ፈልግ

ሱዳናውያን ስደተኞች ሱዳናውያን ስደተኞች 

የመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች በጦርነት ለምትታመሰው ሱዳን አዲስ የእርዳታ እቅድ ማውጣታቸው ይፋ ሆነ

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ዘገባ ከሆነ፥ ሱዳን ውስጥ ያለውን ጦርነት ሸሽተው በሃገር ውስጥ እና በጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ በድምሩ 17.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ በዚህ ዓመት ብቻ 4.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ንግግር ቢደረግም አሁንም ድረስ ጦርነቱ ሱዳንን እያወደመ ባለበት ወቅት፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አጋሮቹ ለጎረጎሳዊያኑ 2024 አዲስ የሰብአዊ እና የስደተኞች የዕርዳታ እቅድ ማውጣታቸው ተነግሯል ።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት (OCHA) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በአፍሪካ ሀገር ውስጥ በጣም አስቸኳይ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት 4.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ጥምር ጥሪ አቅርበዋል።

1.5 ሚሊዮን ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለዋል

ከአጠቃላይ 25 ሚሊዮን የሱዳን ህዝብ፥ ግማሽ ያህሉ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ጎረቤት ሀገራት በመሰደዳቸው አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ሁለቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች አስታውቀዋል።

ጥቅምት 2014 ዓ.ም. የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በጋራ በመሩት በሁለቱ የቀድሞ አጋሮች መካከል ማለትም የሱዳን ፕሬዚዳንት በሆኑት በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ታማኝ ወታደሮች እና በተቀናቃኛቸው በጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መካከል ለወራት ከዘለቀው ከፍተኛ ውጥረት በኋላ ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የእርስ በርስ ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል።

ጦርነቱ ከዋና ከተማይቱ ካርቱም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋው እና ጄኔራል ዳጋሎ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ካሳወቁ በኋላ እንደገና የቀጠለው ጦርነት፥ ለበርካታ ሰዎች መፈናቀል፣ ረሃብ እና ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ውድመትን ማድረሱን ብሎም ህዝቡን ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ እንደዳረገ እና የጤና እንክብካቤ እና የትምህርት ተደራሽነት እጥረት እንዳስከሰተ ተነግሯል።

ሁለቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እንዳስታወቁት፥ ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት እየተጋለጡ ሲሆን፥ 19 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንደሆኑ፥ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በስፋት እየተስተዋሉ እና በስርዓተ-ፆታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶች እንደተበራከቱ ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት የተዳረጉበት ይህ ጦርነት፥ እስካሁን ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ አንዳስገደዳቸው ፤ ከእነዚህም መካከል አብዛዎቹ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን እንደተሰደዱ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን እና በአካባቢው በአጠቃላይ 17.4 ሚሊዮን ሰዎችን ለመደገፍ አቅዷል

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁት ይህ የተቀናጀ እቅድ በሱዳን እና በቀጠናው 17.4 ሚሊዮን ሰዎችን ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል።

የሰብአዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ እና የአደጋ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ማርቲን ግሪፊዝ ዕቅዱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “ለጋሾች በሚያደርጉልን ድጋፍ ምግብ፣ መጠለያ እና ንፁህ ውሃ ለማቅረብ፥ እንዲሁም ህፃናትን እንድናስተምር እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል እና የተረፉትን ለመንከባከብ እንድንችል ያግዘናል” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፥ ባለፈው ዓመት የተሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ ካወጣነው በግማሽ ያነሰ መሆኑን ገልጸው፥ “በዚህ ዓመት በተሻለ ሁኔታ እና በአስቸኳይ ልንሰራ ይገባል” ብለዋል።

በ 2015 ዓ.ም. በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም፥ በዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ በሰብአዊ ድርጅቶች በሱዳን ውስጥ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን መርዳት ተችሎ እንደነበር እና ስደተኞቹ ያሉባቸው ሃገራትን በመደገፍ ለተፈናቃዮቹ ወሳኝ የህይወት አድን ድጋፍ እና ጥበቃ ለማድረግ እንደተቻለ ተገልጿል።

በያዝነው ዓመት ስደተኞችን ለመደገፍ የተያዘው እቅድ እነዚህን በጎ ተግባራት ለማስቀጠል እና በተጨማሪም እስከ 2.7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን የመልሶ ማቋቋም አቅም ግንባታ ተግባራትን ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏ።
 

08 February 2024, 16:55