ፈልግ

በኪየቭ በደረሰ የሚሳኤል ጥቃት በኋላ ማህበራዊ ሰራተኞች የደረሰባቸውን ጉዳት እየጠገኑ በኪየቭ በደረሰ የሚሳኤል ጥቃት በኋላ ማህበራዊ ሰራተኞች የደረሰባቸውን ጉዳት እየጠገኑ   (ANSA)

ዩክሬን ከባድ በሆነ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት እየተናጠች መሆኑ ተነገረ

እሁድ እለት በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ዩክሬን ላይ ከባድ የሆነ የሩስያ ሰው አልባ የአየር ጥቃት ከደረሰ በኋላ ተጨማሪ ጉዳት ገጥሟታል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ካቶሊኮች የዓለም የህሙማን ቀንን እያከበሩ ባሉበት ወቅት፥ በጦርነቱ የደከሙ እና ከፍተኛ የጦር መሳሪያ እጥረት ያለባቸው የዩክሬን ሀይሎች እሑድ ዕለት ከባድ ጦርነት እንደገጠማቸው ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አማኞች ለታመሙ ወንድሞችና እህቶች እየጸለዩ ባለበት ወቅት፥ ሩሲያ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አሰማርታ ኪየቭን እና ደቡባዊ ዩክሬንን በመደብደቧ ዩክሬን ሌላ የመከራ ምሽት ያሳለፈች ሲሆን፥ በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰላማዊ ሰው እንንደተጎዳ ተገልጿል።

ጥቃቱ የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመርን እና በሚኮላይቭ ወንዝ እና የባህር ወደብ ውስጥ የሚገኙ የመኖሪያ ሕንፃዎችን ከጥቅም ውጭ ማድረጉ ተዘግቧል።

የዩክሬን ደቡባዊ ወታደራዊ እዝ እንደገለጸው የአየር መከላከያ ስርአቱ ከአምስት ሰዓታት በላይ በመከላከል ስራ ላይ እንደነበር እና በደቡባዊ አካባቢዎች በተለይም በጥቁር ባህር አቅራቢያ በሚገኘው ማይኮላይቭ ክልል ላይ 26 የሩሲያ ሻሄድ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን አስታውቋል። 

ሆኖም በዋና ከተማዋ ኪየቭ አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ዜናዎች የተሰሙ ሲሆን፥ የከተማው ባለሥልጣናቱ እንደተናገሩት ከ45 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል 40 የሚሆኑት መውደማቸው እና በመዲናዋም ሆነ በአቅራቢያ ምንም ጉዳት ወይም ውድመት አለመድረሱን ገልጸዋል። 

ነገር ግን የቅርብ ጊዜው የኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ያካተተው የሩስያ ጥቃት የደረሰው ቀደም ብሎ ቅዳሜ እለት ሲሆን፥ የዩክሬን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ካርኪቭ ሶስት ህፃናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በሩሲያ የአየር ጥቃት መሞታቸውን ባለስልጣናቱ አረጋግጠዋል።

ሆኖም መቆጣጠሪያ ጣቢያው ከተመታ እና እሳቱ በፍጥነት ወደ ብዙ ቤቶች በመዛመቱ ምክንያት የህይወት አድን ሠራተኞች የሴቶችን እና የህጻናትን ህይወት ለማትረፍ ሲሯሯጡ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ታይቷል።

የሩሲያ ዘዴዎች

የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳሉት ሩሲያ በአጠቃላይ በደርዘን የሚቆጠሩ የሻሄድ አውሮፕላኖችን በተለየ ሁኔታ በካርኪቭ እና ኦዴሳ ያሰማራች ሲሆን፥ በተጨማሪም በዩክሬን ዳኑቤ ዴልታ አካባቢ በሚገኙ ሬኒ እና ኢዝሜል ከተሞችም ማሰማራቷን ተናግረዋል ። በዩክሬን ከተማ ከተሰማሩ 31 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል የዩክሬን አየር ሃይል 23ቱን መትቶ መጣሉን ገልጿል።

ሩሲያ የወሰደቻቸው ጥቃቶች የሚያሳዩት የዩክሬንን የወደብ እና የእህል ኤክስፖርት መሠረተ ልማትን የመምታት ስትራቴጂ ነው ተብሏል። ኦዴሳ የዩክሬን ትልቁ ወደብ ሲሆን፥ የሬኒ እና ኢዝሜል ወደቦች እህልን በዳኑቤ ወንዝ በኩል ወደ አውሮፓ ለመላክ አስፈላጊ ቦታዎች እንደሆኑ ይታወቃል።

የሩሲያ ሚኒስትሮች የጦር መሳሪያ ምርትን እንደሚጨምሩ እና ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር የአቅርቦት ስምምነት እንደሚፈራረሙ አጉልተው እየተናገሩ ባለበት ወቅት፥ የዩክሬን ጦር አዛዦች በበኩላቸው ከምዕራባውያን አጋሮቻቸው የሚቀርቡ የጦር መሳሪያዎች እጥረት እያጋጠማቸው እንዳለ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በእነዚህ የጦር መሳሪያዎች ምክንያት የደረሰው ጉዳት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ የደረሰው ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ግጭት፥ በበርካታ ትውልዶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለቱም ወገኖች ይሞቱበታል ብሎም ይቆስሉበታል የሚል ስጋትን ጨምሯል።

'የንግድ ስምምነት የለንም'

እነዚያ ሳተላይቶች ለዩክሬን የጦርነት አቅም ወሳኝ እንደነበሩ እና ሩሲያ እነሱን መጠቀም መቻሏ የኪየቭን ታክቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚያዳክም ተገልጿል።

ሆኖም የስታርሊንክ ሲስተምን የሚመራው ‘ስፔስ ኤክስ’ ባለፈው ሳምንት “ከሩሲያ መንግስትና ከወታደራዊ ሃይሉ ጋር ምንም አይነት የንግድ ስራ እንደማይሰራ” እና አገልግሎቱም በሩሲያ እንደማይሰራ ተናግሯል።

ነገር ግን ውጊያው ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፥ በቂ መረጃ እንዳለው የሚነገርለት የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር፥ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የምታደርገው ጦርነት በሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች መኖራቸውን ገልጿል።

ልክ በዩክሬን ውስጥ እንዳሉት ሆስፒታሎች በሩሲያ ውስጥ ያሉትም በጦርነቱ የቦንብ ድብደባ እንደሚደርስባቸው ተነግሯል።

የብሪታንያ የመከላከያ ባለስልጣናት በዓለም የህሙማን ቀን እንደገለፁት የትጥቅ ግጭቱ በመላው ሩሲያ ለሚገኙ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች እጥረት አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ እና የተጎዱ እና የሞቱት ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ ሆስፒታሎች እነሱን ለመንከባከብ ከፍተኛ ፈተናዎች ገጥሟቸዋል ብሏል።
 

13 February 2024, 15:18