ፈልግ

ፍልስጤማውያን የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻ በመፍራት ራፋህን ለቀው ሲወጡ ፍልስጤማውያን የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻ በመፍራት ራፋህን ለቀው ሲወጡ 

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የዓለም አቀፍ ጫና እየበረታ መምጣቱ ተነገረ

የአሜሪካው የስለላ ተቋም የሆነው የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር በኳታር አደራዳሪነት የሚደረገውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ሃማስ በምትኩ የእስራኤልን ታጋቾችን የሚለቅበት እቅድ ላይ ለመወያየት ግብፅ ይገኛሉ።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በካይሮ ከተማ የሲአይኤ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ዊልያም በርንስ፣ የግብፅ አቻዎቻቸው እና በኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል ውይይት ሊደረግ እንደሆነ ተዘግቧል።

ይህ ውይይት እንዲደረግ በዋናነት በር የከፈተው በጋዛ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ዓለም አቀፍ ግፊት እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነም ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እያለ እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተጠለሉበት ራፋህ ከተማ በሚገኘው የሃማስ ጦር ላይ የምድር ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ እንዳለች ዘገባዎች ያሳያሉ።

ለሲቪሎች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች

በለንደን የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኦርሊ ጎልድሽሚት የእስራኤል ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ አይደለም ብለዋል። ይህንንም ሲያብራሩ ‘ሲቪሎችን መጉዳት አንፈልግም፥ ከፍልስጤም ህዝብ ጋር ጦርነት ገጥመን አናውቅም’ ሲሉ ጎልድሽሚት ለቢቢሲ ራዲዮ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ራፋህ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ሲሉ አጥብቀው መናገራቸው ይታወሳል። በወቅቱም 'እስራኤል በከተማዋ መጠጊያ የሚሹትን ዜጎች ለመጠበቅ አስተማማኝ ጥረት ማድረግ አለባት' ብለዋል ባይደን። በማከልም “በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ተፈናቅለዋል፣ በፊት ወደ ሰሜን ሸሽተው ነበር፥ አሁን ደግሞ ወደ ራፋህ ተሰደዋል፣ እነዚህ ሰዎች ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው” ሲሉ ፕረዚዳንት ባይደን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን እስራኤል በራፋህ ማንኛውንም ዘመቻ ከመጀመሯ በፊት 'በደንብ እንድታስብ' አሳስበዋል።

የምግብ አቅርቦቶች ቆመዋል

በሌላ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ (UNRWA) ለጋዛ ሰርጥ አስፈላጊ የሆኑ የምግብ አቅርቦቶች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ በእስራኤል ባለስልጣናት እየተከለከሉ ነው ብሏል።

“የምግብ እጦትን ለመቅረፍ አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶች ከእስራኤሉ የአሽዶድ ወደብ ወደ ጋዛ ሰርጥ ዱቄት ለማስገባት ከእስራኤል ባለስልጣናት ፈቃድ ባለማግኘታቸው ምክንያት ቀርተዋል” ሲል ኤጀንሲው በመግለጫው ገልጿል።

የጋዛ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት እንደሚገልጹት ይህ ግጭት ከተነሳበት ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ 28,340 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብለዋል።
 

14 February 2024, 14:12