ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በተከበረው 37ኛው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በተከበረው 37ኛው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ተስፋ የሌለበት በሚመስል ዓለም ውስጥ ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሀገረ ስብከት ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያዘጋጁትን መልዕክት ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ይህ የምንገኝበት ጊዜ የተስፋ ጊዜ መሆኑን አስታውሰው፥ ይህን ተስፋ ችግር እና መከራ በበዛበት ዓለም ውስጥ እንዴት ማስቀጠል እንደሚችል ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ለ38ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያዘጋጁትን መልዕክት ማክሰኞ ኅዳር 4/2016 ዓ. ም. ይፋ አድርገዋል።

“በተስፋ ደስ ይበላችሁ!” በሚል ርዕሥ በጻፉት መልዕክታቸው፥ ክርስቲያናዊ ተስፋ እግዚአብሔር በመካከላችን መኖሩን እንድናውቅ የሚያደርገን እንደሆነ ገልጸው፥ ይህንን አዎንታዊ አመለካከት ጨለማ በበዛበት ዓለም ውስጥ ጠብቆ ለማቆየት እና ለመጋራት የሚያግዙ ስልቶችንም ጠቁመዋል።

ተስፋ ቢስነት

"በተስፋ ደስ ይበላችሁ!" የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከት ወጣቶች ቀን መልዕክት ጭብጥ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች ከጻፈው መልዕክት የተወሰደ ሲሆን፥ በሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት፥ “ወጣትነት በተስፋ እና በህልም የተሞላ፣ ሕይወትን በሚያበለጽጉ በርካታ ውብ ነገሮች እነርሱም፥ በእግዚአብሔር የፍጥረት ግርማ፣ በጓደኝነት፣ ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እና በሌሎች በርካታ መልካም ነገሮች የተሞላ ነው” ብለዋል።

ሆኖም የምንኖረው ዓለም፥ ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተስፋ የሌለበት በሚመስል የችግር እና የጦርነት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ተናግረው፥ ብዙዎችም የፀሐይ ብርሃን በማይገባበት ጨለማ ቤት ውስጥ እንዳሉ ሆኖ ይሰማቸዋል ብለዋል።

በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ደስታ እና ተስፋ እንዴት አድርገን ልንለማመድ እንችላለን? ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ በተለይም በንጹሃን ላይ የሚደርስ ስቃይ ስናስብ እኛም ዘማሪው ዳዊት የዘመራቸውን አንዳንድ መዝሙሮች በመድገም እግዚአብሔርን፥ “ለምን ሆነ?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን ብለዋል።

ወደ ተስፋ የሚወስዱ መንገዶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ጊዜ ክርስቲያናዊ ተስፋን ለመያዝ የሚረዱ ሁለት ዘዴችን ጠቁመዋል። የመጀመሪያው፥ ተስፋ የእኛ ጥረት፣ ዕቅድ ወይም ችሎታ እንዳልሆነ መገንዘብ ነው ብለው፥ ይልቁንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገናኘት የሚወለድ እንደሆነ እና ክርስቲያናዊ ደስታ እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር ከማወቅ የሚገኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ክርስቲያናዊ ተስፋ በፍቅር እና በእምነት ላይ የተመሠረተ እንጂ የሚናቅ እንዳልሆነ ተናግረው፥ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይተወን እና ለቃል ኪዳኑ ታማኝ ሆኖ ስለ መቆየቱ እርግጠኞች የሚንሆንበት እንደሆነ ገልጸው፥ “በሞት ጥላ ሸለቆ እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” (መዝ. 23:4) የሚለውን ጠቅሰዋል።

ሁለተኛው፥ በሥቃይ ውስጥ ሆነን ተስፋ የምናደርግበት እና እግዚአብሔር ለችግራችን የሚሰጠው መልስ አካል መሆን እንደምንችል መገንዘብ ነው ብለዋል። በእርሱ አምሳል የተፈጠረን እኛ፣ ተስፋ ቢስ በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ ስንገኝ እንኳን የፍቅሩ ምልክቶች ልንሆን እንችላለን ብለዋል።

ተስፋን ሲጋሩት ያድጋል

“ይህን ደስታ እና ተስፋ ከእግዚአብሔር ከተቀበልን በኋላ የግላችን ልናደርገው አንችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶች በውስጣቸው የተቀጣጠለውን የደስታ እና የተስፋ ብርሃን ማሳደግ እና ከሌሎች ጋርም መጋራት እንዳለባቸው አሳስበው፥ ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ይበልጥ እንደሚያድጉ ተናግረዋል።

በተለይም ተስፋ ከማጣት የተነሳ በውጭ ሲታዩ ደስተኞች የሚመስሉ ነገር ግን በውስጣቸው ከሚያለቅሱ ጓደኞቻቸው ጋር ወጣቶች በቅርብ እንዲገናኙ አደራ ብለው፥ በግዴለሽነት እና በግለኝነት ባሕል እንዳይበከሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያናዊ ተስፋ እንደ መልካም ስሜት ለሁሉ ሰው እንዲሆን የታሰበ በመሆኑ የግላችን ልናደርገው አንችልም ሲሉ፥ በሀገረ ስብከት ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያዘጋጁትን መልዕክት ደምድመዋል።

 

 

16 November 2023, 12:10