ፈልግ

የዩክሬን 57ኛ ብርጌድ ወታደሮች በኩፒያንስክ ወጣ ብሎ በሚገኝ አከባቢ እየተጓዙ የዩክሬን 57ኛ ብርጌድ ወታደሮች በኩፒያንስክ ወጣ ብሎ በሚገኝ አከባቢ እየተጓዙ  

ዩክሬን በዩናይትድ ስቴትስ ስለተደረገላት ወታደራዊ ድጋፍ ምስጋናዋን አቀረበች

የዩክሬን እና የምዕራባውያን መሪዎች ሀገሪቱ ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት በጦር መሳሪያ፣ በተለይም ከፍተኛ የተተኳሽ መሳሪያ እጥረት ስላለባት ልትሸነፍ ትችላለች የሚለው ስጋት እያየለ በመጣበት ወቅት፥ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ማሳለፋቸውን በደስታ ተቀብለዋል። ሞስኮ ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ ዕርዳታ ግጭቱን የበለጠ እንደሚያባብስ ማስጠንቀቂያ ብትሰጥም፥ ምክር ቤቱ ለዩክሬን የሚሰጠውን 61 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ ዕርዳታ በተጨማሪ ለእስራኤል እና ለሌሎች አጋር ሃገራት ወደ 34 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋውን ከፍተኛ የውጭ ዕርዳታ አጽድቋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የዋሽንግተን ድጋፍ ዩክሬናውያንን ከሞት የሚታደግ ነው በሚል ምስጋናቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ አቅርበዋል።

ይህ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ለረጅም ጊዜያት ሲጠብቁት የነበረው ወቅት ነው። በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ድምጽ ያላቸው 210 ዲሞክራቶች እና 101 ሪፐብሊካኖች ዩክሬን የሩሲያን ወራሪ ጦር እንድትመክት የሚያስችላትን ተጨማሪ ግዙፍ ወታደራዊ እርዳታ አጽድቀዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ 'ግራንድ ኦልድ ፓርቲ' የሚባሉት 112 የሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች ውሳኔውን የተቃወሙ ሲሆን፥ ይህም ቁጥር ሪፐብሊካኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ጥልቅ ክፍፍል አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።

ያለ አሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ አገራቸው በጦርነቱ ልትሸነፍ እንደምትችል ያስጠነቀቁት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የአሜሪካ የሕግ አውጭዎች ለወሰዱት ውሳኔ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሩሲያ በፍርስራሽ ውስጥ ለመቅበር እየሞከረች ላለው ሀገራችን፣ ለሉአላዊነቷ፣ ለህዝቧ እና ለአኗኗር ዘይቤዋ የሚደረገውን ማንኛውም የድጋፍ ተናሳሽነት ዩክሬን ትልቅ አክብሮት እንዳላት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳን ዘለንስኪ የዋሽንግተን ድጋፍ “ጦርነቱን እንዳይስፋፋ የሚያግዝ እና ሀገራችንን ጠንካራ የሚያደርግ ነው” ካሉ በኋላ “አሜሪካ በዚህ ጦርነት የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ በአጋርነት የመሪነት ስፍራዋን አሳይታለች” ሲሉም በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። አክለውም “በደንቦች ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ሥርዓትን ለማስጠበቅና ለሁሉም አገሮች የሚሰራ ህግ እንዲኖር ይህ ዓይነት አመራር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሆኖም ግን ይሄንን የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ የድጋፍ ውሳኔ ሩሲያ የተቃወመችው ሲሆን፥ ከክሬምሊን የወጣው መግለጫ ዕርዳታው “ለበለጠ አደጋ እና ሞት” እንደሚዳርግ ገልጿል።

ረጅም ጊዜ የወሰደው ይህ የድጋፍ ህግ በቀጣይ ሳምንት ለህግ መወሰኛ ምክርቤቱ ቀርቦ ከጸደቀ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፊርማቸውን አሳርፈውበት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

ሩሲያ በ2006 ዓ.ም. የዩክሬን ግዛት የሆነችውን ክሬሚያን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ ውስጥ ካስገባች እና በየካቲት 2014 ዓ.ም. ደግሞ ዩክሬን ላይ ወረራ በማድረጓ ለተከሰተው ጉዳት እና ሞት ዋና “መሃንዲስ” ነች ሲሉ ተቺዎች ይቃወማሉ።

ራስን የመከላከል ክርክር

ኪየቭ ‘ዩክሬን እንደ ነፃ እና ሉዓላዊ ሀገር ራሷን ለመከላከል ስትሰራ ቆይታለች’ በማለት ትገልፃለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ እርዳታ በቅርቡ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው መሰረት፣ ፔንታጎን የጦር መሳሪያዎችን በፍጥነት ወደ ዩክሬን ማዛወር እንደሚችል ከወዲሁ አስታውቋል።

በአውሮፓ እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የማከማቻ ሥፍራዎች ገና ከወዲሁ ዩክሬናውያን በጣም የሚፈልጓቸውን አንዳንድ ተተኳሾችን እና የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን እንዳከማቹ ተዘግቧል።

የወታደራዊ እርዳታ ጥቅሉ የተያዙትን የሩስያ ንብረቶች ለመውረስ እና ወደ ዩክሬን ለማዘዋወር ብሎም መልሶ ለመገንባት የሚውል የገንዘብ ድጋፍን እንደሚያካትት ተገልጿል።

በዚህ መልኩ ከሚሰጠው 61 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ውስጥ 23 ቢሊየኑ በዩክሬን የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች እና ጣቢያዎችን ለማጠናከርና የጎደሉ ግብአቶችን ለማሟላት የሚውል ነው ተብሏል።

በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋር ሃገራት በስፋት እየተሳተፉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፥ እንደ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ያሉ አንዳንድ የኔቶ ወታደራዊ ህብረት አባል ሀገራት የሁለቱ ሃገራት ግጭት ወደ ሰፊው የምስራቅ እና ምዕራብ ሃገራት ግጭት ሆኖ ሊዛመት እንደሚችል እና ይህ ደግሞ አውሮፓን እና ዓለምን ሊጎዳ ይችላል ብለው ስጋታቸውን ያቀርባሉ።

ሩሲያ ታህሳስ 2014 ዓ.ም. በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ጀምሮ በርካታ ሕፃናትን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ብሎም ቆስለዋል ተብሎ ይታመናል።
 

22 April 2024, 14:52