ፈልግ

የመጋቢት 22/2011 ዓ.ም 3ኛው የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ የመጋቢት 22/2011 ዓ.ም 3ኛው የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ 

የመጋቢት 22/2011 ዓ.ም 3ኛው የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

“ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ”

“የእግዚአብሔርን ምህረት መፈታተን በፍጹም አይገባም!”

የእለቱ ምንባባት

1.     ዘጸዐት 3፡1-8

2.    መዝ 102

3.    1 ቆሮ. 10፡1-6. 10-12

4.    ሉቃስ 13፡1-9

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የንስሓ ጥሪ

በዚህ ጊዜ መጥተው፣ ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ያወሩለት ሰዎች በዚያ ነበሩ። እርሱም እንዲህ መለሰላቸው፤ “ታዲያ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ሥቃይ የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? አይደለም እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። ወይም ደግሞ በሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ በደለኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”

ደግሞም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ “አንድ ሰው በወይኑ ዕርሻ ቦታ የተተከለች አንዲት የበለስ ተክል ነበረችው፤ እርሱም ፍሬ ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፣ ‘እነሆ፤ ፍሬ ለማግኘት ልፈልግባት ሦስት ዓመት ወደዚህች በለስ መጥቼ ምንም አላገኘሁም፤ ስለዚህ ቍረጣት፤ ለምን ዐፈሩን በከንቱ ታሟጥጣለች?’ አለው።

“እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፍግ እስከማደርግላት ድረስ ለዘንድሮ ብቻ ተዋት፤ ለከርሞ ካፈራች መልካም ነው፤ አለበለዚያ ትቈርጣታለህ።’ ”

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ”

ዛሬ በተጀመረው ሦስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 13፡1-19) ስለእግዚኣብሔር ምሕረት እና እኛ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንዳለብን ይናገራል። ኢየሱስ ፍሬ አልባ ስለሆነ አንድ የበለስ ዛፍ ምሳሌ ይናገራል። አንድ ሰው በየአመቱ በመኸር ወቅት ፍሬ እንደ ሚሰጠው በመተማመን እና ተስፋ በማድረግ በወይኑ አትክልት ስፍራ የበለስ ዛፍ ይተክላል። በተከታታይ ለሦስት አመታት ያህል በተደጋጋሚ ፍሬ ባለመስጠቱ የተነሳ አዝኖና ተስፋ ቆርጦ ዛፉን ለመቁረጥ ይወስናል። ከዚያም በኋላ በወይን እርሻ ውስጥ የሚሰራውን ገበሬ ጠርቶ በዚህ ዛፍ አለምደሰቱን በመግለጽ ይህ ዛፍ መሬቱን ያለአግባብ እየተጠቀመ በመሆኑ እንዲቆርጠው ይጠይቀዋል። ነገር ግን አትክልተኛው ሰው ባለቤቱ ይህንን ዛፍ እንዲታገሠው እና ለአንድ ዓመት ያህል እንዲመለከተው በመጠየቅ ለዚህች የበለስ ዛፍ የበለጠ እንክብካቤ የተሞላበት ጥበቃ እንደ ሚያደርግ እና ይህ ዛፍ ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ለየት ያለ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ እንደ ሚያደርግለት የገልጽለታል። ይህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ነበር። ይህ ምሳሌ ምን ያመለክታል? በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ማንን ይወክላሉ?

የአትክልቱ ቦታ ባለቤት እግዚኣብሔር ሲሆን አትክልተኛው ደግሞ ኢየሱስ ነው፣ የበለስ ዛፍ ደግሞ  ግድየለሽ እና ደረቅ የሆነው የሰብአዊነታችን መገለጫ ነው። ኢየሱስ በአባቱ ፊት ሰለሰዎች ያማልዳል፣-ሁሌም እንዲህ ያደርጋል- ሰዎች የፍቅርና የፍትህ ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ጊዜ እንዲሰጣቸው ያማልዳል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እና ባለቤቱ ሊቆርጠው ያሰበው የበለስ ዛፍ የሚወክለው ፍሬ አልባ የሆነ ሕይወት ሲሆን ይህም ምርት መስጠት የማይችል መልካም ነገር የማያደርገውን ሕልውና ይወክላል። ለራሱ ብቻ የሚኖር፣ የተሟላ እና የተረጋጋ ሕይወት ያለው፣ በእራሱ ምቾት ብቻ ተዘናግቶ የተቀመጠ፣ በአከባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ትኩረት ያልሰጠ፣ በአጠገቡ ለሚኖሩ በችግር፣ በስቃይ እና በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ግድ የሌለው ሰውን ይወክላል። ይህ የራስ ወዳድነት መንፈስ እና መንፈሳዊ ድርቀት በንጽጽር ስንመለከት አትክልተኛው ሰው ለዚህ የበለስ ዛፍ ያለውን ታላቅ ፍቅር ይመለክታል፣ እርሱ ስራውን በሚገባ እስክያከናውን ድረስ እና ተገቢውን እንክብካቤ እስኪያደርግለት ድረስ ጌታው በትዕግስ እንዲጠባበቅ ይጠይቀዋል። ያ ፍሬያማ ያልሆነ ዛፍ ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ልዩ የሆነ እንክብካቤ እንደ ሚያደርግለት ለጌታው ቃል ይገባል።

ይህ የአትክልት ስፍራ ምሳሌ የእግዚያብሔርን ምሕረት ያሳያል፣ ይህም እኛ መንፈሳዊ ለውጥ እስክናመጣ ድረስ ጊዜ የሚሰጠን ነው። ሁላችንም መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንደ ሚገባን፣ በእየለቱ በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ በማምጣት ወደ ፊት መጓዝ እንደ ሚገባን፣ በዚህም የጉዞ ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት እና ምህረት አብሮን እንደ ሚጓዝ ያሳያል። ምንም እንኳን በሕይወታችን ውስጥ አንዳንዴ ፍሬያማ ባንሆንም እንኳን እግዚአብሔር ይታገሰናል፣ ወደ መልካም ጎዳና እንድንመለስ እና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እድገት ማምጣት እንችል ዘንድ እድል ይሰጠናል። አትክልተኛው ሰው ለባለቤቱ፣ “ጌታ ሆይ ለአንድ ዓመት ያህል ተወው” በማለት እንደ ተናገረው ቅዱስ ወንጌል ይተርካል። መንፈሳዊ ለውጥ የማምጣት ሂደት ገደብ የለውም፣ ስለዚህም በተቻለ መጠን በቶሎ መንፈሳዊ ልወጥ ማምጣት ይኖርብናል፣ ያለበለዚያ ግን ያ እድል መቼም ቢሆን ተመልሶ ሊመጣ አይችልም። በዚህ አሁን በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት በይበልጥ ወደ ጌታ ለመቀረብ ምን ማደርግ አለብኝ፣ መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት ምን ማድረግ ይኖርብኛል፣ በሕይወታችን ውስጥ ፍሬያማ እንዳንሆን የሚያደርጉንን ነገሮች እንዴት ቆርጠን መጣል እንችላለን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። “አይ እኔ የሚቀጥለውን የዐብይ ጾም ወቅት እጠብቃለሁ!” ማለት አይኖርብንም። በሚቀጥለው አመት የዐብይ ጾም ወቅት በሕይወት እኖራለሁ ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ? ሁላችንም ብንሆን ዛሬን ብቻ ነው ማሰብ የሚገባን፣ በዚህ በትዕግስት በተሞላው የእግዚኣብሔር ምሕረት ፊት ሆኜ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። በእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ ላይ በእጅጉ ልንታመን እንችላለን፣ ነገር ግን ይህንን የምሕረት ጸጋ አላግባብ መጠቀም አይኖርብንም። በእግዚኣብሔር ምሕረት ተማምነን መንፈሳዊ ድክመቶቻችንን ጤናማ አድርገን በመቁጠር መኖር አይኖርብንም፣ ነገር ግን በልበ ቅንነት ለዚህ የእግዚኣብሔር ምህረት ፈጣን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

በዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ጌታ ጥሪ ያቀርብልናል። እያንዳንዳችን በዚህ ጥሪ ተፈትነን፣ በህይወታችን ውስጥ የሚከሰቱትን፣ አስተሳሰባችንን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በማረም ለዚህ ጥሪ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል። በተመሳሳይም ሁላችንም የእግዚኣብሔርን ትዕግስት እንደ መልካም አጋጣሚ እና እድል በመጠቀም ተነስተን መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችለውን ጉዞ መቀጠል ይኖርብናል። እግዚአብሔር አባት ነው፣ በመሆኑም ደካማውን አያጥፋውም፣ ነገር ግን ደካማው እንዲጠነክር እና በርትቶ እንዲሰራ እድሉን ይሰጠዋል፣ እንክብካቤም ያደርግለታል። በዚህ ለፋሲካ በዓል ዝግጅት በምናደርገበት የዐብይ ጾም ወቅት የምናደርገውን ዝግጅት በተገቢው መልኩ ማከናወን እንችል ዘንድ፣ መንፈሳዊ የሆነ ተአድሶ እንድናመጣ እና ለእግዚኣብሔር ጸጋ እና ምሕረት ራሳችንን መክፈት እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማለጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 15/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

28 March 2019, 11:47