ፈልግ

ወይዘሪት አጋታ ሊዲያ ናታኒያ፥ ወይዘሪት አጋታ ሊዲያ ናታኒያ፥  

“የሀገረ ስብከት የወጣቶች ቀን ወጣቶች የኢየሱስን ታላቅነት የሚገልጹበት ዕድል ነው”

በቫቲካን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ጽሕፈት ቤት አባል ወይዘሪት አጋታ ሊዲያ ናታኒያ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ የተከበረውን የሀገረ ስብከት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰቢያን መሠረት በማድረግ ባደረገችው ውይይት፥ “ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን የዘወትር መታመኛችን እግዚአብሔር ነው” በማለት ተናግራለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ ለተከበረው ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከቶች የወጣቶች ቀን መሪ ርዕሥ፥ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” የሚል እንደ ነበር ይታወሳል። እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. ከተከበረው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ጋር ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከት ወጣቶች ቀንም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። 

በቫቲካን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ አካል አባል የሆነችው ወይዘሪት አጋታ ሊዲያ ናታኒያ፥ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፥ ስለ ክብረ በዓሉ አስፈላጊነት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተስፋ መልዕክት በማስመልከት ሃሳቧን ገልጻለች።


ተስፋ እንድናደርግ ተጠርተናል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዘንድሮው የሀገረ ስብከት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያስተላለፉት መልዕክት “እጅግ ጠቃሚ ነው” ያለችው ወዘሪት ናታኒያ፥ “በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖርን ያለነው እንደ ወጣቶች በተስፋ በማመን አይደለም” ስትል ተናግራ፥ “ቅዱስነታቸው በዚህ የተስፋ መልዕክታቸው፥ ወጣቶች ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥማቸው እና የትም ቢሄዱ እግዚአብሔር የዘወትር መታመኛቸው እንደንደሆነ ለማስረዳት ፈልገዋል” በማለት ተናግራ፥ የሀገረ ስብከት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን እና የክርስቶስ ንጉሥ በዓል አንድ ላይ መከበሩ “የክርስቶስን ታላቅነት በራሳችን መንገድ እንዴት መግለጽ እንደምንችል ለማሰላሰል ዕድል የሰጠ ነው” ብላለች ።

ለዚህም እንደማሳያ በለንደን ለብዙ ዓመታት የኖረችው ኢንዶኔዥያዊት ወጣት ወይዘሪት ናታኒያ፣ በተለያዩ ባሕሎች ውስጥ የራሷን ተስፋ ለማሰራጨት ያደረገችውን ሙከራ ገልጻለች። “ስድስት ሃይማኖቶች ስላሏት የኢንዶኔዢያ ውበት በአውሮፓ ውስጥ ለሚገኙ ጓደኞቼ መናገር እወዳለሁ” ያለችው ወይዘሪት ናታኒያ፥ "በእውነተኛ ተስፋ በማመን በእርግጥ አብረን መኖር እንችላለን" ብላለች።

በቫቲካን ውስጥ ወጣት ድምፅ

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2018 ዓ. ም. በቫቲካን የተካሄደውን የወጣቶች ሲኖዶስ ተከትሎ የተቋቋመ መሆኑን የተናገረችው ወይዘሪት ናታኒያ፥ ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመው፥ በሲኖዶሱ የመጨረሻ ሠነድ ውስጥ፥ “ከተለያዩ ቦታዎች እና አስተዳደጎች የተውጣጡ ወጣቶችን የሚወክሉ የምክክር ቡድን አባላት” የሚል ጥሪ ካቀረበ በኋላ እንደ ነበር ተናግራለች።

ዋና ግቡ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንዳላቸው እና እንደሚሰማቸው ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጻለች። ምንም እንኳን በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኝ ቢሆንም፥ ከሌሎች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጋር ለመገናኘት ዝግጁ እንደሆነ፥ በተለይም ከቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ርዕሥ ላይ ተከታታይ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ወ/ሮ ናታኒያ ጠቅሳለች።

ከዚህም በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ላይ በተደረገው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ መጠየቃቸውንም ገልጻ፥ ምንም እንኳን የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ አካል የስልጣን ጊዜ በቅርቡ የሚያበቃ ቢሆንም፥ “እኛ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች ሁሉ ጋር መጓዝ እንደምንችል እና ድምፃችን በእውነት እንዲሰማ ማድረግ የቻልንበት ነው” ስትል ወይዘሪት ናታኒያ ተናግራለች።

 

28 November 2023, 16:41