በሕብረተሰቡ ውስጥ ቅዱስ ወንጌልን ማዳበርና ማስረጽ
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ
ክፍል አስራሁለት
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅታችን ተከታታዮች፣ ከእዚህ ቀደም በነበሩን ዝግጅቶቻችን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ እና ማህበራዊ አስተምህሮ፣ “ቤተክርስቲያን እግዚኣብሔር ከሰዎች ጋር የሚኖርባት ማደርያ ናት” በሚል አርዕስት አንድ ዝግጅት ወደ እናንተ አድማጮቻችን ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን በዛሬው በክፍል አስራሁለት ዝግጅታችን ደግሞ “የቤተክርስቲያን ተልዕኮ እና ማህበራዊ አስተምህሮ በሕብረተሰቡ ውስጥ ቅዱስ ወንጌልን ማዳበርና ማስረጽ” በሚል አርዕስት ያዘጋጀንላችሁን አስተምህሮ እናቀርብላችኋለን፣እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
አቅራቢ እና አዘጋጅ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
1.2. በሕበረተሰቡ ውስጥ ወንጌልን ማዳበርና ማስረጽ
ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሯን ወንጌልን ለመስበክና ውስብስብ በሆኑ የማኅበራዊ ግንኙነቶች መዋቅር ውስጥ እንዲገለጥ ለማድረግ ትፈልጋለች። ይህም በሕብረተሰቡ ውስጥ ወደ ሚኖረውና የቅዱስ ወንጌልን ስብከት ወደ ሚቀበለው ሰው የማድረስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡን ራሱን በወንጌል ትምህርት የማዳበርና እና የማስረጽ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን የሰውን ፍላጎት ትረዳለች ማለት ሕበረተሰቡን በተልዕኮዋና ደህንነትን ሥራዋም ጭምር ማሕበረሰቡን ታሳትፍላች ማለት ነው። “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል” (ሮሜ 8፡16) ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ቤተክርስቲያን ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ አላት። ብዙን ጊዜ ሰዎች በሕበረተሰቡ ውስጥ የሚኖሩበት የጋራ ሁኔታ፣ የኑሮ ደረጃን፣ ብሎም እያንዳንዱ ሰው ስለራሱ ማንነት የሚረዳበትንና ራሱንና ጥሪውን በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጥባቸውን ሁኔታዎች ይወስናል። ከዚህ የተነሳ ቤተክርስቲያን በህብረተሰቡ ውስጥ የሚደርገውን ውሳኔና የሚከናወነውን ነገር ችላ ማለት አትችልም። ስለግብረገባዊነት ጥራት ማለትም በእውነት ሰብአዊ ለሆኑና ስብአዊ ስለሆነ ማህበራዊ ሕይወት ገጽታዎች ትኩረት ትሰጣለች። ሕበረተሰብና እርሱ የሚከተለው ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ሥራ፣ ሕግ፣ ሉአላዊነት፣ መልእክት እና ዕቅድ በአንድ መልኩ ይሁን በሌላ ከእዚያ ውጭ አይደለም፣ ግብረገባዊነትን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ይነካልና። በመሰረቱ በሕብረተሰቡና በእርሱም ውስጥ የሚከናወነው ነገር ሁሉ ሰውን ይወክላል። ሕብረተሰብ “ለቤተክርስቲያን ቀዳሚና መሰረታዊ መንገድ” በሆኑ ወንዶች እና ሴቶች የተገነባ ነው። የማሕበረሰቡ ሥር መሰረት በፍቅር ላይ የተገነባ እንዲሆን ቤተክርስቲያን አጥብቃ ትሻለች። በፍቅር ላይ ሥር መሰረቱን ያደረገ ማሕበረሰብ ደግሞ የአብሮነት፣ የትብብር፣ የአንድነት . . . ወዘተ የመሳሰሉትን ትሩፋቶች ይቀናጃል ማለት ነው።
“ለእግዚአብሔር ህዝብ የሕይወት ህግ የሚወክለው የጋራ ፍቅር ትእዛዝ በኅብረተሰቡ እና በፖለቲካ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ሰብዓዊ ግንኙነቶች ማነቃቃት ፣ ማፅዳት እና ከፍ ማድረግ አለበት። ሰው መሆን ማለት ማሕበራዊ ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው። ምክንያቱም የቅድስት ሥላሴ አምላክ ምስል እና ሕብረት በፍቅር ትዕዛዙ ላይ የተመሰረተ የሁሉም “የሰው ልጅ ስነ ምግባር”መሠረት ናቸው” (Compedum of Catholic Social doctrine Teaching no 34) ።
ዘመናዊውን ባህል፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክስተት የሰብዓዊ አንድነት የሚያጠናክረውና በግልፅ የሚያረጋግጠው ፣ አሁን ደግሞ በራዕይ ብርሃን ውስጥ “የሰው ዘር አንድነት አዲስ ምሳሌ ነው፣ በመጨረሻም አንድነታችንን ሊያነቃቃ ይገባል። ይህ የላቀ ሕብረት ያለው አንድነት፣ ማለትም በሦስቱ አካላት (እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ) አንድም ሦስትም የሆነውን ቅርበት እና ሕብረት ያለው የእግዚአብሔር ሕይወት ነፀብራቅ ነው፣ ይህ ደግሞ እኛ ‘ክርስቲያኖች’ ሕብረት ብለን የምንጠራው ቃል ነው። ስለሆነም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለው የአንድነት እና የሕብረት መንፈስ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ የራሷን አዎንታዊ አስተዋጾ ለማድረግ ማሕበራዊ አስተምህሮዎቿን ተጠቅማ ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሐሳቦችን ታቀርባለች፣ ታስተምራለች።
ቤተክርስቲያን በማህበራዊ አስተምህሮዋ አማካይነት ጌታ በአደራ የሰጣትን ሥራ ትስብካለች። በክርስቶስ አማካይነት የመጣውን የነጻነት መልእክት በማወጅ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንዲገለጥ ታደርጋልች። ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ “በክርስቶስ ስም ለሰው፣ ለክብሩና ከሰዎች ጋር በሱታፌ ለመኖር ላለው ጥሪ ምስክር ትሆናለች። ከመለኮታዊ ጥበብ ጋር በሚጣጣም መልኩ የፍትህና የሰላምን አስፈላጊነት ታስተምረዋለች”።
ቤተክርስቲያን እና የሰው ልጅ የተሰላሰለ አንድነት አላቸው። ቤተክርስቲያን ያለ የሰው ልጆች ቤተክርስቲያን ሆና ልትቀጥል አትችልም። “ቤተክርስቲያን በሰው ልጆች ደስታ እና ተስፋዎች ውስጥ፣ በጭንቀት እና በሀዘን ውስጥ የምትካፈለው በሁሉም ስፍራ እና ጊዜ ውስጥ ካሉ ወንዶች እና ሴቶች ጋር በመሆን ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውን እና ቀጣይ የሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ለማምጣት ነው በመካከላቸው የምትገኘው” (Second Vatican Ecumenical Council, Pastoral Constitution Gaudium et Spes, 1: AAS 58 (1966), 1025-1026)።
በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያን የአንድነት እና የሕብረት፣ ብሎም የስነ-ምግባር መሰረት የሆነውን ቅዱስ ወንጌል በቤተክርስቲያን አማካይነት በዛሬው ዘመን በሚገኙ ሰዎች መካከል እዲያስተጋባ ታደርጋለች። ይህ ማኅበራዊ አስተምህሮ ደግሞ ነጻነትን የሚያመጣ ቃል ኪዳን ይሆናል። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ሰው ልብ ዘልቆ ከሚገባውና ለብን ለፍቅር፣ ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለሰላም ሃሳብና ዕቅድ ከሚያዘጋጀው ከእግዚኣብሔር መንፈስ የሚመጣ የእውነትና የእረፍት ስፍራ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ የማኅበራዊ ኑሮ ዘርፋን በወንጌል ስብከት ማዳረስ ማለት ለክርስቶስ እና ለሰው የሚስማማ ሕብረተሰብ ለመገንባት እንዲቻል በወንጌል የሚገኘውን መልእክት የማስተላለፍና የነጻነት ድል በሰው ልብ ውስጥ ማስተጋባት ማለት ነው። ለእግዚኣብሔር መንግሥት ይበልጥ የሚሰማማ እና ይበልጥ ሰብዓዊ የሆነ ከተማ መገንባት ማለት ነው።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፣ ይህ ቀድም ሲል ያቀረብንላችሁ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ በሚል አርዕስት ዘወትር ማክሰኞ የምናቀርበው ሳምንታዊ ዝግጅት ነበር። የዚህን አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት እናቀርብላችኋለን፣ እንድተታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
በፌስ ቡክ ገጻችን Vatican News – Amharic ላይ ዕለታዊ ዝግጅቶቻችንን መከታተል ትችላላችሁ!