ፈልግ

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት 

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ

ክፍል አስራ ዐራት

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮዋን የምታከናውነው እና ቤተክርስቲያን “በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብቼ መሳተፌ ተገቢ ነው” በማለት ይህንን አስተምህሮዋን የምታከናውንበትን ምክንያት በሰፊው ስታብራራ የሚከተሉትን ማሳመኛ ነጥቦችን በመጥቀስ ነው።

ማንኛውም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሚጀምረው ግብረገባዊ ሥነ-ስርዓቶችን በቀጥታ ከተፈጥሮ በላይ ካለው መለኮታዊ የሆነ ኃይል ካለው ስነ-ምግባር ጋር በማቆራኘት ይጀምራል። ይህም ማለት ማንኛውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው አዎንታዊ የሆነ ስነ-ምግባር በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ከፈጣሪ ጋር ይገናኛል ማለት ነው።

በዚህም መሰረት የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የሆኑ እሴቶች በቀጥታ ከስነ-ምግባር ጋር የተቆራኙ ጉዳዮች በመሆናቸው የተነሳ እና እነዚህም ጉዳዮች የስነ-ምግባር እና የሃይማኖት እሴቶችን አቅፈው የሚይዙ ጉዳዮች በመሆናቸው የተነሳ ጭምር ቤተክርስቲያን የማኅበረሰቡ የሞራል፣ የስነ-ምግባር እና የሃይማኖት እምብርት በመሆኗ፣  ቤተክርስቲያን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብት ይሰጣታል ማለት ነው። ይህንንም ጣልቃ ግብነት የምታደርገው ሙያዊ የሆነ ትንታኔዎችን በመስጠት የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ በማስገደድ ሳይሆን ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እና ስነ-ምግባራዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ እነዚህ ስነ-ምግባራዊ እና ማሕበራዊ እሴቶች በታሪክ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በማሰብ የምታደርገው ጣልቃ ግብነት ነው።

በእርግጥ ይህ የቤተክርስቲያን “አስተምህሮ መልእክት በህብረተሰቡ ሕይወት ውስጥ በቀጥታ የሚመጣውን ውጤት ስለሚጠቁም የዕለት ተዕለት ሥራን እና ትግልን ስለሚመዝን ማህበራዊ ትምህርቶችን ማስተማርና ማስፋፋት ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ ቤተክርስቲያኗ ከተሰጣት ወንጌላዊ ተልዕኮ ጋር እና አዳኝ የሆነውን ክርስቶስን ከመመስከር ጋር የተያያዘ ነው” (John Paul II, Encyclical Letter Sollicitudo Rei Socialis, 41: AAS 80 (1988), 570-572)። ይህ የቤተክርስቲያኗ የተጓዳኝ ፍላጎት ወይም እንቅስቃሴ አይደለም፣ ወይም ቤተክርስቲያኗ በሁለተኛ ደረጃ የምታከናውነው ተልዕኮ አይደለም፣ ይልቁንም በቤተክርስቲያኗ የአገልግሎት ማዕከል ልብ ውስጥ የሚገኝ እና እንደ ማነኛውም የቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚቆጠር እና የሚተገበር ነው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትሳተፋለች ሲባል በአንድ ሀገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባለች ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን በደሎች፣ ኢፍታዊ ተግባሮች፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና ድኸ በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም ለዓለም ድምጿን ታሰማለች ማለት እንደ ሆነ ልብ ሊባል ይገባል። በእዚህ ረገድ የቤተክርስቲያናችን ተልዕኮ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፣ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው የመላእክት ጠባቂ ለመሆን ሳይሆን የሰው ልጆችን አቅፋ ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ በማድረግ፣ “የሕዝቡ ደስታ ደስታዬ፣ የሕዝቡ ለቅሶ ደግሞ ለቅሶዬ ወይም ሐዘኔ ነው” በማለት ሕዝቡ በሰላም እና በደስታ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን በረከት እየታቁዳሱ እንዲኖሩ ለማድረግ፣ በመጨረሻም የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የሆነ ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል።

በመጽሐፍ ቅዱሳችንም ውስጥ ይህ ጽንሰ ሐሳብ በብዙ ስፍራዎች ተጠቅሶ እናገኛለን። ለምሳሌ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል (ሉቃስ 4፡18) በማለት ኢየሱስ እዚህ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ ስገልጽ እንሰማለን። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው እና የድኾች አባት በማባል የሚታወቀው የፈረንሳይ ሀገር ተወላጅ የነበረው ቅዱስ ቪንሰንት ይህንን የኢየሱስን ዓላማ የግሉ መፈክር አድርጎ በመያዝ በወቅቱ በፈረንሳይ ሀገር ለነበሩ የድኸ ማህበረሰቦች አልኝታነቱን በመግለጽ ሐብታሞችን ከድኾች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን ማኅበራዊ ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጎ ማለፉን፣ በተመሳሳይ መልኩም በጣም ብዙ የሚባሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱሳን ለድኾች ያላቸውን አለኝታ በመግልጽ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እንዲወገዱ የበኩላቸውን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገው አለፈዋል። ቤተክርስቲያናችንም የክርስቶስን እና የእነዚህ ቅዱሳንን ፈለግ በመከተል በሕዝቦች ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ሁሉ በደሏ በማድረግ፣ ለቅሶዋቸው ለቅሶዋ፣ ሐዘናቸው ሐዘኔ ነው በማለት አሁንም የሰላም እና የፍትህ ጥሪዋን ታሰማለች።

ቤተክርስቲያን ይህንን የምታደርግበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት “የሰው ልጆችን ማዕከል” ባደርገ መልኩ ነው። የሰው ልጆች ባሉበት እምነት አለ፣ እምነት ባለበት ቤተክርስቲያን አለች፣ በተክርስቲያን ባለችበት ማኅበረሰብ አለ፣ ማኅበርሰብ ባለበት ደግሞ መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮች ይንጸባረቃሉ፣ ቤተክርስቲያን ስነ-ምግባራዊ የሆኑ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ፣ ሰዎች በሰላም እና በመከባበር እንዲኖሩ መልካም የሆኑ ነገሮችን በማበረታታት በተቃራኒው ደግሞ የማኅበርሰቡን ሰላም የሚነሱትን ክፉ ነገሮችን በብርቱ ትቃወማለች፣ እንዳይስፋፉም በወንጌል እና በሰበዓዊነት ላይ የተመሰረቱ አስተምህሮችን ትሰጣለች። ምክንያቱም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች እና ኢፍታዊ ድርጊቶች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ በመሆኑ የተነሳ ነው፣ በተለይ አቅመ ደካማ እና ድኸ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በኢፍታዊ ተግባራት ጫና የተነሳ ቀጥተኛ ሰለባ ስለሚሆን ማኅበራዊ አስተምህሮ አስፈላጊ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታምንበታለች።

 በማኅበራዊ ትምህርቷ ቤተክርስቲያን “እግዚአብሔርንና በክርስቶስ የተገኘውን የመዳን ምስጢር ለሁሉም የሰው ልጆች ታውጃለች፣ እናም በዚያው ምክንያት ሰው ራሱን ለሌላው ሰው የክርስቶስን ፍቅር እንዲገልጽ ያነሳሳዋል” (John Paul II, Encyclical Letter Centesimus Annus, 54: AAS 83 (1991), 860)። ይህ ቅዱስ ወንጌልን በቃል ከማወጅ ጋር ብቻ የተያያዘ ነገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ምስክርነት ከመስጠት የሚመነጭ አገልግሎት ነው።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

09 June 2020, 15:56