ፈልግ

ሄይቲያዊያን ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ እየተባረሩ ሄይቲያዊያን ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ እየተባረሩ 

የሃይማኖት ተቋማት በዶሚኒካን ሪፐብሊክ በሄይቲ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እንዲቆም ጠየቁ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከመቶ የሚበልጡ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ድርጅቶች የሄይቲ አጎራባች በሆነችው ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ውስጥ በሚገኙ የሄይቲ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን “ሕገወጥ እና ኢፍትሐዊ አያያዝ” በይፋ አውግዘዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከስፔን ቋንቋ ተናጋሪው የዓለም ክፍል የተውጣጡ 127 ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ እየተካሄደ ያለውን የሃገሪቱ የወታደራዊ ኃይል እና ‘የስደተኞች አጠቃላይ መምሪያ’ ቢሮ (DGM) ወኪሎችን ተግባር አውግዘዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው መሠረት የዶሚኒካን ባለሥልጣናት ስልጣናቸውን “ጥበቃ ሊያደርጉላቸው በሚገባቸው ሰዎች ላይ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ወንጀል ለመፈጸም” እንደተጠቀሙበት ገልጿል።

መግለጫው መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. አርብ ዕለት ምሽት ላይ ስለተከናወነው አንድ ክስተት በማስታወስ፥ በዕለቱ የአከባቢው ባለሥልጣናት “በቪላ ጓሬሮ ከተማ ውስጥ በሚገኙት የሳንታ ሉቺያ ማህበረሰብ እና በሳንታ ክሩዝ ዴ ኤል ሴቦ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ንፁሃን ቤተሰቦች ላይ የሄይቲ ተወላጆችን ለማፈናቀል ህገ-ወጥ እና ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል” በማለት ገልጿል።

ህገወጥ የሆነ ከሃገር የማስወጣት ተግባር

የሀይማኖት እና ማህበረሰብ ተኮር ድርጅቶቹ በተለይ “ከሃገር ለማስወጣት” በሚል ሰበብ ታፍነው በተወሰዱት ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት አውግዘዋል።

ተቋማቱ በተጨማሪም “በስደተኞች አጠቃላይ መምሪያ ቢሮ እና በወታደራዊ ወኪሎች ስደተኞቹን ከሃገር ለማስወጣት በሚል ሰበብ ከተጎዱት ቤተሰቦች የገንዘብ፣ የሞባይል ስልኮች እና ሌሎች እቃዎች መሰረቁን” አውግዘዋል።

የዶሚኒካን ባለሥልጣናት በእነዚህ ቤተሰቦች ላይ የቃላት እና አካላዊ ጥቃት እንደፈጸሙ እንዲሁም “በዶሚኒካን ሪፐብሊክ ውስጥ መደበኛ የመኖሪያ ፍቃድ ሰነድ ያላቸውንም ሰዎች ጭምር” በማንገላታት ተከሰዋል።

የአገሪቱን ሕገ መንግሥት መጣስ

መግለጫው በእነዚህ ባለስልጣናት የተፈፀሙት ድርጊቶች በዶሚኒካን ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሠረት ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጿል።

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39 ላይ “በዶሚኒካን ግዛት ሁሉም ግለሰቦች በህግ ፊት እኩል ናቸው፥ እንዲሁም ተመሳሳይ መብት አላቸው፥ በዚህ ምክንያት ተመሳሳይ ጥበቃ እና አያያዝ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲል ቃል ይገባል። ከዚህም በተጨማሪም ህገ-መንግስቱ “በፆታ፣ በቀለም፣ በእድሜ፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በዜግነት፣ በቤተሰብ ትስስር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በፍልስፍና አመለካከት፣ ማህበራዊ ወይም ግላዊ መብቶች ያለ ምንም አድልዎ እንደሚከበሩ” ይገልጻል። ከእነዚህ መብቶች መካከል አንቀጽ 69 ላይ ያለውን የፍትህ ሂደት መብት እና አንቀጽ 71 ላይ የሚገኘው በዘፈቀደ ወይም ያለምክንያት ነፃነታቸውን እንዳይነፈጉ’ የሚሉት ይገኙበታል።

መግለጫው፥ ህገ መንግስቱ በዶሚኒካን ተቋማት ተጥሷል በማለት ቅሬታውን የገለፀ ሲሆን፥ “የዶሚኒካን ባለስልጣናት እነዚህን ሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ ድርጊቶችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ለሁሉም ሰዎች ግልጽ እና ፍትሃዊ የአስተዳደር ሂደቶች ዋስትና እንዲሰጡ” ጠይቋል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ የዶሚኒካን ፕሬዝዳንት ለሆኑት ሉዊስ አቢናደር ባቀረቡት ጥሪ “በብዛት ምዝበራ እና ስርቆት ላይ ያነጣጠሩ ልማዶች ለማስቀረት ቁርጠኛ ትእዛዝ እንዲሰጡ” ጠይቀዋል።

መስከረም 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንት አቢናደር “ወይ ሄይቲን ለማዳን በጋራ እንታገላለን፣ ወይም የዶሚኒካን ሪፐብሊክን ለመጠበቅ ብቻችንን እንዋጋለን” በማለት በአንድነት መቆም እና መረዳዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር።

የ127ቱ የሃይማኖት ድርጅቶች የጋራ መግለጫ “አርብ ማለዳ ላይ የተፈጸመው ይህ ተግባር ‘ሄይቲን ለማዳንም’ ወይም ‘ዶሚኒካን ሪፑብሊክን ለመጠበቅ’ ያለመ እንዳልሆነ አመላክተዋል።

ድርጅቶቹ በመጨረሻም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በዶሚኒካን ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙትን የእነዚህን በጣም ደካማ የሆኑትን ሰዎች” መብቶች እንዲጠብቁ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
 

27 March 2024, 12:43