ፈልግ

ዶናልድ ትራምፕ  ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ቅዱስ ሥፍራ በጎበኙበት ወቅት፤  ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ቅዱስ ሥፍራ በጎበኙበት ወቅት፤  

ዶናልድ ትራምፕ በቅ. ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ስም ወደሚጠራ ቅዱስ ሥፍራ ያደረጉት ጉብኝት ወቀሳን ማስከተሉ ተነገረ።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ግንቦት 25/2012 ዓ. ም. በዋሽንግተን ከተማ ውስጥ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስም ወደሚጠራ ብሔራዊ የንግደት ሥፍራ ያደረጉት ጉብኝት ወቀሳን ማስከተሉ ተገለጸ።

የቫቲካን ዜና፤

የዋሽንግተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዊልተን ግሬጎሪ እንዳስረዱት፣ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በከተማው ወደሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካቶሊካዊ የንግደት ሥፍራ ያደረጉት ጉብኝት  የሚኒያፖሊስ ግዛት ነዋሪ በነበረው በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ምክንያት በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ ለማዛባት አልመው ያደረጉት መሆኑን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዊልተን ግሬጎሪ ከፕሬዚደንት ትራምፕ ጉብኝት ቀደም ብለው ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ ፕሬዚደንት ትራምፕ ወደ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሥፍራ ያደረጉት ጉብኝት የቤተክርስቲያኒቱን የእምነት መርሆችን የሚጥስ፣ የአቋም ልዩነት ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ የሁሉንም ሰው መብት የማስጠበቅ ተልዕኮዋን የሚቃረን ነው ብለው፣ እነዚህን መንፈሳዊ ሥፍራዎች አግባብነት ለሌለው ዓላማ መጠቀሚያ ማድረግ በጣም ግራ የሚያጋባ እና የሚያስቀይም ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብሔራዊ የንግደት ሥፍራ ያደረጉት ጉብኝት በአጠገቡ ከሚገኘው የአሜሪካ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ለሰልፍ ከወጡ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ዘንድም ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ ታውቋል። ሰልፈኞቹም በበኩላቸው “ቤተክርስቲያናችን በፎቶ ግራፍ ማታለያ አይደለም” ፣ “ለጥቁሮች ሕይወት ክብር ይሰጥ” ሲሉ ተሰምተዋል። ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብሔራዊ የንግደት ሥፍራ አስተዳደር በመልዕክቱ፣ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝ ዓላማ በዓለም አቀፉ የሃይማኖት ነፃነት አፈጻጸም ትእዛዝ ላይ እንዲፈርሙበት ከዋይት ሀውስ ቀጠሮ በተያዘለት መሠረት መሆኑን አስታውቋል።

የዋሽንግተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዊልተን ግሬጎሪ በንግግራቸው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሰውን ልጆች መብት እና ክብር በማስጠበቅ እና በመከላከል ጠንከር ያለ አቋም የነበራቸው መሆኑን  አስረድተው፣ የእርሳቸው  ቅርስ ይህን እውነት በግልጽ ይመሰክራል ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዊልተን ግሬጎሪ፣ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሌላ ሥፍራ ወደሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ እንደተናገሩት፣ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አቋም ቢሆን ኖሮ፣ በአምልኮ እና በሰላማዊ ሥፍራ ፊት ለፊት ፎቶ ግራፍ ለመነሳት ሲባል ለነጻነታቸው ሲሉ ድምጻቸውን የሚያሰሙት ሰዎችን ዝም ለማሰኘት በእንባ አስመጭ ጋዝን እና በጦር መሣሪያዎች ማስፈራራት አይፈቅድም ነበር ብለዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ያደረጉት ጉብኝት በቤተክርስቲያኗ አስተዳደር እና ምዕመናን በኩል ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ ታውቋል።

ባሁኑ ጊዜ በበርካታ የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ለተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ ምክንያቱ፣ የሚኒያፖሊስ ግዛት ነዋሪ የነበረው ጆርጅ ፍሎይድ፣ ከሱቅ ለገዛው ዕቃ የሐሰት ባለ 20 ዶላር ኖት ከፍሏል ተብሎ በመጠርጠር በፖሊሶች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መሬት ላይ ደፍተውት፣ ከፖሊሶቹ መካከል አንዱ ለ9 ደቂቃ ያህል አንገቱ ላይ በጉልበቱ ቆሞበት ትንፋሽ በመከልከል አፍኖት ለሞት እንዲበቃ በማድረጉ እንደሆነ ይታወቃል።

05 June 2020, 09:50