ፈልግ

አንድ የፍልስጤም ቤተሰብ እስራኤል በራፋህ ያደረሰችውን የአየር ጥቃትን ተከትሎ የወደመው ቤታቸው ውስጥ ሆነው አንድ የፍልስጤም ቤተሰብ እስራኤል በራፋህ ያደረሰችውን የአየር ጥቃትን ተከትሎ የወደመው ቤታቸው ውስጥ ሆነው  (AFP or licensors)

ኖርዌይ፣ ስፔን እና አየርላንድ በሚቀጥለው ሳምንት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና እንደሚሰጡ አስታወቁ

ኖርዌይ፣ ስፔን እና አየርላንድ በሚቀጥለው ሳምንት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና በይፋ እንደሚሰጡ ያስታወቁ ሲሆን፥ እስራኤል በአገራቱ ውሳኔ ላይ ቁጣዋን ገልጻ በአካባቢው የበለጠ አለመረጋጋትን ይፈጥራል በማለት በሦስቱ አገራት ውስጥ ያሉ አምባሳደሮቿን ጠርታለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል የሚካሄደውን ንግግር ያግዛል በሚል ከሚቀጥለው ማክሰኞ ጀምሮ ለፍልስጥኤም የአገርነት እውቅናን እንደሚሠጡ አስታውቀዋል።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚንስትር ጆናስ ጋህር ስቶር እንደተናገሩት እርምጃው ‘የተራዘመ እና ጭካኔ የተሞላበት ግጭት’ ብለው በጠሩት ጦርነት መዳረሻ እያጡ ያሉትን ንጹሃን ዜጎች ለመደገፍ የሚያስችል ዘዴ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍልስጤምን የአገርነት ዕውቅና መስጠት ያለውን ችግር ለመፍታት ብቸኛውን “ጎን ለጎን በሰላም እና በመረጋጋት የሚኖሩ ሁለት አገራት” መፍጠርን ተግባራዊ ማድረግ ነው ካሉ በኋላ፥ የኖርዌይ ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ሌሎችም አገራት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርግ “ጠንካራ መልዕክት ነው” ሲሉ የአገራቸውን ውሳኔ ዓላማ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ውሳኔውን ለሃገሪቱ ፓርላማ ይፋ አድርገዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይመን ሃሪስ በበኩላቸው ደብሊን ከተማ ላይ በሰጡት መግለጫ ሌሎች ተጨማሪ ሃገራት ‘በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ይህን አስፈላጊ እርምጃ በመውሰድ ከእኛ ጋር እንደሚቀላቀሉ’ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

ስፔን እና አየርላንድ ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት ውሳኔያቸው ከእስራኤል በተቃራኒ በመቆም ወይም ሐማስን በመደገፍ ሳይሆን፣ ሰላምን ለመደገፍ ነው ብለዋል።

ሶስቱ ሃገራት ለወሰዱት እርምጃ እስራኤል በምላሹ በኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን ያሉ አምባሳደሮቿን “ለአስቸኳይ ምክክር” በሚል ወደ ሃገሯ የጠራች ሲሆን፥ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር እዝራኤል ካትስ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ‘ግልጽ እና የማያሻማ መልእክት ለአየርላንድ እና ኖርዌይ እየላክን ነው፡ የእስራኤልን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑትን እና ደህንነቷን አደጋ ላይ የሚጥሉትን በዝምታ አናልፍም፣ ፊት ለፊት እንጋፈጣቸዋለን’ ብለዋል።

የሦስቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ረቡዕ ዕለት ይፋ እንዳደረጉት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅናን በመስጠት የሁለት አገራት መፍትሄን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ቢያንስ 140 የዓለም አገራት ለፍልስጤም ዕውቅናን ሰጥተዋል።

ይህም በተባበሩት መንግሥታት የአረብ አገራት ስብስብ የሆኑትን 22 አገራትን ጨምሮ፣ 57 የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል አገራት እንዲሁም 120 የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ አባላትን ያካተተ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ለፍልስጤም በይፋ ዕውቅናን ካልሰጡ አገራት መካከል የሚገኙ ናቸው።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂዎች በደቡባዊ እስራኤል ላይ ባደረሱት ከባድ እና ድንገተኛ ጥቃት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ200 በላይ የሚሆኑ ሌሎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት እየሰነዘረች ሲሆን፥ በዚህ ዘመቻ በትንሹ 35,600 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
 

23 May 2024, 12:52