ፈልግ

ኢራን ውስጥ አስገዳጅ የሂጃብ ህጎችን በመቃወም እ.አ.አ. ከ2002-2023 ድረስ ሲካሄዱ ከነበሩ ተቃውሞች አንዱ ኢራን ውስጥ አስገዳጅ የሂጃብ ህጎችን በመቃወም እ.አ.አ. ከ2002-2023 ድረስ ሲካሄዱ ከነበሩ ተቃውሞች አንዱ 

የአሜሪካን የሃይማኖት ነፃነት የሚጣስባቸው ሃገራት ዝርዝር እንዲጨምር ሃሳብ ቀረበ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን (USCIRF) ዘንድሮ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት የኢራን መንግስት አዲስ ያወጣው አስገዳጅ የሂጃብ ህግ ሰብአዊ መብትን ስለሚጥስ ይህን ህግ ባወጡ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ላይ የተጠናከረ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል የጠየቀ ሲሆን፥ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አምስት ተጨማሪ ሃገራት በከፍተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት ይካሄድባቸዋል በሚል ‘በተለየ ሁኔታ ትኩረት የሚሹ አሳሳቢ አገሮች’ ተብለው ዝርዝራቸው የወጡ 12 ሃገራት ውስጥ እንዲካተቱ አሳስቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን የሀገሪቱን አስገዳጅ የሂጃብ ህግ ተላልፈዋል በተባሉት ኢራናዊያን ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እየጨመረ በመምጣቱ በኢራን ባለስልጣናት እና የደህንነት ሃላፊዎች ላይ ተጨማሪ የታለመ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን ከመንግሥት ተጽዕኖ የሌለበት፣ የገንዘብ እርዳታ የማያገኝ፣ በራሱ የሚተዳደር ነፃ ኮሚሽን ሲሆን፥ በነፃነት የማምለክ ችግር የተከሰተባቸው አገሮችን በመጎብኘት ሁኔታዎችን ገምግሞ ለዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለፕሬዚዳንቱና ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዘገባ ያቀርባል።

ኮሚሽኑ በሀይማኖት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እና በውጭ የእምነት እና የሃይማኖት ነፃነትን ለማስፋፋት የታለመ የውጭ ፖሊሲ ምክሮችን ለአሜሪካ መንግስት እና ኮንግረስ የሚያቀርብ እ.አ.አ በ1998 የተመሰረተ የሁለትዮሽ የፌደራል አካል ነው።

ምክሮቹ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃይማኖት ነፃነትን “ስልታዊ በሆነ መልኩ፣ ቀጣይነት ያለው እና ከባድ ጥሰቶች” ላይ የሚሳተፉ ወይም ሲፈፀም እርምጃ የማይወስዱ የመንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን ዓመታዊ ስም ዝርዝር ሲያወጣ ለማገዝ በየዓመቱ በሚታተም ሪፖርት ውስጥ እንደሚካተት ተነግሯል።

በኢራን በሂጃብ ላይ የሚደርግ ጥብቅ ቁጥጥር

በቅርቡ በተለቀቀው የጎርጎሳዊያኑ የ 2024 ዓመታዊ ሪፖርት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን ኢራንን በድጋሚ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ተብለው በተለዩ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ያስገባ ሲሆን፥ የአሜሪካ አስተዳደር በኢራን የመንግስት ኤጀንሲዎች እና ኃላፊዎች በፈጸሙት ከፍተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት ምክንያት የግለሰቦቹን ንብረት በማገድ እና/ወይም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ በመከልከል ውጤታማ ማዕቀብ እንዲጥል መክሯል።

በዚህ ዓመት በሚያዝያ ወር ላይ የኢራን ባለስልጣናት ‘ኑር’ (በፋርስኛ “ብርሃን”) የተሰኘ አዲስ የሂጃብ ዘመቻ ከፍተው ሂጃብ ለመልበስ ፍቃደኛ ያልሆኑ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በኃይል በቁጥጥር ስር አውለዋል። ይህ አዲስ የእስር ተግባር የመጣው የተባበሩት መንግስታት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ እውነታን አጣሪ ኮሚቴ ኢራን በምትተገብረው አስገዳጅ የሂጃብ ህግ እና ሌሎች የእምነት ነፃነት ጥሰቶች ላይ የወሰደችው እርምጃ በሰው ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል መሆኑን ከወሰነ ከሳምንታት በኋላ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ የአሜሪካ መንግስት እነዚህን ግኝቶች እንዲደግፍም ጠይቋል።

አምስት ተጨማሪ ‘አሳሳቢ አገሮች’ ተብለው የተለዩ ሃገራት

ኮሚሽኑ በዓመታዊ ሪፖርቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፍጋኒስታንን፣ አዘርባጃንን፣ ህንድን፣ ናይጄሪያን እና ቬትናምን ቀደም ብለው የሃይማኖት ጥሰት ይፈፀምባቸዋል ተብለው በተለዩት 12ቱ ‘አሳሳቢ ሃገራት’ ዝርዝር ውስጥ እንዲያካትት ያሳሰበ ሲሆን፥ ይህም አጠቃላይ የሃገራቱን ቁጥር ወደ 17 ከፍ አድርጎታል።

ከኢራን በስተቀር እነዚህ ሃገራት ሰሜን ኮሪያን፣ ኒካራጓይ፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ፓኪስታን፣ ማይናማር፣ ኩባ፣ ሩሲያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ታጂኪስታን እና ቱርክሜኒስታንን ያካትታሉ።

በልዩ ዝርዝር ውስጥ ያሉ አሳሳቢ ሃገራት እና አካላት

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን መሰረት ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራቅ፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ማሌዥያ፣ ስሪላንካ፣ ሶሪያ፣ ቱርክ እና ኡዝቤኪስታን መንግሥታታቸው “ከባድ” የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት የሚፈጽሙባቸው ወይም ሲፈጸም እርምጃ በማይወስዱ አገሮች ልዩ የምልከታ ዝርዝር (SWL) ውስጥ መካተት እንዳለባቸው ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል።

ሪፖርቱ በተለይ በከባድ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት እና ብዙ ጊዜ ብጥብጥ ላይ ይሳተፋሉ ተብለው በተለዩ አሳሳቢ አካላት ወይም መንግሥታዊ ላልሆኑ ቡድኖች የሚሆኑ ምክሮችን ያካትታል። ከእነዚህም መካከል በሶማሊያ የሚገኘው የአልሸባብ አሸባሪ ድርጅት፣ በናይጄሪያ የሚገኘው ቦኮ ሃራም፣ ሀያት ታህሪር አል ሻም የሚባለው የሶሪያ እስላማዊ ቡድን፣ በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲዎች፣ የሳህል ግዛት እስላማዊ መንግሥት፣ በምዕራብ አፍሪካ ግዛት ውስጥ ያለው እስላማዊ መንግሥት (የምዕራብ አፍሪካ አይ ኤስ ተብሎም ይጠራል) እና በማግሬብ እና በምዕራብ አፍሪካ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የጂሃዲስት ድርጅት የሆነው ጃማት ናስር አል-ኢስላም ዋል ሙስሊሚን ይገኙበታል።

ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን የ2024 ሪፖርት፣ ኮሚሽኑ እ.አ.አ. በ1998 በዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ህግ (IRFA) ሥር ከተቋቋመ ጀምሮ ከወጡት 25ኛው ሲሆን፥ የመጀመሪያው እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም እንደወጣ ተነግሯል።
 

08 May 2024, 15:52