ፈልግ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ወጣቶች፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ወጣቶች፣  

ደቡብ አፍሪቃ “ሕያው ክርስቶስ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን በመጠበቅ ላይ መሆኗ ተገለጸ።

በደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍ ሰፊ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ክቡር አቶ ሾን ላቴጋን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከወጣቶች ጋር በመሆን ወጣቶችን በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንዲሳተፉ ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው ለዚህም አንዳንድ አጋጣሚዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት “ሕያው ክርስቶስ” በሚል ርዕሥ በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ለንባብ የበቃው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንዲደርሰው መጠየቁ ተገለጸ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. በኢጣሊያ ውስጥ በሎሬቶ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባደረጉበት ዕለት የወጣቶችን ክርስቲያናዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን በስፋት የተመለከተውን እና “ሕያው ክርስቶስ” የተሰኘ አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በፊርማቸው አጽድቀው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከዓለም ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ሆነው ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ከተማ ባደረጉት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ወጣቶች፣ እምነታቸው እና ጥሪያቸውን በጥበብ እና በማስተዋል ተገንዝበው ትክክለኛ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕሥ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ የጉባኤያቸውን ጠቅላላ ሃሳብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማቅረባቸው ሲታወቅ ቅዱስነታቸውም የጉባኤውን ጠቅላላ ሃሳብ ተቀብለው ከተመለከቱት በኋላ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ “ሕያው ክርስቶስ” የተሰኘ አዲሱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እትም ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ለአንባቢዎች ይፋ መሆኑን በቫቲካን የተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ሕያው ክርስቶስ” የተሰኘ አዲሱ ቃለ ምዕዳናቸው ሦስት ክፍሎች እንዳሉት እነርሱስም ማድመጥ፣ ማስተዋል እና ትክክለኛ ውሳኔን ማድረግ የሚሉ እንደሆነ ያስታወቁ ሲሆን ለወጣቶች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀርብ የሚያግዝ ይህ ቃለ ምዕዳናቸው በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ወጣቶች ዘንድ በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየ መሆኑ ታውቋል።

በደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍ ሰፊ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ክቡር አቶ ሾን ላቴጋን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከወጣቶች ጋር በመሆን ወጣቶችን በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንዲሳተፉ ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው ለዚህም አንዳንድ አጋጣሚዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። አቶ ሾን ላቴጋን የግል ልምዳቸውን በማካፈል እንዳስረዱት ወጣቶችን በቤተክርስቲያ ሕይወት በንቃት ለማሳተፍ የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ ቢኖር፣ የግል ተሞክሮአቸውን እንዲያጋሩ ማድረግ እና ማደፋፈር እንደሆነ ገልጸዋል። አነሰ በዛም ወጣቶች የክርስቲያናዊ ሕይወት ወይም የቤተክርስቲያን ሕይወት ልምድ ሲኖራቸው በቤተክርስቲያን የመቆየት ፍላጎት ይኖራቸዋል ካሉ በኋላ ቀጥሎ ያለው ጥያቄ ወጣቶች የቤተክርስቲያን ሕይወት ልምድ እንዲኖራቸው እድሉን እንዴት እናመቻች የሚል ነው ብለዋል።

ወጣቶችን ወደ ቤተክርስቲያን በመጋበዝ እንዲሳተፉ ማበረታታት፣

ወጣቶች በቤተክርስቲያን ሕይወት እንዲሳተፉ ለማድረግ የተፈለገበት ሁለት ዋና ምክንያቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ሾን በቅድሚያ ወጣቶችን ወደ ቤተክርስቲያን በመጥራት በቤተክርስቲያን ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሁለተኛ ልብን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ይህም በወጣቶች እና በቤተክርስቲያን መካከል ግልጽነትን ለማሳደግ ስለሚረዳ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የአባልነት ስሜት እንዲኖራቸው ማድረግ እና ለደህንነታቸው ዋስትናን የሚያገኙት በቤተክርስቲያን ሲታቀፉ መሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አባል አቶ ሾን ላቴጋን ልምዳቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ዘርዝረው እንደገለጹት ወጣቶችን ወደ ቤተክርስቲያን ለመጥራት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የአባልነት ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶች አሉ ብለው ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ወጣቶች በዘመናዊው የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በኩል የሚያደርጉት ግንኙነት ሕብረትን በማሳደግ በመካከላቸው ፍቅርን ለመጨመር ይረዳል ብለው በተለይም ሙዚቃ፣ ማሕበራዊ መገናኛዎች እና የቪዲዮ ፊልሞች ጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እኔ ማነኝ? የየትኛው ወገን አባል ነኝ?

ወጣቶች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ትልቁ “እኔ ማነኝ? ከየትኛው ወገን ነኝ?” የሚሉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሾን ይህም አስፈላጊ የማንነት ጥያቄ እንደሆነ ተናግረው በዚህ ረገድ ሙዚቃ የወጣቶችን የማንነት ጥያቄን በመመለስ ትልቅ ሚናን ይጫወታል ብለው በሰሜን አሜርካ ውስጥ ወጣቶች ሙዚቃን በስፋት እንደሚያዳምጡ፣ የሚያዳምጡትም ሐፍታቸውን ለማሳወቅ ሳይሆን በሚያዳምጡት የሙዚቃ ዓይነት በኩል ማንነታቸው ማወቅ ስለሚችሉ ነው ብለዋል። ስለዚህ በቤተክርስቲያን እና በወጣት ማሕበራት ሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ ሙዚቃ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ሾው በየቁምስናዎች የመዝሙር አገልግሎት መጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

“ሕያው ክርስቶስ” የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስመልከት አስተያየታቸውን የገለጹት የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አባል አቶ ሾው፣ ይህ የቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ለወጣቶች ለሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስፈላጊውን ትኩርት እንዲሰጡ የሚያደርግ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸው ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ወጣቶችን በአገልግሎት ዘርፍ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን በገንዘብ አቅም ማገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ውጤታማ የሆኑ የወጣት ሐዋርያዊ አገልግሎት መሪዎችን ለማዘጋጀት ስልጠናን የሚያገኙበት እድል እንዲመቻችላቸው ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
02 April 2019, 18:50