድ ዋና ከተማ በሆነችው በዳብሊን ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት እንደሚቀሩ ይታወቃል። ይህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚገኙበት ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውጤት በመሆኑ፣ ለቤተ ሰብ የሚሰጠው ትኩረትና የሚደረግለት ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል። በሰሜን አሜርካ በፊላደልፊያ የተደረገው ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ፣ በ2006 ዓ. ም. ከተደረገው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኋላ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና መርህ ቃልም “በዘመናችን የቤተ ሰብ ተልዕኮና ጥሪ” የሚል እንደ ነበር ይታወሳል። በቅርቡ በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ሊካሄድ የታቀደው የቤተሰብ ጉባኤም “የፍቅር ሐሴት” የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት የመላው ዓለም ቤተ ሰብ በሕብረት ሆነው በመመልከት የሚያጎለብቱበት አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።        

14 August 2018, 09:00