ፈልግ

አዲስ የተመረጡት የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ አዲስ የተመረጡት የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ  (AFP or licensors)

ተሰናባቹ የሴኔጋል ፕሬዝዳንት የተካሄደው ምርጫ “ለዲሞክራሲ ድል ነው” አሉ

ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ እሁድ ዕለት ዲሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የ43 ዓመቱ ፋዬ በአፍሪካ በዕድሜ ትንሹ ፕሬዝዳንት መሆናቸውም ተዘግቧል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሴኔጋል ከሰባት ሚሊዮን በላይ መራጮች በተሳተፉበት ምርጫ አዲስ ፕሬዝዳንት ተመርጧል። የካቲት 17 ላይ መደረግ የነበረበትን ምርጫ የቀድሞው ፕረዚዳንት በተለያዩ ምክንያቶች ማራዘማቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ አሁን የተደረገው ምርጫ ያለምንም ችግር መካሄዱም ተነግሯል።

የአዲሱ ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ደጋፊዎች ቅድመ ውጤቶቹ መነገር እንደጀመሩ ነው በጎዳናዎች ላይ ወጥተው ደስታቸውን መግለጽ የጀመሩት።

የአዲሱን ተመራጭ ፕሬዝደንት ፋዬ ድል አስገራሚ የሚያደርገው ነገር ምርጫው ሊደረግ አንድ ሳምንት ሲቀረው ከእስር ቤት ተለቀው ምርጫውን ማሸነፋቸው እንደሆነም ተነግሯል።

ፕርዚዳንት ፋዬ ከአንድ ዓመት በፊት ከተቃዋሚው መሪው ኦስማን ሶንኮ ጋር በአመፅ ወንጀል ተከሰው 11 ወራትን በእስር ቤት አሳልፈዋል። አብረዋቸው የታሰሩት ሶንኮ ግን በሁለት ጥፋቶች ተከሰው ከምርጫው መታገዳቸው ይታወቃል።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ

ሰኞ ዕለት ገዢውን ፓርቲ ወክለው ሲወዳደሩ የነበሩት እና የፋዬ ተቀናቃኝ የነበሩት አማዱ ባ እና ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፥ ፋዬ በምርጫው በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ፥ ሁለቱም ምርጫው የተካሄደበት መንገድ ዲሞክራሳዊ ነው በማለት አወድሰዋል።

የምርጫ ቅስቀሳው ሊጀመር ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው የካቲት ወር ላይ ሊደረግ የነበረውን ምርጫበ10 ወራት ለማራዘም የሞከሩት ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ሳል የእሁዱ ምርጫ “ለሴኔጋል ዲሞክራሲ ድል ያደረገበት ነው” ብለዋል።

የምዕራብ አፍሪካ ቲንክ ታንክ ዋቲ ተንታኝ እና የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ባባካር ንዲያዬ ከሮይተርስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ፕሬዝደንት ሳል ምርጫውን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መሞከራቸው በሃገሪቷ ተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎችን እንዳስነሳ እና በሶስት ዓመታት ውስጥ ስምንት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ባስተናገደው ክልል ውስጥ የባሰ ዲሞክራሲያዊ ውድቀትን ያመጣል የሚል ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል ካሉ በኋላ፥ ሴኔጋልን ወደ ሌላ ቀውስ እንድትገባ ያደርጋታል የሚል ስጋትም ነበር ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ሰላምን ማቆየት ይቻላል የሚል ተስፋ አላቸው

የዳካር ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ቤንጃሚን ዲያዬ ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ያላቸውን ተስፋ ባለፈው ሳምንት ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት ከተፈጠረ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ፥ ሰፍኖ የነበረው “ትንሽ ሰላም” በድምጽ መስጫው ወቅትም ይሁን በኋላ ተጠብቆ እንዲቆይ እና እንዲጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገለጸው ነበር።

አገራቸው ዲሞክራሲን ለማስፈን ረጅም ርቀት እንደተጓዘች በማስታወስ፥ “ከአሁን በኋላ ስሕተት መሥራት አንችልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ብጹእ አቡነ ዲያዬ መራጮቹ ‘ግጭትን ሊያመጡ የሚችሉ’ ማንኛውንም ቃላት ወይም ድርጊት እንዲያስወግዱ በመምከር፥ በልዩነታቸው ውስጥ “እርስ በርስ እንዲከባበሩ” እንዲሁም በመብቶች እና በመመሪያዎች ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሁሉም ሰው ሀሳቡን በነፃነት እንዲገልጽ” ተፎካካሪዎቹን መክረው ነበር።

የዳካሩ ሊቀ ጳጳስ በሴኔጋል የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለይ በፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን በኩል ስለ ሰላም እያበረከተችው ያለውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል።

ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገውን አስተዋጽኦ በመጥቀስ “የግል ፍላጎቶቻችንን ገታ በማድረግ የጋራ የሆኑ ነገሮቻችን ላይ ለማተኮር ሁሉም ሰው ቆም ብሎ እንዲያስብ” ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ብጹእ አቡነ ባባካር ዲያዬ እሁድ ዕለት በተካሄደው ምርጫ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ በሰላም መምጣታቸው እና ከምርጫው ጋር የተያያዘ ምንም አይነት ነገር ባለመከሰቱ በሴኔጋል ውስጥ ዴሞክራሲ እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።

 

 

28 March 2024, 22:35