ፈልግ

የዘረኝነት ተቃውሞ ሰልፍ በኒዩ ዮርክ ከተማ፤ የዘረኝነት ተቃውሞ ሰልፍ በኒዩ ዮርክ ከተማ፤ 

ሊቀ ጳጳስ ዳንኤል፥ “ዘረኝነትን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ማውገዝ ይኖርብናል”።

በሰሜን አሜሪካ፣ የጋልቨስቶን-ዩስተን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል ዲ ናርዶ፣ ሰኔ 2/2012 ዓ. ም. ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ ዘረኝነት በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የቆየ ታሪክ መሆኑን አስታውሰው፣ እያስከተለ ያለውን ማኅበራዊ ችግር በመገንዘብ፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዳንኤል አክለውም ዘረኝነት በማኅበረሰባቸ ውስጥ በግልጽ ሲንጸባረቅ የቆየ መሆኑን ገልጸው፣ በቀላሉ መፍትሄ የሚገኝለት ባይሆንም መጋፈጥ ይኖርብናል ብለዋል። የጆርጅ ፍሎይድ የቀብር ሥነ ሥርዓት በትውልድ ከተማ በሆነችው ቴክሳስ፣ ሰኔ 9/2012 ዓ. ም. መፈጸሙ ታውቋል።  

የቫቲካን ዜና፤

ባለፉት ጊዜያት የቤተክርስቲያን መሪዎች ስለ ዘረኝነት ከመናገር ተቆጥበው መቆየታቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዳንኤል፣ ዘረኝነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ኢፍትሃዊ ተግባራት  ጎልተው ሲመጡ ተቃውሞን ማሰማት እየተለመደ መምጣቱን አስታውቀዋል። “ልባችንን ክፍት እናድርግ” የሚለውን እና ዘረኝነትን የሚቃወም የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሐዋርያዊ መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ዳንኤል፣ “እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ የሰሜን አሜሪካ ቤተክርስቲያን በተግባር መኖር አልቻለችም ብለዋል። ዘረኝነትን የሚያንጸባርቁ አንዳንድ ተግባራት በቤተክርስቲያናቸው ውስጥም መኖራቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል፣ ይህ እንዳይደገም እያንዳንዳችን ሃላፊነትን በመውሰድ እና በመታረም ከደረሰብን ቁስል ለመዳን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዘረኝነትን እና ኢፍትሃዊነትን የሚቃወሙ መልዕክቶችን ወደ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች በማሰራጨት ግንዛቤን ሲሰጥ መቆየቱን እና ከምዕመናን የሚመጡ የስልክ ጥሪዎችን በመቀበል የምክር አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ብጹዕ አቡነ ዳንኤል ገልጸው፣ ሀገረ ስብከታቸውም ዘረኝነትን በመቃወም ከማኅበረሰቡ አዕምሮ ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ ዝቅ ይላሉ፣ እራሳቸውን ከሌሎች እንደሚበልጡ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ፍርድን ይቀበላሉ” በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል፣ ዘረኝነት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚቃረን፣ ኢሰብዓዊ ተግባር በመሆኑ ሊወገድ ይገባል ብለዋል። ዘረኝነትን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ማውገዝ ይኖርብናል ብለው፣ ዘረኝነትን በአመጽ ሳይሆን ሃላፊነት በታከለበት ሰላማዊ መንገድ መቃወም ያስፈልጋል ብለዋል።

ጆርጅ ፍሎይድ ለሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ከእርሱ አስቀድሞ ኤሪክ ጋርኔርም እንደዚሁ “መተንፈስ አልችልም” በማለት የተናገሩትን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ በትክክል መተንፈስ እንችላለን ብለው፣ ይህን ማድረግ የምንችለው ዘረኝነት ያስከተለውን ኃጢአት ከማኅበረሰባችን መካከል ስናስወግድ ብቻ ነው ብለዋል።

 

12 June 2020, 13:16