ፈልግ

በአስመራ ውስጥ ዕርዳታን ከሚማጸኑ እናቶች እና ሕጻናት መካከል፣ በአስመራ ውስጥ ዕርዳታን ከሚማጸኑ እናቶች እና ሕጻናት መካከል፣  

በኤርትራ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደረግ ተጽዕኖ በተርጂዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ተገለጸ።

የኤርትራ መንግሥት በአገሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ የተቸገሩ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት መፍጠሩን በስደት እና መከራ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን በማድረግ የሚታወቅ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አስታወቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲዘጉ መወሰኑ በሺህዎች የሚቆጠሩትን ዜጎች የሚጎዳ መሆኑ ታውቋል። የአካባቢው ምንጮች በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን ለሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንዳስታወቁት ውሳኔው በተለይም የገጠራማውን አካባቢ ነዋሪ ሕዝብ ጉዳት ላይ የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል። ከመንግሥትም በኩል ቢሆን ምንም ዓይነት እርዳታ ለማይደርሰው የገጠራማው አካባቢ ሕዝብ የምናበረክተው መጠነኛ የሆነ እርዳታን እንኳን እንዳናዳርስ ተከልክለናል ያለው የመልዕክቱ ምንጮች፣ ትምህርት ቤቶች ቢዘጉ፣ የሕክምና መስጫ ተቋማትም ቢዘጉ፣ በአገልግሎት ላይ የተሰማሩ ካህናት እና ደናግል አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ ቢገደዱ ተረጂው ሕዝብስ ምን ሊሆን ይችላል ማለታቸው ታውቋል።

ምንጮቹ በማከልም “ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ቢሆን ኤርትራን የሚያስታውሳት ወይም የሚያውቃት የሜዲቴራኒያንን ባሕር አቋርጠው ወደ ኢጣሊያ ወደቦች በሚደርሱ ኤርትራዊያን ስደተኝች ብቻ ነው ወይ”? በማለት ጥያቄውን አቅርቧል። በስደት ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንዳስታወቀው፣ የኤርትራ መንግሥት በቅርቡ 22 የሚሆኑ በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የሚገኙ በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመሩ የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዲዘጉ መወሰኑን ገልጾ፣ የመንግሥት ውሳኔ ለምን ይህ ሆነ ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ እ. አ. አ. በ1995 ዓ. ም. በወጣው እና ከመንግሥት ሌላ የሐይማኖት ተቋማት ማሕበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት በሚገድብ ደንብ መሠረት እንደሆነ መግለጹን አስታውቋል። ባለፉት ሁለት ዓመታትም ሌሎች ስምንት የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመንግሥት ትዕዛዝ መዘጋታቸውን ያስታወሰው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን መንግሥትስ ቢሆን በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች በቂ መድሐኒት እና ሕክምና መስጫ መሣሪያዎች እጥረት በሚታይበት ሁኔታ እንዴት ሥራ ማከናወን ይቻላል ብሏል።

ምንጮቹ እንደገለጹት ቢያንስ አገልግሎት እንዲያቋርጡ የተደረጉት የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች እና ማዕከላት ወደ ሕዝብ ንብረትነት ቢዛወሩ ኖሮ ሕዝቡ ተጠቃሚ መሆን ይችል ነበር፣ ነገር ግን ይህም ሳይሆን ቀርቶ ማዕከላቱ ታሽገው ኣንዲቀመጡ መደረጋቸው ሕዝቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።

በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንዳስታወቀ ዛሬ ላይ እንዲዘጉ የተደረጉ በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚተዳደሩ የጤና አገልግሎት ተቋማት የሕክምናን አገልግሎት ለሚሻ የአገሪቱ ሕዝብ በሙሉ አገልግሎት ሲያበረክቱ የቆዩ መሆናቸውን ገልጿል። እንዲታሸጉ የተደረጉት የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ በአገልግሎቱ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ደናግሎች መኖሪያም ጭምር በመሆኑ ባሁኑ ጊዜ ደናግል ወደ ሌላ የማሕበራቸው መኖሪያ በሆኑት ቤቶች ተጠግተው የሚኖሩ መሆኑ ታውቋል። ከደናግሉ አብዛኛዎቹ አገር ለቀው እንዳይወጡ የተከለከሉ መሆኑ ታውቋል። በኤርትራ መንግሥት ሕግ መሠረት ሴቶች ከ40 ዓመት ዕድሜ በታች፣ ወንዶች ደግሞ ከ50 ዓመት ዕድሜ በታች ከሆኑ ከአገር መውጣት የማይችሉ መሆኑ ሲታወቅ፣ ከተጠቀሱት የዕድሜ ጣሪያ በላይ ቢሆናቸው እንኳ በአገሪቱ የሚሰጠውን የውትድርና አገልግሎት ሳያበርክቱ ከአገር መውጣት የማይችሉ መሆኑ ታውቋል።

በአገሪቱ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚተዳደሩ 50 ትምህርት ቤቶች እና ከ100 በላይ የመዋዕለ ሕጻናት ማዕከላት እንዳይዘጉ ስጋት መኖሩ ታውቋል። ያለፈው ዓመት ብቸኛው የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት እንዲዘጋ መደረጉ ይታወሳል። የካቶሊክ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የመጨረሻ ፈተናቸውን በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ማዕከላት ሆነው እንዲፈተኑ ትዕዛዝ መውጣቱ ታውቋል።

ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች ከ1986 ዓ. ም. ወዲህ በፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የምትመራ መሆኗ ታውቋል። ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ኤርትራን፣ ሰብዓዊ መብቶችን ከሚጋፉ መጨረሻዎቹ አገሮች መካከል ሰባተኛ አገር አድርጓት መፈረጁ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

25 July 2019, 17:09