ፈልግ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኦፕሬሽን አካል ሆኖ የምግብ እርዳታ ጋዛ በሚገኘው ዴር አል ባላህ ከተማ እየተሰራጨ ይገኛል የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኦፕሬሽን አካል ሆኖ የምግብ እርዳታ ጋዛ በሚገኘው ዴር አል ባላህ ከተማ እየተሰራጨ ይገኛል   (© WFP/Photolibrary)

እስራኤል ዕርዳታ እንዲገባ በጋዛ ዋና መንገድ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ቁጥጥር ገታ ማድረጓ ተነገረ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ዋና መንገድ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲገባ ወደፊት ገደቡ መነሳቱ እስከሚገለጽ ድረስ በየቀኑ ለተወሰኑ ሠዓታት ወታደራዊ እንቅስቃሴውን መግታቱን፥ ይህም እስካልተወሰነ ጊዜ ድረስ እንደሚቀጥል ገልጿል። በአንጻሩ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ የሃማስ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረው ውጊያ ይቀጥላል ማለቱን ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ አንዳንድ አካባቢዎች ተጨማሪ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲገባ ስትል ከዚህን በፊት ስታደርግ የነበረውን ጥብቅ ወታደራዊ ቁጥጥር 'ዕለታዊ ስልታዊ ፍቃድ' በሚል ክፍት ማድረጓ ተነግሯል።

እንደ ጦሩ ገለጻ፥ ከኬረም- ሻሎም ማቋረጫ ወደ ሳላህ አል-ዲን እና ወደ ሰሜን በሚወስደው መንገድ ወታደራዊ እንቅስቃሴው ከሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በየቀኑ ለሠዓታት ጋብ እንደሚል ተብራርቷል።

የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በጋዛ ዙሪያ ዕርዳታን ለተጎጂዎች ለማከፋፈል ከፍተኛ ችግር እንዳለ ደጋግመው ሲዘግቡ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ኤጀንሲ የሆነው ዩኒሴፍ እንዳስታወቀው ከዚህን በፊት እርዳታ የጫኑ መኪኖች አስፈላጊው የፍቃድ ወረቀት ቢኖራቸውም ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይገቡ መከልከሉን ዘግቧል።

ሰብአዊ እርዳታውን ከጫኑት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ጋር የነበሩት የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጀምስ ኤልደር እንደተናገሩት ይህ ሁኔታ ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ሐማስ በራፋህ በፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት የተገደሉትን የስምንት ወታደሮችን ማንነት ይፋ አድርጓል። ከኢየሩሳሌም የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ወታደሮቹ የተገደሉት በራፋህ የአዳር ተልእኮ ካደረጉ በኋላ ወደ ጦር ሰፈር እያመሩ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቅዳሜ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ያለውን ሁኔታ “ከባድ ጦርነት” ሲሉ የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ሀገሪቱ ሃማስን በማጥፋት እና በጋዛ የታሰሩትን እስራኤላውያንን ማስፈታት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት ጨምረው አሳስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሃማስ መንግሥታዊ መዋቅርን እና ወታደራዊ አቅምን ማስወገድ፣ ታጋቾቻችንን በሙሉ መመለስ፣ ጋዛ በእስራኤል ላይ ስጋት እንደማትፈጥር ማረጋገጥ እና በሰሜንም ሆነ በደቡብ ያሉ ነዋሪዎቻችንን በሰላም መመለሱ ላይ አትኩረን እንሰራለን ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል።

የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ለማስቆም ከፍ እያለ ከመጣው ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ግፊት ባሻገር የሚቀርቡ የተኩስ አቁም ስምምነቶች አሁንም ፍሬያማ አለመሆናቸው እየተነገረ ይገኛል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስርት ይሄንን እየተናገሩ ባለበት ወቅት በቴል አቪቭ ጎዳናዎች ላይ የወጡ ተቃዋሚዎች ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ታጋቾች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በመጠየቅ ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
 

17 June 2024, 15:49