ፈልግ

ዐብይ ጾም በተጀመረበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የዐመድ መቀባት ስነ-ስረዓት በተካሄደበት ወቅት ዐብይ ጾም በተጀመረበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የዐመድ መቀባት ስነ-ስረዓት በተካሄደበት ወቅት  

ጾም ምንድነው? መጾምስ ለምን አስፈለገ?

ጾም ማለት የርሃብ አድማ መምታት ማለት ሳይሆን ራሳችንን በመግዛት፣ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔርን እና ወንድሞቻችንንን በመውደድ መንፈሳዊ ጸጋ እንድናገኝ የምንጸልይበት የንስሓ ወቅት ነው።

በኦሪት ዘጸአት ላይ እንደ ተጠቀሰው እስራኤላዊያን በግብጽ በጭቆና ስር በነበሩበት ወቅት በከፍተኛ ለቅሶ እና ስቃይ ውስጥ ገብተው በነበሩበት ወቅት ምንጊዜም የሕዝቡን ስቃይና ለቅሶ ማዳመጥ የማይታክተው እግዚኣብሔር በሙሴ አማካይነት በባርነት ቀንበር ሥር ከነበሩበት ከግብጽ እንዲወጡ በማድረግ ለ40 ዓመታት በበረሃ ውስጥ በጠንካራ ክንዱ እየመራቸው ወደ ነጻነት እንደ ወሰዳቸው ይታወቃል።

በተመሳሳይ መልኩም እነዚህ 40 የዐብይ ጾም ቀናት ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁላችን ከባርነት እና ከኋጢያት ተላቀን ወደ ነፃነት በመጓዝ ከክርስቶስ ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው። እያንዳንዱ እርምጃ፣ ድካም፣ ፈተና፣ ውድቀትና ከውድቀት መነሳት የመሳሰሉትን ነገሮች አቅፎ የያዘ ሲሆን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት በእግዚኣብሔር የደኅንነት እቅድ ውስጥ አስቀምጠን ስንመለካታቸው ብቻ ነው። ይህንን ጉዳይ በጥልቀት በምንገመግምበት ወቅት እግዚኣብሔር የእኛን ሞት ሳይሆን ደህንነታችንን ስቃያችንን ሳይሆን ደስታችንን እንደ ሚፈልግ መገንዘብ እንችላለን።

ዐብይ ጾም መንፈሳዊ ለውጥ የምናደርግበት ወቅት ሊሆን ይገባል፣ ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት ተገቢ በሆነ መልኩ የሚጓዝ ሰው በለውጥ መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ ይገኛል ለማለት እንችላለን፣ የዐብይ ጾም ወቅት ከኋጢያት ባርነት ወደ ነፃነት የሚደረግ የለውጥ ጎዞ ነው።

ነገር ግን በረሃን አቋርጦ መጓዝ ቀላል ነገር አይደለም፣ በበርሃ ውስጥ ድካም፣ ፈተና፣ ጥርጣሬ የመሳሰሉት ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉና። በእነዚህም ነገሮች ውስጥ ልክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጁዋ በመከራ ውስጥ በነበረበት ወቅት ሁሉ በታላቅ እምነት ከሙታን እንደ ሚነሳ እና የእግዚኣብሔር ፍቅር ሁሌም አሸናፊ እንደ ሚሆን አምና በተስፋ እየተጠባበቀች እንደ ነበረች ሁሉ እኛም ተስፋ መቁረጥ አይገባንም በእዚህም ተስፋ ተሞልተን የዐብይ ጾም ወቅትን በታላቅ ደስታ እና ተስፋ መኖር ይጠበቅብናል።

ቤተክርስቲያን ለሕዝቦች የድህነንነት መንገድ ለማዘጋጀት፡ ፆምን ታውጃለች፣ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የበለጠ ያስገዙ ዘንድ  በትህትና ይመላለሱ ዘንድ፤ ፀጋን ያገኙ ዘንድ  ጊዜን መድባ ፆምን እንድንጾም ታዘናለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ የአንድነት ጉዞ፣ የጋራ ጉዞ ነውና በዚህ የጋራ ክርስቲያናዊ ጉዞ የተለያዩ የፆም ጊዜያት ቤተ ክርስቲያን ወስና ሰጥታናለች፡፡ ከእነዚህም አንዱ ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጉጉት የምንጠብቀው የዐብይ ጾም ነው፡፡ ይህን ልዩ የጸጋ ጊዜ፡  ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ጊዜ እያንዳንዳችን  ዕድሉ እንዳያመልጠን መትጋት ይኖርብናል (ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  የ2010 ዓ.ም የዐብይ ጾም ወቅትን አስመልክተው ካስተላለፉት መልእክት የተወሰደ)

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የ2009 ዓ.ም  የዐብይ ጾም መግቢያን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት “ዐብይ ጾም እኛ ምዕመናን የሥጋ ፈቃዳችንን በመተው የነፍሳችንን ፈቃድ በሙሉ ልባችን በማስገዛት የምንጾመው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ራሳችንን ከዓለማዊ ነገሮች በማራቅ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን የምንፈጽመውና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቀርበን የእርሱን የምህረት ደጅ በመጥናት ጌታ ሆይ ማረን ጌታ ሆይ ራራልን፣ጌታ ሆይ፣ይቅር በለን በማለት የእርሱን ምህረት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ወቅት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በማቴዎስ ወንጌል 6፡16-24 ላይ ጾም በምንጾምበት ወቅት ማድረግ የሚገባንን ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን በዝርዝር ያስቀምጣል። በመጀመሪያ ደረጃ “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ” (ቁ. 16) የሚለው ሲሆን በማስከተል ደግሞ “አንተ ግን ስትጾም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ” (ቁ. 17) የሚለው ሲሆን በሦስተኛ እና በመጨረሻ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ “ሐብትህን ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት በምድር ላይ አትሰብስቡ ነገር ግን ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት በሰማይ ላይ ሐብታችሁን አከማቹ” (ቁ. 19-20) በማለት ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይመክረናል። በመጀመሪያ “አንተ ግን ስትጾም” በማለት ይጀምራል። ጾም ምንድነው የሚለውን ጥያቀ ይጭርብናል። በሁለተኛ ደረጃም በምንጾምበት ወቅት ፊታችንን ላይ ጹዋሚ መሆናችንን ለሰዎች ለማሳየት ብለን ፊታችን ላይ የሐዘን ምልክት ማሳየት እንደ ሌለብን ያሳስበናል። በሦስተኛ ደረጃ አብታችንን ሌባ በሚሰርቀ ሥፍራ ሳይሆን ማኖር ያለብን ብል በማይበላው ስፍራ በሰማይ ማኖር እንደ ሚገባን ያሳስበናል።

ጾም ምንድነው? መጾምስ ለምን አስፈለገ?

ስለ ጾም አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዘርዝረው ከሚገኙ በርካታ አመላካች ከሆኑ ጥቅሶች መካከል የተወሰኑትን እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

ጾም በብሉይ ኪዳን ውስጥ

በሐይማኖታዊ ምክንያት ያለ ምግብና ያለ መጠጥ መዋል (መ. አስቴር 4.16)፣ ከሥጋና ከሚያረክስ መጠጥ መታቀብን ያመለክታል ይለናል (ትንቢተ ዳኔል 10. 2.3)። ሙሴ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ጾመ (ዘዳግም 9:9,19)። የእስራኤል ሕዝብ በማስተሰሪያ ቀን እንዲጾሙ ታዘዙ (ኦ. ዘሌዋዊያን 16. 29-31)። ከባቢሎንም ምርኮ ቡኋላ ለእስራኤል ሕዝቦች አራት የጾም ጊዜያት ታወጁ (ት. ዘካሪያስ 8.19)። ከእነዚህም ሌላ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተነሳ የግል ጾም (2ሳሙኤል 12:22) ወይም ደግሞ የማኅበር ጾም (መ.መሳፍንት 20:26, በተጨማሪም በመጽሐፈ ኢዮብ 1:14) መታወጁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እናገኛለን።

በተጨማሪም ጾም ሐዘንን (መ. ነህምያ 1:4)፣ ንስሓን (1ሳሙኤል 7:6)  ላይ እንደ ተጠቀሰ ያሳያል። ሰዎች በጾም ራሳቸውን አዋረዱ (መዝሙር 69:10)፣ የእግዚኣብሔርን እርዳታ ፈለጉ (ዘጸሃት 34: 28፥ ዕዝራ 8:21-23) የሚለውን ያሰማናል። ነብያትም ጾም ምን ማለት እንደ ሆነ በመልካም ሁኔታ ገልጸዋል (ኢሳያስ 58: 1-12፣ ኤርሚያስ 14:11,12) የተጠቀሱትን በጾማችን ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብን እና በጾማችን ወቅት ለባልንጀሮቻችን መልካምን ነገር በማድረግ በእግዚኣብሔር ፊት ሞገስ አግኝተን ለኋጢያታችን ካሳ፣ ለነብሳችን ፈውስ፣ ለስጋችን ደግሞ ጤናና በረከት የምናገኝበት ወቅት እንዲሆን መፈጸም የሚገባንን ተግባራትን ይዘረዝራሉ።

በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ ልክ በሐዋሪያት ሥራ 27:9 እንደ ተጠቀሰው አይሁዳዊያን የማስተሰሪያ ጾምን አከበሩ ይለናል። ፈሪሳዊያንም በሳምንት ሁለት ጊዜ ሰኞና ሐሙስ ይጾሙ ነበር (ሉቃስ 18:12) ላይ መንበብ ያቻላል። እነ ሐናም ብዙ ጊዜ ይጾሙ ነበር (ሉቃስ 2:37)፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀን መጾሙንና ለእኛም የጾምን አስፈላጊነት አስተማረ (ማቴዎስ 4:2) ላይ እንደ ተጠቀሰው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር በነበረበት ወቅት አልጾሙም ነበር ወደ አባቱ ከሄደ ቡኋላ ግን እንደ ሌሎቹ እንዲጾሙ ነገራቸው ይለናል የማቴዎስ ወንጌል 9: 14-17።

በጾማችን ወቅት ሁሉ እግዚኣብሔርን እንጂ ሰውን ማየት እንደ ማይገባ መጽሐፍ ቅዱሳችን ያስተምረናል (ማቴ. 6:16-18)። ምዕመናን ወንጌላዊያንን ሲልኩ፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን (ቀሳውስትን) ሲሾሙ ይጾሙ እንደ ነበረ በሐዋሪያት ሥራ 13:2 የተጠቀሰውን የባርናባስና የሳውልን ለልዩ ተልዕኮ መመረጣቸውን ይገልጽልናል። ዋንኛው የጾም ዓላማ ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘት ነውና ሰው ሲጾም ጊዜውን ለጸሎት ሊያውል ይገባዋል በመጽሐፈ ዕዝራ 8:23፣ በማቴዎስ 17:21 እና በሉቃስ 2:37 ላይ እንደ ተጠቀሰው። በአጠቃላይ ጾም ምዕመናን ሁለንተናቸውን ከዓለማዊ ሀሳብና ምኞት መልሰው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲያተኩሩና እንዲጸልዩ ያደርጋቸዋል። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ጾም ማለት የርሃብ አድማ መምታት ማለት ሳይሆን ራሳችንን በመግዛት፣ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔርን እና ወንድሞቻችንንን በመውደድ መንፈሳዊ ጸጋ እንድናገኝ የምንጸልይበት የንስሓ ወቅት ነው። ታዲያ ጾም ለእኛ ለክርስቲያኖች የርሃብ አድማ ማለት አይደለም የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ከሆነ በተለይ ለኛ ለክርስቲያኖች ለየት ያለ ትርጉም ሊሰጠን ይገባል ማለት ነው።

“ጾም የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታዊ እውነታዎችን እንድናውቅና በዚህ መንገድ የእግዚኣብሔር ቃል ሕይወታችንን ዘልቆ በመግባት እኛ የሕይወታችን የጉዞ መንገድ ምን መሆን እንዳለበት በማስረዳት ማን እንደሆንን፣ ከየት እንደመጣን ወዴት እንደ ምንሄድ እንድንገነዘብ በማድረግ የሕይወትን መንገድ ያሳየናል” (በነዴክቶስ 16ኛ ከተናገሩት የተወሰደ)።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

28 March 2019, 14:57