ፈልግ

የወንድማማችነት ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት፣ የወንድማማችነት ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና አል ጣይብ ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ።

ሰነዱ የሰላም እና የዕርቅ መንገድን ለመጓዝ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን የሚያመለክት፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ ሰላምን እና እርቅን የሚመኙ፣ መልካም ፈቃድ ያላቸው በሙሉ በጋራ ሆነው እንዲሠሩ የሚያሳስብ፣ በዘመናችን አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በስም በመጥቀስ ያስታወሰ፣ ድፍረት የታከለበት፣ ትንቢታዊ ሰነድ ከመሆኑ በተጨማሪ በእግዚአብሔር የሚያምን በሙሉ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በእምነት ተነሳስቶ ቆራጥ ውሳኔን በማድረግ፣ ሃላፊነትንም በመውሰድ፣ የሚኖርባት ዓለም ፍትህ የነገሠባት እንድትሆን ለማድረግ ትብብርን የሚጠይቅ ሰነድ ነው ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካለፈው እሑድ ጥር 26 እስከ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አርብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመፈጸማቸው በፊት ከአል አዛር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ከአል ጣይብ ጋር በመካከላቸው ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ስምምነት መፈራረማቸው ታውቋል። ስምምነታቸው ሰላምን እና እርቅን ማምጣት ለሚሹት፣ የክርስቲያን እና የሙስሊም ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን በጎ ፈቃድ ላላቸው በሙሉ መልካም መንገድ የሚከፍት ነው ተብሏል። በሁለቱ የእምነት ተወካዮች መካከል የተደረገው ስምምነት በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል በመደረግ ላይ ላለው የጋራ ውይይት፣ ለሰው ልጅ መጻዒ ሕይወት እድገት የሚያገለግል የሰላም እና የተስፋ ምልክት በመሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው በማለት የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ተገኝተው ያደረጉት ስምምነት፣ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ አክለው ገልጸዋል።

እንደ አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገለጻ መሠረት በሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች መካከል የተደረገው ስምምነት ክፋትን በበጎ መመለስ እንደሚያስፈልግ፣ በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያሳስብ፣ መቻቻልን እና እርስ በእርስ በመከባበር በሰው ልጆች መካከል ሁለ ገብ እድገት እንዳይመጣ የሚያደርጉ እንቅፋቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው ተብሏል።

ድፍረት የታከለበት ትንቢታዊ ሰነድ ነው፣

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በታላቁ አል አዛር ኢማም፣ በአል ጣይብ መካከል የተደረሰው ስምምነት የያዘ ሰነድ፣ የሰላም እና የዕርቅ መንገድን ለመጓዝ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን የሚያመለክት፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ ሰላምን እና እርቅን የሚመኙ፣ መልካም ፈቃድ ያላቸው በሙሉ በጋራ ሆነው እንዲሠሩ የሚያሳስብ፣ በዘመናችን አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በስም በመጥቀስ ያስታወሰ፣ ድፍረት የታከለበት፣ ትንቢታዊ ሰነድ ከመሆኑ በተጨማሪ በእግዚአብሔር የሚያምን በሙሉ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በእምነት ተነሳስቶ ቆራጥ ውሳኔን በማድረግ፣ ሃላፊነትንም በመውሰድ፣ የሚኖርባት ዓለም ፍትህ የነገሠባት እንድትሆን ለማድረግ ትብብርን የሚጠይቅ ሰነድ ነው ተብሏል።

የእግዚአብሔርን ስም ለክፉ ተግባር መጠቀሚያ ማድረግ አያስፈልግም፣

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ እንደገለጹት ሁለቱም የሐይማኖት መሪዎች፣ ማለትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የታላቁ አል አዛር ኢማም፣ አል ጣይብ በእኩል ድምጽ የእግዚአብሔርን ስም ለጦርነት ወይም ለክፉ ተግባር መጠቀሚያ እንዲያውለው የሚያስችል ስልጣን ለማንም እንዳልተሰጠ እና እንደማይሰጠው ማሳሰባቸውን ገልጸዋል። በሴቶች እህቶቻችን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም በደል እንደሚወገዝ ሁሉ ለመላው የሰው ልጅ ሕይወት ጥበቃን እና ክብርን መስጠት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል።

ባህልን ማሳደግ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የታላቁ አል አዛር ኢማም፣ አል ጣይብ በስምምነታቸው መደምደሚያ እንደገለጹት የሰው ልጅ በብዙ ችግሮች የተነሳ ቆስሎ እንደሚገኝ፣ ከችግሮችም መካከል ልዩነቶች እና የአክራሪነት ርዕዮተ ዓለም መኖሩን ገልጸው ይህን ለማስወገድ የውይይት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ለመጭው ትውልድ የተሻለ ዓለምን ማስረከብ የሚቻለው አሁን በምንኖርባት ዓለም ውስጥ በሰላም መኖር ስንችል ነው ብለዋል።                    

04 February 2019, 16:40