ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የረቢዎችን ቡድን ሲቀበሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የረቢዎችን ቡድን ሲቀበሉ   (Vatican Media)

የአይሁድ ረቢዎች እና ሊቃውንት ር.ሊ.ጳጳሱ በጥላቻ መካከል ወዳጅኝነትን ስለዘሩ እናመሰግናለን አሉ

የረቢዎች እና የአይሁድ - ክርስቲያን ህብረት ሊቃውንት ቡድን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጻፉት ደብዳቤ፥ ብጹእነታቸው ‘በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አይሁዶች እጃቸውን ስለዘረጉ’ እና ‘በፀረ-ሴማዊነት እና በፀረ-አይሁድነት እንቅስቃሴ ላይ ላሳዩት ንቁ ተቃውሞ’ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአንድ ወቅት ፉክክር በነበረበት ጊዜ ወዳጅነት፣ ጠላትነት በነበረበት ጊዜ መግባባትን ለማዳበር የምታደርገው ጥረት ማህበረሰባችንን ቀይሮ በታሪካችን ላይ የዘላለም አሻራ ጥሏል። አለመረጋጋት ለብዙ አስርት ዓመታት የተፈጠሩ ግንኙነቶችን ሳይቀር አደጋ ላይ በሚጥልበት በዚህ ወቅት፣ የዚህን ቃል ኪዳን ማረጋገጫ በቅዱስነትዎ ደብዳቤ ላይ እናገኛለን” እነዚህ ቃላቶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በበርካታ ረቢዎች እና የአይሁድ-ክርስቲያን ህብረት ሊቃውንት የላኩት ደብዳቤ ላይ የሚገኙ አንኳር ነጥቦች ናቸው።

ደብዳቤው ላይ ረቢ ጆሽዋ አህረንስ (ፍራንክፈርት/በርሊን)፣ ረቢ ይትዝ ግሪንበርግ (ኢየሩሳሌም/ኒውዮርክ)፣ ረቢ ዴቪድ ሜየር (ፓሪስ/ሮም)፣ ካርማ ቤን ዮሃናን (ኢየሩሳሌም) እና መልካ ዚገር ሲምኮቪች (ቺካጎ) በጋራ ፊርማቸውን አኑረዋል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሃማስ ታጣቂዎች የተፈፀመውን ጭፍጨፋ እና በዓለም ላይ እንደ ማእበል እየተንሰራፋ የመጣውን ፀረ-አይሁዳዊነት መስፋፋት ተከትሎ፥ ይኸው ቡድን በአይሁድ እና በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ቅርርብ ለማጠናከር ለቅዱስ አባታችን ደብዳቤ ጽፎ እንደነበር ይታወሳል።

ጥር 24 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘እስራኤል ላሉ አይሁዳውያን ወንድሞች እና እህቶች’ ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ያላትን አጋርነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ልከው ነበር።

በዚህን ጊዜ በቅድስት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ በሁሉም ጎሳዎች እና ህዝቦች መካከል አስቸኳይ እርቅ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበው እንደነበርም ይታወሳል።

ለብጹእነታው በተላከው ደብዳቤ ላይ የፈረሙት ልሂቃን ረቢ ሙሼ ኢብን ዕዝራን በመጥቀስ ለቅዱስ አባታችን ምስጋናቸውን ሲገልጹ፥ “ከልብ የሚወጡ ቃላት ወደ ልብ ይገባሉ” በማለት ጽፈዋል።

በእርግጥ ደብዳቤው በመቀጠል፥ “በዓለም ዙሪያ ላሉ አይሁዶች እና በተለይም በእስራኤል ለሚገኙ በዚህ በታላቅ ጭንቀት ጊዜ እጆትን በመዘርጋትዎ እና እየተስፋፋ የመጣውን ፀረ-ሴማዊነትን እና ፀረ-አይሁድነትን በቁርጠኝነት ስለተቃወሙ እንጽናናለን” ይላል ደብዳበው።

“እየኖርን ያለነው ጽናትን፣ ተስፋን እና ድፍረትን በሚፈልግ ታሪካዊ ወቅት ላይ ነው” ይልና ደብዳቤው፥ የ ‘ኖስትራ አታቴ’ (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ክርስቲያን ካልሆኑ ሀይማኖቶች ጋር ስለምታደርገው ግንኙነት የወጣ አዋጅ) ለኛ ትልቅ ተምሳሌት ነው፥ ይህም ወንድማማችነትን በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ግጭቶች ውስጥም ቢሆን መልሶ ማግኘት እንደሚቻል ያሳያል።

እኛ ከካቶሊክ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመተማመን እና ሃይማኖቶች የፈጠራ ኃይሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በመተማመን፥ በሌላ መንገድ ዝግ የሆኑ መንገዶችን ለመክፈት ኃይል ሰጥተውናል” በማለት ይገልፃል።

የፈራሚዎቹን ቡድን ያስተባበሩት ፕሮፌሰር ካርማ ቤን ዮሃናን እንደተናገሩ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ደብዳቤ “በማኅበረሰቦቻችን መካከል ያለውን ውይይት የበለጠ እንድናጠናክር የቀረበ ግብዣ ነው” ካሉ በኋላ፥ “በሁለተኛው የቫቲካን ምክር ቤት ጉባኤ የአይሁድ እና የክርስትና ግንኙነት እንደ አዲስ ምዕራፍ ከጀመረ ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ሆኖታል፥ ዛሬ በእነዚህ አሳዛኝ ጊዜያት ግንኙነታችንን ማደስ አለብን” ብለዋል።

ልሂቃኑ በደብዳቤያቸው እንደገለጹት "አሁን በብዙ ውጥረቶች ውስጥ ብንኖርም፣ ግንኙነቶቻችን እነሱን ለማሸነፍ እና ወደፊት ለመራመድ ጠንካራ እንደሆኑ እርግጠኞች ነን፥ ነገር ግን አሁንም ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ” ብለዋል።

ደብዳቤው የሚያበቃው “በዚህች ምድር የሚከሰቱ ስቃዮች ሁሉ የሁሉም አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ እስላሞች እና የሌሎችም ሁሉ ስቃይ ነው፥ ብሎም በአሁኑ እና በወደፊት ህይወታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ይህን የተሰበረ ዓለም የመፈወስ ግዴታ ወደ ማንነታችን ውስጥ ዘልቆ መግባት አለበት” በማለት ነው።
 

16 February 2024, 14:25