ፈልግ

ሟቹን ጆርጅ ፍሎይ በጸሎት ሲያስታውሱት፤ ሟቹን ጆርጅ ፍሎይ በጸሎት ሲያስታውሱት፤  

ካርዲናል ታርክሰን፣ በሰሜን አሜሪካ ፍትህ፣ በሕዝቡ ዘንድ ይቅርታ እንዲደረግ ጠየቁ።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ የአፍሮ-አሜሪካዊ ወጣት ጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ በሰሜን አሜሪካ የተቀሰቀሰውን ጸረ ዘረኛ አመጽ በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ በአገሪቱ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ሕዝቡም ይቅርታ እንዲደራረግ ጠይቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የሚኒያፖሊስ ግዛት ነዋሪ የነበረው ጆርጅ ፍሎይድ፣ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ. ም. ከአንድ ሱቅ ለገዛው ዕቃ የሐሰት ባለ 20 ዶላር ኖት ከፍሏል ተብሎ በመጠርጠር በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል። የቪዲዮ ምስል ማስረጃ እንደሚያረጋግጠው ከአራቱ ፖሊሶቹ መካከል አንዱ መሬት ላይ ተደፍቶ በሚገኝ ተጠርጣሪ አንገት ላይ ለ9 ደቂቃ ያህል በጉልበቱ ቆሞበት ትንፋሽ ከልክሎት ለሞት እንዲበቃ ማድረጉ ይታወሳል። ከድርጊቱ ማግሥት አራቱም ፖሊሶች በነፍስ ግድያ ወንጀል ከሥራ ገበታቸው መወገዳቸው ታውቋል።  በዚህ አሰቃቂ የአፍሮ-አሜሪካዊ ወጣት ግድያ ምክንያት ቢያንስ በ14ቱ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የሕዝብ አመጽ መቀስቀሱ ታውቋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ የአፍሮ-አሜሪካዊ ወጣት፣ የጆርጅ ፍሎይድ ግድያን በማስመልከት ለቫቲካን ሚዲያ እንደተናገሩት፣ ግድያው ከዘረኝነት ተግባር በላይ ነው ብለው፣ ይህን የመሰለ ተግባር በሰሜን አሜሪካ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች፣ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ሥርዓት ይፈጸመ እንደ ነበር፣ በእስያ እና አውስትራሊያ ውስጥ በነባር ማኅበረሰብ ላይ ይፈጸም እንደ ነበር መሆኑን ገልጸው፣ የዘረኝነት ተግባር በዓለማችን በሰፊው የተሰራጨ ማህበራዊ ክስተት መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ንግግራቸው በመቀጠል ይህን ማህበራዊ ክስተት በቤተክርስቲያናችን ዓይን የተመለከትን እንደሆነ፣ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የተሰጠውን መሠረታዊ ነጻነት የሚጻረር ነው ብለዋል። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን፣ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ውድ ሰብዓዊ ክብር የተላበሰ መሆኑን አስረድተው፣ የሚጠበቅብንም ይህን ክብር ለሰው ልጅ መስጠት፣ መንከባከብ እና ማሳደግ መቻል ነው ብለዋል።

ሰብዓዊ ክብርን መቃወም፣ ማጉደል ወይም የማስወገድ ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት እጅግ አሳሳቢ እንደሚሆን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የሎሳንጀለስ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ በጳጳሳቱ ጉባኤው ስም ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ እንደተናገሩት፣ በሰሜን አሜሪካ እየተካሄደ ያለው የሕዝብ አመጽ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ብሶት መግለጽ ህጋዊ እና ትክክለኛ እንደሆነ፣ በቆዳ ቀለም ልዩነት ብቻ ውርደት ሲያጋጥማቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በንግግራቸው፣ የቤተክርስቲያን አባል እንደመሆናችን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን  ሁላችን የሰው ልጅ ክብር እንዲረጋገጥ እንፈልጋለን ብለዋል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከፈጠረ በኋላ ሁለት ትክክል ያልሆኑ ነገሮች መከናወናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛቸዋልን ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የመጀመሪያው ለእግዚአብሔር ቃል አለ መታዘዝ ሲሆን ሁለተኛው ወንድምን መግደል እንደሆነ አስረድተው፣ በሰው ልጅ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው አመጽ ወንድምን መግደል ነው ብለዋል። ዘረኝነት፣ በልዩነት መካከል ያለውን ውበት ማሳደግ ሲገባን ክፍፍልን ስንፈጥር የሚመጣ ጎጂ የሆነ ማኅበራዊ ክስተት መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ሁሉም የልዩነት ዓይነቶች በሰው ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ነፍስን ማጥፋት ስብዕናችንን እና ቤተሰባዊ አንድነታችንን ከማሳነሱ በላይ ለፍትህ ፍለጋ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ድምጻችንን እንድናሰማ ስለሚያነሳሳን ለፍትህ መቆም መልካም መሆኑን አስረድተዋል። ፍትህ በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚጠግን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ለፍትህ መቆም የሰዎችን ግንኙነት ያሳድጋል ወይም ይገነባል ብለዋል። ለፍትህ መጮህ ወንድማዊ ግንኙነቶችን የሚጎዱ ማኅበራዊ ክስተቶችን መቃወም እንደሆነ ካርዲናል ታርክሰን አስረድተዋል።

“ዘረኝነት ወደ በርካታ የዓለማችን ክፍሎች ዘልቆ የገባ ማኅበራዊ ችግር ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ፣ የዘረኝነት መነሻን ለማወቅ የሰው ልጅ ስብዕና ትክክለኛ ትርጉም እና ቤተሰባዊ አንድነት ምን ማለት እንደሆነ መማርን ይጠይቃል ብለዋል። ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ተመሳሳይ ሰብዓዊ ክብርን እንደምንጋራ ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የተፈጠርነው በእርሱ አምሳያነት ነው ብለዋል። ቤተክርስቲያን ለጆርጅ ፍሎይድ ወንድም የተለየ እርዳታ ባትሰጠውም በአቋሙ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲጓዝ ድምጿን ታሰማለች ብለዋል። በሰሜን አሜሪካ ሕዝቡ ብሶቱን እና ድምጹን አመጽ ሳያካሄድ በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጽ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታሳስባለች ብለዋል። በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በርካታ አመጽ ያልታዩባቸው ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸውን አስታውሰው ከእነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል ብዙዎቹን የመብት እና ነጻነት ተሟጋች የነበሩት ማርቲን ሉተር ኪንግ የመሯቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በንግግራቸው “የሟቹን የጆርጅ ፍሎይድ የክርስትና ሕይወት ጥንካሬ ባላውቅም፣ ሕዝቡ ድምጹን በሰላማዊ መንገድ ከመግለጽ በተጨማሪ ለይቅርታ እና ለሰላም የተዘጋጀ እንዲሆን ያስፈልጋል” ብለዋል። የሰሜን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት እና የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በኅብረት በመቆም፣ ድምጻቸውን ለማሰባሰብ እና አብረው ለመጸለይ የሚያግዝ፣ አንድነታቸውንም የሚያጠናክር የጋራ መድረክ አዘጋጅተ እንዲገናኙ ሃሳባቸውን አቅርበው፣ ሟቹ ጆርጅ ፍሎይድ ባሁኑ ጊዜ የሚጠይቀን የጸሎት እርዳታን እንደሆነ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትገነዘባለች ብለዋል። የጋራ ጸሎት መድረክ መዘጋጀቱ፣ ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ እና ከወጣው ቁስል በክርስቲያናዊ መንገድ ለመፈወስ ያግዛል ብለዋል።         

04 June 2020, 18:25