ፈልግ

በጋዛ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ቀውስ በጋዛ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ቀውስ 

እስራኤል ወሳኝ የሆነውን ወደ ጋዛ የሚያስገባ መሻገሪያ መንገድ እንደገና ከፈተች

እስራኤል በሐማስ የሮኬት ጥቃት ከደረሰባት ከቀናት በኋላ ወደ ጋዛ ከሚያስገቡት ዋና ዋና መንገዶች መሃል አንዱን እንደከፈተች ገልፃለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በሃማስ የሮኬት ጥቃት ከተፈጸመባት ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ጋዛ ከሚያስገቡት ዋና ዋና መንገዶች መሃል አንዱን እንደከፈተች ገልጻለች።

የእስራኤል መንግስት ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ይህ ‘ካሪም ሻሎም’ ተብሎ የሚጠራው መሻገሪያ መንገድ ለሰብአዊ ዕርዳታ መግቢያ እንደሚውል ገልጿል።

የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ከጋዛ ደቡባዊው ጫፍ የሚገኝ እና ከግብፅ የሲናይ በረሃ ጋር የሚዋሰን የድንበር ማቋረጫ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከጋዛ ሰርጥ የሚወጡ ሁለት የድንበር ማቋረጫዎች ብቻ አሉ። ኢሬዝ የሚባለው ከእስራኤል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ በሰሜናዊ ጋዛ ላሉ ሰዎች መሻገሪያ ሆኖ ያገለግላል።

ካሪም ሻሎም ደግሞ በደቡብ ጋዛ ከእስራኤል ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ የንግድ ዕቃዎች መተላለፊያ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የእስራኤል ጦር ሃገሪቷን ከግብፅ ጋር የሚያገናኘውን ወሳኝ የሆነውን የራፋህ መሻገሪያን መያዙን ተከትሎ፣ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ የምታደርገው የቦምብ ድብደባ ሌሊቱን መቀጠሉ ተነግሯል።

የፍልስጤም የሕክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት በዚህ ጥቃት ሰባት የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል ብለዋል።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው የእስራኤል እና የሐማስ ልዑካን ተቋርጦ የነበረውን የተኩስ አቁም ድርድር በካይሮ ለመቀጠል እየጣሩ ባለበት ወቅት መሆኑም ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኒውዮርክ ባደረጉት ንግግር እስራኤል እና ሃማስ “ፖለቲካዊ ድፍረትን” እንዲያሳዩ እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃማስ ታጣቂ ቡድን መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ድንበር ላይ ባደረሰው ጥቃት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እና ከ200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታግተው መወሰዳቸው ይታወቃል፥ እስራኤል ለዚህ ጥቃት ምላሽ የሚሆን በጋዛ የሚገኘው ሃማስ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምራ እነሆ ሰባተኛ ወሩን አስቆጥሯል።
 

09 May 2024, 11:42