ፈልግ

በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሕክምና አገልግሎት ከምትሰጥባቸው ማዕከላት አንዱ፣ በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሕክምና አገልግሎት ከምትሰጥባቸው ማዕከላት አንዱ፣ 

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥት የህክምና መስጫ ተቋሞቿን መዝጋቱ የሐይማኖት ነጻነትን የሚቃረን ነው ብላለች።

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ መንግሥት የሕክምና አገልግሎት የምትሰጥባቸው ተቋማት እንዲዘጉ ማድረጉ እርዳታን ለሚማጸኑት በሙሉ የምታበረክተውን የቸርነት አገልግሎቶት የሚያግድ ነው ብላለች። የኤርትራ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የሚተዳደሩ 22 የሕክምና መስጫ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችንም የቤተክርስቲያኒቱን ማሕበራዊ አገልግሎቶች መንግሥት ተቀብሎ ማንቀሳቀስ ቀላል አለመሆኑ አስታውቋል። የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መልዕክቱ በቤተክርስቲያኒቱ ሥር የሚተዳደሩ 22 የሕክምና መስጫ ተቋማት እንዲዘጉ የተደረጉት ቤተ ክርስቲያኒቱ በማታውቀው እና ባልጠበቀችው መንገድ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ነው ብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕክምና ተቋማት የተዘጉት ማስፈራሪያ ታክሎባቸው ነው!

በኤርትራ ውስጥ የዛገር ሕክምና መስጫ ማዕከል እንዲዘጋ የተደረገው በውስጡ ይሠሩ የነበሩ ደናግል ማስፈራሪያ ተደርጎባቸው፣ ይገለገሉበት የነበረውንም የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ተበታትነው በነበሩበት ሁኔታ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ በፊት፣ ማለትም ያለፈው ዓመት መንግሥት በወሰደው እርምጃ 8 የሕክምና መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የወጣው መልዕክት አስታውሷል። የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንዳስገነዘበው መንግሥት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሕክምና ተቋሞቿን እንድትዘጋ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ማስፈራሪያ፣ ዛቻ እና አመጽ በታከለበት ሁኔታ መሆኑን ገልጿል። በአንዳንድ አጋጣሚዎችም በተቋሙ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ሥራቸውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱት ፈርመው እንደሆነ ገልጸው ፊርማውም በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ብቻ የሚፈጸም እንጂ በሌላ በማንም ሊሆን የማይገባ እንደነበር አስረድቷል።      

የሃይማኖት ነፃነት ጉዳት ደርሶበታል፣

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንዳስረዳው “በኤርትራ የሐይማኖት ነጻነት በህግ የተጠበቀ ነው” ተብሎ ቢነገርም ነገር ግን በቅርቡ ከመንግሥት በኩል የተወሰደው እርምጃ ቤተ ክርስቲያን ከፈጣሪ ዘንድ የታዘዘችውን እና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ የምታቀርበውን የወንድማማች ፍቅር በተግባር እንዳትፈጽም አግዷታል ብሏል። ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሕክምና መስጫ ተቋማት ጋር ሌላ መብት ተጥሶ ተገኝቷል ያለው የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት መልዕክት፣ ዜጎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ የመሆን መብታቸው መጣሱ ነው ብሏል። ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በማከልም የካቶሊክ ተቋማት በፖለቲካው ዓለም ጣልቃ በመግባት በዘርና በሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል የሚል ክስ በፍጹም ሊቀርብባቸው አይችልም ብሎ ምክንያቱም ተቋሞቿ ለማንም የማይወግኑ እና ለነፍሳት ደህንነት ብቻ የቆሙ ናቸው ብሏል።

የቸርነት ተግባር ሊከለከል አይገባም፣

እንደ ኤርትራ መንግሥት አገላለጽ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሚተዳደሩት የሕክምና ተቋማት ላይ የተወሰደው እርምጃ እ. አ. አ. በ1995 ዓ. ም. በወጣው እና የሐይማኖት ተቋማት ማሕበራዊ አገልግሎቶችን በሚገድብ ደንብ መሠረት መሆኑን ግልጿል። የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ አንድ ሕዝባዊ የፖለቲካ ስርዓት ለዜጎች የሚሰጠው የበጎ አድራጎት አገልግሎት ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረጉ ተቀባይነት ያለው አይደለም ብሏል። ሌሎች አገሮችንም ያየን እንደሆነ ማንኛውም ዓለማዊ ፖለቲካ የሚያራምድ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን የምታበረክተው የበጎ አድራጎት አገልግሎት እንዳይከናወን እንቅፋት ሲሆን አልታየም ብሏል። የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንዳስገነዘበው የቤተ ክርስቲያኒቱ የጤና ተቋማት በአገሪቱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚጫወተው ሚና እና ያለው ድርሻ ዝቅተኛ ነው መባሉ በሃቅ ላይ የተመሠረተ አይደለም ብሏል። በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሕክምና መስጫ ተቋማት በየዓመቱ ቢያንስ ለ200 ሺህ፣ በተለይም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች የሕክምና አገልግሎትን የሚያበረክት መሆኑን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

በሕክምና ተቋማት ሠራተኞች ላይ የሐሰት ክስ ተመስርቶባቸዋል፣

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በማከልም በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሕክምና መስጫ ማዕከላት የሚሠሩ ሠራተኞች ገንዘብ እንዲጎድል አድርገዋል በማለት በአንዳንድ ጋዜጦች በኩል የሐሰት ክስ ቀርቦባቸዋል ብሏል። ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ የሐሰት ክሱ ምናልባትም መንግሥት ለወሰደው እርምጃ እንደ ምክንያት ቀርቦ ይሆናል ካለ በኋላ የጋዜጣውንም ዘገባ ሐሰት ነው ብሎታል። መንግሥትም ቢሆን እስካሁን ድረስ የቤተክርስቲያኒቱን የጤና አገልግሎት ተግባር ከሙስና ጋር አለማያያዙን የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በመልዕክቱ አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 July 2019, 15:47