ፈልግ

ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዱ የሆነው የኮሎምቦ ከተማ ቅዱስ አንጦንዮስ ቤተክርስቲያን፣ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዱ የሆነው የኮሎምቦ ከተማ ቅዱስ አንጦንዮስ ቤተክርስቲያን፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእስያ ብጹዓን ጳጳሳት ተባብረው የስሪላንካን ቤተክርስቲያን እንዲደግፉ ጠየቁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሪላንካ አሸባሪዎች ያደረሱትን ጥቃት በድጋሚ አስታውሰው የመላው እስያ ብጹዓን ጳጳሳት እና ሌሎችም በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ የስሪላንካን ቤተክርስቲያን ለመደገፍ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። የጎርጎሮሳዊውን የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ ሚያዚያ 13/2011 ዓ. ም. በተከበረው የብርሃነ ትንሳኤው ዋዜማ ማለትም ያለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 12/2011 ዓ. ም. ምሽት ላይ አሸባሪዎች በስሪላንካ ዋና ከተማ በኮሎምቦ በሦስት ቤተክርስቲያኖች እና በሦስት ሆቴሎች ላይ በሰነዘሩት የቦምብ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ንብረት መውደሙ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የብርሃነ ትንሳኤውን በዓል ምክንያት በማድረግ ያለፈው እሑድ ለሮም ከተማ ሕዝብ እና ለዓለም ሕዝብ ካስተላለፉት መልእክት ቀጥለው በስሪላናካ ዋና ከተማ ኮሎምቦ ውስጥ በሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአሸባሪዎች በኩል በተሰነዘረው የቦንብ ጥቃት በርካታ ምዕመናን ሕይወታቸውን ማጣታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸው ድርጊቱን “የጭካኔ ተግባር” በማለት ማውገዛቸው ይታወሳል። አያይዘውም ከስሪላንካ ክርስቲያኖች ጋር ያላቸውን አንድነት ገልጸው ጥቃቱ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ካሉ በኋላ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።

የእስያ ብጹዓን ጳጳሳት፣

የእስያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም በበኩሏ፣ በስሪላንካ አብያተ ክርስቶያናት ላይ ከአሸባሪዎች በኩል በተሰነዘረው ጥቃት የተሰማትን ሐዘን መግለጿ እና ከሲሪላንካ ክርስቲያኖች ጋር በጸሎት በመተባበር አንድነቷን መግለጿ ታውቋል። የእስያ አህጉር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት የሆኑት እና በሚያንማር የያንጎን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ቻርልስ ቦ፣ በስሪላንካ ለኮሎምቦ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ለብጹዕ ካርዲናል አልበርት ማልኮልም ራንጂት በላኩት የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው፣ አሸባሪዎች በሰነዘሩት ጥቃት ምክንያት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ መጥፋቱ እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸው አደጋውም ሞት ድል የተደረገበት፣ ክፋትም በመልካም የተሸነፈበት የብርሃነ ትንሳኤው ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው “ሞት በሕይወት ላይ ስልጣን አይኖረውም፣ ክፋትም በመልካም ይሸነፋል እንጂ ሃይል የለውም” ብለዋል።

ከ300 በላይ ሰዎች ለሞቱበት እና ከ500 በላይ ሰዎች ክፉኛ ለቆሰሉበት የቦምብ ጥቃት እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ ክፍል አልተገኘም ተብሏል። በስሪላንካ የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃበት ከ2001 ዓ. ም. ወዲህ ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ ነው ተብሏል። የሞት አደጋ ከደረሰባቸው መካከል በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም መኖራቸው ታውቋል። የኮሎምቦ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ራንጂት በንጹሐን ዘጎች ላይ የተፈጸመው የሞት ጥቃት ኢሰብዓዊ ነው ብለው እርሳቸውም በበኩላቸው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው ማስታወሳቸውን ገልጸዋል።

በሚያንማር የያንጎን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ቻርልስ ቦ በመልዕክታቸው እንደገለጹት በአደጋው የተጎዱትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱ፣ በአደጋው ለቆሰሉት በርካታ ሰዎች የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙትን እና እርዳታን በማከፋፈል አገልግሎት የተሰማሩትን በሙሉ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ተናግረዋል። የትንሳኤው ጌታ፣ የሰላም እና የተስፋ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምህረቱን እንዲያወርድ፣ መልካም ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ በተከሰተው አደጋ ምክንያት ሳይደናገጡ፣ ፍርሃት እንዳይዛቸው እና ያለ መተማመን እንዳይኖር በጸሎታቸው ብርታትን ተመኝተው የእስያ አህጉር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ፌዴሬሽን እና መላው የእስያ ምእመናን የስሪላንካን ምእመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ቻርልስ ቦ አደራ ብለዋል።

ስሪላንካ ካላት 20 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 70 ከመቶ በላይ የቡዳ እምነት ተከታይ፣ 12.6 ከመቶ የሕንዱ እምነት ተከታይ እና 9.7 ከመቶ የሚሆን የእስልምና እምነት ተከታይ መሆኑ ሲነገር ወደ 1.5 ሚሊዮን ከሚሆኑ ወይም ከአገሩ ሕዝብ መካከል 6 ከመቶ ከሚሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች አብዛኛውን የካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆኑ ታውቋል።

የሕንድ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣

በሌላ ዜና የሕንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በበኩሏ በስሪላንካ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማትን ሐዘን መግለጿ ታውቋል። የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኦዝቫልድ ግራሲያ በስሪላንካ፣ ለኮሎምቦ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ለብጹዕ አቡነ ራንጂት በላኩት መልዕክት፣ አሸባሪዎች በፈጸሙት ጥቃት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው የአደጋው ሰለባ የሆኑትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸው በስሪላንካ ወንድሞች እና እህቶች ሕይወት ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ እና ትርጉም የሌለው ጥቃት ነው ብለዋል። የትንሳኤው አምላክ ፍትህን እና ሰላምን እንዲያወርድ ጸሎታችንን እናቀርባለን ብለዋል። በስሪላንካ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች፣ ድርጅቶች እና ግለ ሰቦች ሐዘናቸውን መግለጻቸው ታውቋል። ከእነዚህም መካከል የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሃንጋሪ እና የጀርመን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ የኢየሱሳሌም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምክር ቤት እና መንፈሳዊ ማህበራት፣ በኢጣሊያ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር፣ ከኢጣሊያ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት ከክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ፣ በችግር ላይ ለሚገኙ ቤተክርስቲያናትን ድጋፍን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እና የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ጠቅላይ ምክር ቤት የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል።           

23 April 2019, 17:28