ፈልግ

በእስራኤል - ጋዛ ግጭት ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሲያደርግ በእስራኤል - ጋዛ ግጭት ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሲያደርግ  (ANSA)

የጋዛ ጦርነት ተጠናክሮ ባለበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቧ ተነገረ

ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በጋዛ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቧ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት ግጭቱ እንዲቆም ባካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ወቅት፥ ዋሽንግተን 'የተኩስ አቁም ስምምነት' የሚለውን ቃል ከመጠቀም ተቆጥባ እንደነበር ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ ውድቅ ስታደርግ የነበሩትን የተባበሩት መንግስታት ቀደም ሲል ያሳለፉትን ውሳኔዎች ተመሳሳይ ቃል በመጠቀም በጋዛ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ጥሪ ስትጠይቅ ይህ የመጀመሪያዋ እንደሆነ ተነግሯል።

ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ አሜሪካ ባወጣችው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ንግግሮች እንደሚጀምሩ የሚጠቁሙ ሲሆን፥ አሜሪካ በራሷ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ፣ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግና በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም በጋዛ እርዳታ እንዲደርስ መሰናክሎች እንዲነሱ ይጠይቃል።

አሜሪካ ያቀረበችው ሃሳብ ላይ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽ ስለመስጠቱ እንዲሁም መቼ ሊሰጥ እንደሚችል ግልጽ የተደረገ ነገር ዬለም።

ሰኞ ዕለት ሃያ ስድስት የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በጋዛ ሰርጥ ወደ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያመጣውን አስቸኳይ የሰብአዊ ዕርዳታ ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በራፋህ ላይ የታቀደ ጥቃት

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በብራስልስ ባደረጉት ስብሰባ ከሀንጋሪ በስተቀር ሁሉም የአውሮፓ ህብረት ሀገራት እስራኤል በራፋህ ላይ የምታደርገውን ጥቃት በከተማዋ ውስጥ ያለውን የስደተኞች ችግር ያባብሳል በማለት አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል የራፋህ ከተማን ለማጥቃት ያወጣችውን ዕቅድ ዓለምአቀፍ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፥ ብዙ ሀገራት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አሳስበዋል።

የቀይ ባህር ቀውስ

በተያያዘ ዜና በየመን የሚንቀሳቀሰው የሁቲ ታጣቂ ቡድን የአውሮፓ ህብረት የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያን የቀይ ባህር ጥምረት እንዳይቀላቀል አስጠንቅቋል።

ሰኞ ዕለት ብራሰልስ እንዳስታወቀችው የህብረቱ ሃገራት መርከቦች የሁቲ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ በመምጣታቸው፥ የመርከቦቹን እንቅስቃሴን ለመጠበቅ በቀይ ባህር ላይ የባህር ኃይል ተልእኮ መጀመሩን ገልፃለች።
 

22 February 2024, 14:25