ፈልግ

በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠር ተገምቷል። በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠር ተገምቷል።  (ANSA)

ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮሚሽን በስደተኞች ላይ በደረሰው የመርከብ አደጋ የተሰማውን ሐዘን ገለፀ

ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮሚሽን (አይሲኤምሲ) በግሪክ ሰኔ 7/2015 ዓ. ም. በስደተኞች ላይ በደረሰው አሰቃቂ የመርከብ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፥ መንግሥታት የተቸገሩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግሪክ ምዕራባዊ ፔሎፖኔዝ የባሕር ዳርቻ ላይ ረቡዕ ሰኔ 7/2015 ዓ. ም. በደረሰ የመርከብ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠር ተገምቷል። ከአቅም በላይ በመጫኑ ምክንያት በሰጠመ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ላይ ከ400 እስከ 750 የሚደርሱ ስደተኞች ተሳፍረው እንደ ነበር ተነግሯል።

ለአደጋው ምላሽ የሰጡት የዓለም አቀፉ ካቶሊካዊ የስደተኞች ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሞንሲኞር ሮበርት ቪቲሎ፥ በደረሰው አሰቃቂ የሕይወት መጥፋት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ “ይህን የመሳሰሉ  አሳዛኝ ሁኔታዎችን በዓለም ዙሪያ ሲከሰት ዓለም በዝምታ መመልከት የለበትም” ብለዋል።

በስደተኞቹ ላይ የደረሰው አደጋ በጦርነት እና በግጭት ስቃይ እንዲሁም መሠረታዊ ፍላጎቶችን ባለማግኘታቸው የተነሳ አገራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለሚሰደዱ ሰዎች ፍትሃዊ እና አስተማማኝ አማራጮች ሊኖር እንደሚገባ ሞንሲኞር ሮበርት ተናግረዋል። “ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ አስፈላጊውን ከለላ መስጠት፣ ማበረታታት እና ከማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይገባል" በማለት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መናገራቸውን ያስታወሱት ሞንሲኞር ሮበርት አክለውም፥ ይህም በእግዚአብሔር ፀጋ በመታገዝ ሕይወትን ለማዳን፣ ተስፋን ለመስጠት እና በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ማኅበረሰቦችን እና ወንድማማችነትን ሊያጠናክር እንደሚችል ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ካቶሊካዊ የስደተኞች ኮሚሽን “ICMC” የስደት አማራጭ መንገዶችን በማስተዋወቅ፣ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ዕርዳታን ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ ሞንሲኞር ሮበርት ተናግረው፥ “ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በብዙ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ አስተዋጽዖን እንደሚያበረክቱ እናያለን” ብለው፥ በመሆኑም የተቸገሩ ወንድሞችን እና እህቶችን በደስታ ልንቀበላቸው ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የስደተኞች ኮሚሽን በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ስደተኞች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዕርዳታን የሚያስተባብር ካቶሊክ ኤጀንሲ መሆኑ ይታወቃል።

 

19 June 2023, 15:13