ፈልግ

በክርስትና እና በእስልምና ሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት፣ በክርስትና እና በእስልምና ሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት፣ 

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በእምነት ተቋማት መካከል መተማመን እንዲያድግ አሳሰቡ።

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በክርስትና እና በእስልምና ሐይማኖት ተቋማት መካከል ሲደረግ የቆየው የጋራ ውይይት 18ኛ ዙር ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መልዕክቱ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደርግ የጋራ ውይይት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ካቶሊካዊ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በማከልም ከዚህ በፊት የኢጣሊያ ከተማ በሆነው በአሲዚ የተደረጉትን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይቶችን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡዳቢ ከተማ የተደረገውን የጋራ ውይይት እና ከውይይቱ በኋላ የጸደቀውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ መኖሩን በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የሐይማኖቶች አንድነት እና የአብያተ ክርስቲያናት የጋራ ውይይት ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ጁሊያኖ ሳቪና ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መጭው እሑድ ጥቅምት 23/2012 ዓ. ም. በመላው ኢጣሊያ ሊከበር የታቀደው የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች የጋራ ውይይት 18ኛ ዓመት ዋና ዓላማ በሁለቱ እምነቶች መካከል ያለውን ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለማሳደግ መሆኑ ታውቋል። በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ላለው ወዳጅነት ትልቅ እገዛን ያደረገው ያለፈው ዓመት ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ አቡዳቢ ከተማ ላይ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በአህመድ አል ጣይብ መካከል የተፈረመው የዓለም ሰላም እና የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት መሆኑ ታውቋል።

በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የጋራ ውይይት እንዲጀመር ምክንያት የሆነው፣ በመስከረም 1/1994 ዓ. ም. በኒዮርክ ከተማ የተፈጸመውን የአሸባሪዎች ጥቃት በጋራ ለመቃወም በመነሳታቸው መሆኑ ታውቋል። በውቅቱም በተደረገው የመጀመሪያ የጋራ ውይይት ላይ ሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት ፍርሃትን፣ ልዩነትን፣ አመጽን እና አክራሪነት ለማስወገድ በጋራ እንደሚሰሩ መስማማታቸው ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በኢጣልያ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች “ያለ ወንድማማችነት እና አንድነት መልካም የወደ ፊት ጊዜ ሊመጣ አይችልም” የሚል መፈክር የሚያስተጋቡ ሰላማዊ ሰልፎች በቪቼንዛ፣ በቶሪኖ፣ በቬሮና፣ በፋዬንዛ እና በሌሎችም የኢጣሊያ ከተሞች ሲካሄዱ መቆየታቸው ታውቋል።

ከአሲዚ እስከ አቡ ዳቢ፣

በጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በአቡዳቢ ከተማ የተደረሰው የዓለም ሰላም እና የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት በየዓመቱ ለሚከበረው የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት የበለጠ እንዲጠናከር መልካም አጋጣሚን እንደፈጠረላቸው፣ በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሐይማኖቶች አንድነት እና የአብያተ ክርስቲያናት የጋራ ውይይት ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ጁሊያኖ ሳቪና ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። በማከልም በየዓመቱ ለሚከበርው የሁለቱ ሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ቀን እንዲጀመር ቀዳሚ ምክንያት የሆነው ጥቅምት 17/1979 ዓ. ም. የተለያዩ ሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በኢጣሊያ ከተማ በሆነችው አሲዚ በተሰበሰቡበት ወቅት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ ዓለም ሰላም ያስተላለፉት መልዕክት መሆኑን አስረድተዋል።

በሰኔ 22/2011 ዓ. ም. በሮም በሚገኝ መስጊድ የተደረገ ስብሰባ፣

የሰላም ጥረት ሌላ ተጨማሪ አቅጣጫን ይዞ መጥቷል ያሉት ክቡር አባ ጁሊያኖ፣ የሰላም ተደራዳሪዎች እና የፖለቲካ አቋምን ይዘው ከሚቀርቡ ወገኖች በተጨማሪ ሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት፣ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ተገናኝተው የሚያቀርቡት የጋራ ጸሎት መልኮታዊ ሃይል ያለውን መሆኑን አስረድተው ይህ መለኮታዊ ሃይልም የሰውን ጥበብ እና ጉልበት የሚበልጥ መሆኑን አስረድተዋል። በአቡዳቢ ከተማ የተደረሰውን የዓለም ሰላም እና “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ያስታወሱት ክቡር አባ ጁሊያኖ ስምምነቱ የሁለቱን እምነቶች ተከታዮች አንዱ ሌላውን እንደ ወንድም እና እንደ እህት በመመልከት በመካከላቸው ፍቅርን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል። ክቡር አባ ጁሊያኖ ቀጥለውም ዘንድሮ ሰኔ 22/2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ ታላቁ መስጊድ ውስጥ የመላው ዓለም ሐይማኖት ተቋማት እና የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ለጋራ ጸሎት መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል።

እርስ በእርስ መከባበር፣

በመላው ዓለም የሐይማኖት ተቋማት እና የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች የጋራ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ስቴፋኖ ሩሶ መገኘታቸው የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ማስደሰቱን ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ በኢጣሊያ ከሚገኙ የእስልምና ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተጨማሪ ከሰነጋል፣ ከባንግላዲሽ፣ ከፓክስታን እና ከቱርክ የመጡ መኖራቸውን በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የሐይማኖቶች አንድነት እና የአብያተ ክርስቲያናት የጋራ ውይይት ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ጁሊያኖ ሳቪና ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 October 2019, 15:11