ፈልግ

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት 

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ

ክፍል አስራ አምስት

ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ለምን ጣልቃ ትገባለች ቢባል መልሱ አንድ እና አንድ ነው፣ የአንድ ማሕበረሰብ ማዕከል ያው የሰው ልጅ ራሱ በመሆኑ ነው። ማኅበረሰብ ስንል በተደራጀ ሁኔታ በጋራ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህም በእዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ የጋራ ተግባሮች እና ሥራዎች እንዴት መከናወን እንደ ሚገባቸው በመወሰን የሥራ ክፍፍል በማድረግ የተለያዩ ማኅበራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት፣ ሰዎች በጋራ የሚሳተፉበት፣ የሰዎች ስብስብ የሚለውን ያሰማል። በተጨማሪም በአንድ አገር ውስጥ ወይም በአጠቃላይ በሌላ አገራት የሚኖሩ  ሰዎች ሁሉ ማህበረሰብ ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። በአጠቃላይ ሰዎች በጋራ የሚኖሩበት ሥፍራ እንደ ሆነም ያሳያል (Cambridge online dictionary፡ 2018፡ retrieved 02/02/2018 ይህ ትርጉም ከካብሪጂ መዝገበ ቃል የተወሰደ ነው።)

በአጠቃላይ ማኅበረሳባዊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያመለክት ነው። በዚሁ መሰረት ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ በተከታታይ የምትሰጥበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ማከርኩት “የሰው ልጆችን ማዕከል” ባደርገ መልኩ ነው። የሰው ልጆች ባሉበት ማኅበረሰብ አለ፣ ማኅበረሰብ ባለበት ደግሞ እመንት አለ፣ እምነት ባለበት ቦታ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን አለች፣ ቤተ ክርስቲያን እና ማኅበረሰብ ባሉበት ደግሞ መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮች ይንጸባረቃሉ፣ ቤተክርስቲያን ስነ-ምግባራዊ የሆኑ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ፣ ሰዎች በስላም እና በመከባበር እንዲኖሩ መልካም የሆኑ ነገሮችን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ እሴቶችን በማበረታታት በአተቃራኒው ደግሞ የማኅበርሰቡን ሰላም የሚነሳውን ክፉ ነገሮችን በብርቱ ትቃወማለች፣ እንዳይስፋፉም በወንጌል እና ሰብዓዊ ምርሆች ላይ የተመሰረቱ አስተምህሮችን ትሰጣለች።

የሰው ልጆች ተሰብስበው በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ማኅበራዊ ግጭቶች ኢፍታዊ ተግባሮች፣ የመብት ጥሰት እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ክስተቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ልፈጠሩ ይችሉ ይሆናል፣ ተፍጥሮአዊ ክስተት ነው፣ እየተከሰተም ይገኛል።

በማንኛውም ምክንያት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ተገቢ ያልሆኑ ግጭቶች የሕብረተሰቡን ሰላም በማወክ፣ በተለይም ደግሞ ሕጻናት፣ ሴቶችን እና አዛውንቶችን አደጋ ላይ በመጣል ማኅበራዊ ኑሮን አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የሕዝቡን ሰላም በማወክ የእግዚኢኣብሔር ስጦታ የሆነ የሰው ልጆች ነፍስ እንደ ዋዛ እንዲጠፋ የሚያደርግ ክስተት ሊያስከትል ይችል፣ እያስከተለም እንደ ሚገኝ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በቀላሉ ገምግሞ ለመረዳት ይቻላል። በእዚህም ምክንያት የተነሳ ቤተክርስቲያን የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነ የሰው ልጆች ክቡር የሆነ ነፍስ እንደ ዋዛ እናድይቀጠፍ፣ የግጭቶች ሁሉ መንስሄ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን ነቅሳ በማውጣት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ውይይት እንዲደርግ፣ ለችግሮች ሁሉ ሰላማዊ የሆነ ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመወያየት ባሕልን ባማከለ መልኩ ችግሮች እና አለማግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ የበኩላን ማኅበራዊ አስተዋጾ ማድርግ ሰለሚኖርባት በእዚህ አግባብ በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በትኩረት ትሳተፋለች። ይህ ሲባል ግን “ቤተክርስቲያን በማኅበረሰቡ ውስጥ ላሉት የህይወት ጉዳዮች ሁሉ ኃላፊነት አትወስዳለች ማለት አይድም ፣ ነገር ግን ያላትን ችሎታ ተጠቅማ ትናገራለች ፣ ይህም አዳኝ የሆነውን ክርስቶስን ማወጅ ነው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2420)።

በተመሳሳይ መልኩ ቤተክርስቲያን በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ሙያዊ ትንታኔ የመስጠት ሕጋዊ የሆነ መብት ባይኖራትም ነገር ግን በተቃራኒው በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት የሚጎዳው የሰው ልጅ መሆኑን አጥብቃ ስለምትረዳ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሳትፎ ታደርጋለች። ምክንያቱም ፍታዊ የሐብት ክፍፍል በአንድ ሀገር ውስጥ የሌለ ከሆነ፣ መሰረታዊ የሚባሉ ተቋማት የማይሟሉ ከሆነ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ያው የማኅበረሰብ ክፍሉ ነው፣ በተለይም ደግሞ ድኽ እና አቅመደካም የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል የእዚህ ጥቃት ሰለባ ይሆናል። በተመሳሳይ መልኩም በአንድ ሀገር የፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ በሚከሰተው ሙስና፣ ሕዝብን ያላማከለ ውሳኔ፣ ስነ-ምግባርን የሚጣረዝ እና የተፈጥሮ ሂደትን ባላመከለ መልኩ የሰው ልጆችን ደህንነት እና ሕልውናን አደጋ ላይ የሚጥሉ ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ወቅት ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞዋን ቤተክርስቲያን የማስተጋባት ሞራላዊ ግዴታ አለባት።

በሁለተኛ ደረጃ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮዎችን እንድትሰጠ መብት የሚሰጣት  ደግሞ የክርስቲያን ራዕይ ታሪካዊ ገጽታ ስላለው ነው። ቤተክርስትያን ከማኅበርሰቡ እና  ከታሪክ ጋር ከፍተኛ እና እውነተኛ ህብረት አላት። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ማብቂያ ላይ ይፋ ከሆኑ ሰነዶች መካከል አንዱ የሆነው እና ቤተክርስቲያን በአሁኑ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ማደረግ ስለሚገባት ሐዋርያዊ ተግባር በተመለከተ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ይፋ ካደረጋቸው ሰነዶች መካከል አንዱ የሆነው እና ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚመለከተው በላቲን ቋንቋ “GAUDIUM ET SPES” በአማርኛው “ደስታ እና ተስፋ” በሚል አርዕስት የቀረበው ሰነድ እንደ ሚያስረዳው “በዚህ ዘመን ያሉ ወንዶች ደስታ እና ተስፋዎች ፣ ሀዘንና ጭንቀቶች ፣ በተለይም ድሆች ወይም በማንኛውም መንገድ የተጠቁ ፣ እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች ሀዘንና ጭንቀት ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ሀዘንና ጭንቀት ናቸው” (GAUDIUM ET SPES PROMULGATED BY PASTORAL CONSTITUTION ON THE CHURCH IN THE MODERN WORLD HIS HOLINESS, POPE PAUL VI ON DECEMBER 7, 196፣ ቁ 1) በማለት ማነኛው ዓይነት በሰብዓዊነት ላይ የሚከሰቱ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተግባራት ቤተክርስቲያን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ እንደ ሚመለከታት ይገልጻል። በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ማእከሉን ያደርገው የሰው ልጆች ላይ ነው።

16 June 2020, 09:10