ፈልግ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ  

የቤክርስቲያን ተልዕኮ እና ማህበራዊ አስተምህሮ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ

ክፍል አስራአንድ

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፣ ከእዚህ ቀደም በነበሩን ዝግጅቶቻችን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ አራት ዋና ዋና የታሪክ ሂደቶችን አልፎ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከእነዚህ ደረጃዎች መካከል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕዮተ ዓለም (እ.አ.አ 1891-1931)፣ አዲስ የክርስቲያን አስተሳሰብ (እ.አ.አ. 1931-1958)፣ አዎንታዊ አስተሳሰቦችን ከምያራምዱ ማኅበራዊ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል እና ትንቢታዊ አስተሳሰቦች (እ.አ.አ ከ1978-2005) የሚሉትን አራቱን  የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ያለፈባቸውን የታሪክ ሂደቶች በቅደም ተከተል በአጭሩ ከእዚህ ቀደም ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እለት የክፍል አስራአንድ ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተልዕኮ እና ማህበራዊ አስተምህሮ በሚል አርዕስት ያዘጋጀንላችሁን አስተምህሮ እናቀርብላችኋለን፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

አቅራቢ እና አዘጋጅ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ እና ማህበራዊ አስተምህሮ

1. ስብከተ ወንጌል እና ማህበራዊ አስተምህሮ

1.1 ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚኖርባት ማደርያ ናት!

በሰው ልጅ ደስታ እና ተስፋ፣ መከራና ሃዘን የምትካፈለው ቤተክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውን እና በእርሱ መካከል ያለውን የእግዚኣብሔር መንግሥት የምስራች ቃል ለመስበክ በሁሉም ስፍራ እና ጊዜ ከሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች ጋር ትቆማለች። እርሷ በሰዎች መካካለ እና በዓለም ውስጥ የእግዚኣብሔር ፍቅር ምስጢር ብሎም ለሰው ልጅ ነጻነት እድገት ለሚደረው እውነተኛ ሥራ እና ቁርጠኝነት መነሻ እና ማዳበሪያ የሆነው የድንቅ ተስፋ ምስጢር ናት። ቤተክርስቲያን በሰዎች መካከል የእግዚኣብሔር የመገናኛ ድንኳን “በሰዎች መካከል የእግዚአብሔር መኖሪያ” (ራእይ 21፡3) ናት። ይህም የሆነው ሰው ይበልጥ ዓለምን ሰብዓዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ብቻውን እንዳይሆን ተስፋ እንዳይቆርጥ ወዳጁንም እንዳይፈራ ለማደርግ ነው። ከዚህም የተነሳ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝ ፍቅር ድጋፍ ያገኛሉ። ቤተክርስቲያን የአንድነት አገልጋይ እንደ መሆኗ መጠን ረቂቅ ወይም መንፈሳዊ ብቻ ሳትሆን ሰው የሚኖርበት የታሪክና የዓለም ገጽታ ያላት ናት። በመሆኑም ሰው የእግዚኣብሔርን ፍቅር ያገኛል፣ ከመለኮታዊ ክብር ጋር መስተጋብር አለው።

እያንዳንዱ ሰው በህብረተሰቡ ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ክፍት የሆነ ዓይነተኛና የማይደጋገም ማንነት ያለው ፍጡር ነው። ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችንና ተዛማጅ ቡድኖችን፣ በእርስ በእርስ ግንኙነትና በሃሳብ ልውውጥ በሚያስተሳስረው የግንኙነቶች መዋቅር በሕበረተሰቡ ውስጥ በጋራ መኖር ትክክለኛ የኑሮ ጥርት እንዲረጋገጥ ያደርጋል። ሰዎች ማህበርሰቦችን በማቋቋም የሚሹትን የሚያገኙት የጋራ ጥቅም ለግላዊ፣ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ጥቅማቸው ዋስታና ነው። መዋቅሮች ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ሕጋዊና ባህላዊ አሰራሮች ላሉት ህብረተሰብ መነሻና ቅርጽ ምክንያት የሆኑት እነዚህ ጉዳዮች ናቸው። ቤተክርስቲያን “በዘመናዊ ህብረተሰብ ውስጥ ባሉ ውስብስብ የግንኙነት መዋቅሮች ለሚሳተፈው” የሰው ልጅ ማኅበራዊ ትምህርቷን ትሰጣለች። ስለ ሰው ልጅ ያላትን እውቀት የሰውን ጥሪ እና ተስፋ፣ እመንት እና ርኅራኄ፣ መብት እና ግዴታ የመረዳት እንዲሁም በሰዎች ሕይወት፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ የምታስተጋባውን የሕይወት ቃል የመናገር ችሎታ አላት።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፣ ይህ ቀድም ሲል ያስደመጥናችሁ የካቶሊክ ቤተክርስቲያ ማሕበራዊ አስተምህሮ በሚል አስርዕስት ዘወትር ማክሰኞ በእዚህ ሰዓት ወደ እናንተ የምናቀርበው ሳምንታዊ ዝግጅት ነበር። የዚህን ማሕበራዊ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት እናቀርብላችኋለን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

በፌስ ቡክ ገጻችን Vatican News – Amharic ላይ ይህንን ዝግጅት ለመከታተል ትችላላችሁ።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
12 May 2020, 11:53