ፈልግ

በደቡባዊ ጋዳሬፍ ግዛት ውስጥ የተፈናቀሉ ሱዳናውያን በደቡባዊ ጋዳሬፍ ግዛት ውስጥ የተፈናቀሉ ሱዳናውያን  (AFP or licensors)

ሱዳናዊያን ሲቪሎች ከፍተኛ ጥቃት፣ እንግልት እና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን እየተጋፈጡ ነው ተባለ

አስራ አራተኛ ወሩን የያዘው በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት ምንም ዓይነት የመርገብ ምልክት እንዳለሳየ የተገለጸ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እና የሰብአዊነት መብት ተሟጋቾች በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሲቪሎች ከለላ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሱዳን ጦር እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት እስካሁን በትንሹ 15,000 ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት እንደተገደሉ፥ እንዲሁም ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ 8 ሚሊዮን ያህሉ በሀገር ውስጥ እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በጎረቤት ሃገራት ቻድ እና ደቡብ ሱዳን ተሰደዋል።

ግጭቱን ተከትሎ ምግብ፣ መድኃኒት እና የሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት በካርቱም እና በሌሎች አካባቢዎች በመከሰቱ ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ።

በኃያላኑ የሱዳን የጦር መሪዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት 25 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን በሕይወት ለማትረፍ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካባቢዎችም ሰብአዊ እርዳታውን ለማቅረብ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ተነግሯል።

እንደ ‘ኤም ኤስ ኤፍ ዶክተሮች’ እና የሥራ ባልደረቦችን የመሳሰሉ በአከባቢው የሚገኙ የእርዳታ ሰራተኞች የጤና ተቋማትን ጨምሮ የሲቪል መሰረተ ልማቶች በተዋጊዎቹ የጥቃት ኢላማ በመሆናቸው ለሲቪሎች እና ለህክምና ባለሙያዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው የተማጸኑ ሲሆን፥ የሰብአዊነት ህግን ንቀው ሰላማዊ ዜጎችን እየጨፈጨፉ ባሉ ወታደሮች እና ሚሊሻዎች እየደረሰ ያለውን አስደንጋጭ ጭካኔንም አውግዘዋል።

በህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች

በዓለም ዙሪያ በተከሰቱ ግጭቶች በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ሪፖርት በማድረግ የተከሰሰችው የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልዕክተኛ እንደገለጹት በመጀመሪያነት እና በዋናነትበጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ውስጥ በወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለው ነገር እንደሚያሳስባቸው ተናረዋል።

ልዩ መልዕክተኛዋ ቨርጂኒያ ጋምባ “በቀሪዎቹ የዚህ ዓመት ወራቶች እና የሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ ከምንም በላይ የሚያሳስበኝ ጉዳይ የሱዳን በተለይም ዳርፉር እና ቻድ ጉዳይ ነው፥ ምክንያቱም [ጦርነቱ] እየተስፋፋ ነው” ብለዋል።

በተፋላሚ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለው “አስፈሪ የትጥቅ ትግል” በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ለግድያ እና ለአካል ጉዳት፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶችን በመፈጸም፣ በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች ላይ ጥቃት በማድረስ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን እና የሱዳን ጦር ሃይሎችን በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንዲካተት ማድረጉን ገልጸዋል።

ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ቅዳሜ ጉባኤያቸውን ያጠናቀቁት የሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት መሪዎች በሰሜን ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሁኔታ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በወቅቱ ባወጡት ረቂቅ መግለጫ ላይ የውጭ አካላት በሱዳን ያለውን ግጭት ማባባሱን እንዲያቆሙ አሳስበው፥ በግጭቱ ምክንያት “በሲቪል ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በየጊዜው እየባሰበት ነው” ብለዋል።

ረሃብ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ ኢኮኖሚውን ስላሽመደመደው የህዝቡን ብሶት በማባባስ ሚሊዮኖች ለረሃብ እየተጋለጡ ሲሆን፥ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በሀገሪቱ ትልቁ የግብርና ምርት የሚመረትባት የገዚራ ግዛት ተቆጣጥሯል።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ ምግብ የሚያቀርበው እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በህይወት እንዲቆዩ እያደረገ ያለው ‘ካርቱም ኤይድ ኪችን’ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በሚቀጥለው መስከረም ወር 70 በመቶው ህዝብ “አስከፊ ረሃብ” እንደሚጠብቀው እና በዚህም ምክንያት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በረሃብ ምክንያት ሊሞት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
 

18 June 2024, 17:43