ፈልግ

በኮሎምቦ የምዕመናን ሐዘን እና ዋይታ፣ በኮሎምቦ የምዕመናን ሐዘን እና ዋይታ፣ 

የስሪላንካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት “የአሸባሪዎች ጥቃት ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል የለበትም”።

የስሪላንካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት አቡነ ዊስተን ፌርናንዶ፣ ሰሞኑን አሸባሪዎች በምዕመናን ላይ ያደረሱት የሞት አደጋ አሳዛኝ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በማሰብ አስጨናቂ ወቅቶችን በትዕግስት ማለፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የአገራቸው የፖለቲካ መሪዎችም የተከሰተውን አደጋ ለፖለቲካ ፍጆታቸው እንዳያውሉት አሳስበው የስሪላንካ የደህንነት አገልግሎት ስለ አደጋው መከሰት አስቀድሞ ያወቀ ቢሆንም መከላከል እንዳልቻለ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጎርጎሮሳዊውን የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ እሑድ ሚያዚያ 13/2011 ዓ. ም. በተከበረው የብርሃነ ትንሳኤው ዋዜማ ዕለት ምሽት፣ በስሪላንካ ዋና ከተማ በኮሎምቦ በሦስት ቤተክርስቲያኖች እና በሦስት ሆቴሎች ላይ ሸባሪዎች በሰነዘሩት የቦምብ ጥቃት ከሦስት መቶ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው እና ንብረት መውደሙ ይታወሳል። ከጥቃት በኋላ ለአገሩ ሕዝብ ንግግር ያደረጉት የስሪላንካ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ማይትሪፓላ ሲሪንሴና ጥቃቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ከአገሪቱ የደህንነት አገልግሎት በኩል መንግሥትን ምንም ዓይነት መረጃ አለ መድረሱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው በደህንነት አገልግሎት ላይ አስቸኳይ የስልጣን ሹም ሽር ማድረጋቸው ታውቋል። አሸባሪዎች ካደረሱት ጥቃት አስቀድሞ የሕንድ የደህንነት አገልግሎት፣ በስሪላንካ ውስጥ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ቢነገርም የስሪላንካ የደህንነት አገልግሎት ችላ ማለቱን ገልጸዋል። ከሕንድ የደህንነት አገልግሎት በኩል የደረሰው የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መጋቢት 26/2011 ዓ. ም. እንደነበር እና ሁለተኛ ማስጠንቀቂያም ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ እንደነበር ታውቋል። የሕንድ የመረጃ አገልግሎት እንዳስታወቀው የስሪላንካ ዋና ከተማ ኮሎምቦን ኢላማ ያደረገ የጥቃት ዕቅድ እንዳለ እና በደቡብ ሕንድ እና በስሪላንካ መካከል በድንበር አካባቢዎች፣ በማውልቪ ዛራን ቢን ሐሺም የሚመራ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን መግለጹ ታውቋል። የስሪላንካ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ከአገሪቱ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ለስሪላንካ የደህንነት አገልግሎት ከሕንድ በኩል በቂ መረጃዎች ደርሰው የነበረ ቢሆንም፣ የደረሰው መረጃ ወደሚመለከተው ክፍል ሳይደርስ ቀርቷል ብለዋል። ይህ የመረጃ ክፍተት አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአመራር ብቃት ማነስ እና ስንፍና ነው በማለት በስሪላንካ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቀሳን በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በአገሪቱ በሚገኙ ልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ዘንድ፣ አሸባሪዎች ባደረሱት ጥቃት ለሞቱት ምዕመናን የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተፈጸመ መሆኑ ሲታወቅ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የስሪላንካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ዊስተን ፌርናንዶ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ምዕመናኑ ከእግዚአብሔር ላገኘው መጽናናት እግዚአብሔርን አመስግነው፣ የብርሃነ ትንሳኤው በዓል ትልቅ በረከት በመሆኑ ምዕመናኑ የደረሰበትን ሐዘን እና ስቃይ በጸጋ ተቀብለዋል ብለዋል። በማከልም የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እና እርሱ ያስተማረው ትምህርት በቤተክርስቲያናቸው ላይ የሚደርስ ችግር፣ መከራን እና ሐዘንን በትዕግስ ለማለፍ ሐይል ሆኖናል ብለዋል። ከምዕመናን በኩል አንዳንዶቹ በብርሃነ ትንሳኤው ዕለት የሞትን ጽዋ መቅመስ የሚያስደስት ነው ማለታቸውን ገልጸው ይህም የምዕመናኑን የእምነት ጽናት እና ጥንካሬን ያመለከታል ብለዋል። በጥቃቱ የተቆጡ መኖራቸውን የገለጹት የስሪላንካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ዊስተን ፌርናንዶ እነዚህ ምዕመናንም ቢሆኑ ከካህናት ከደናግል እና ከምዕመናን ባገኙት የመጽናኛ መልዕክት ብራታትን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የስሪላንካ ካቶሊካዊት ቤተከስቲያን ካሁን ወዲያ ከመንግሥት ምን ትጠብቃለች?

ከመንግሥት በኩል በታየው ቸልተኝነት እጅግ ማዘናቸውን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ዊስተን ፌርናንዶ፣ ስለ ጥቃቱ መፈጸም መንግሥት አስቀድሞ መረጃ የደረሰው ቢሆንም ተገቢ ትኩረት እና ምላሽ እንዳልተሰጠበት ገልጸው ይህም የአገሪቱ የደህንነት አገልግሎት ድክመት ያሳያል ብለዋል። ለአገራቸው ጠንካራ አስተዳደር እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ብጹዕነታቸው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ድክመትን ምክንያት በማድረግ በአገሪቱ የሚገኙት የተለያዩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች የተፈጸመውን ስሕተት ለፖለቲካ ፍጆታቸው  እንዳያውሉት አሳስበው ይህን ከማድረግ ተቆጥበው ለአገሪቱ እድገት እና ደህንነት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ዊስተን ፌርናንዶ አገራቸው መልካም አስተዳደር ያስፈልጋታል ብለው የተከሰተውን ጥቃት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግ ተገቢም አይደለም ብለዋል።                                 

25 April 2019, 17:25