ፈልግ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግስትን በመቃወም በቴል አቪቭ የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግስትን በመቃወም በቴል አቪቭ የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ  

የእስራኤል ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ

መስከረም 26 የሃማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በመግባት ጥቃት ካደረሱ በኋላ በቴል አቪቭ ሲካሄዱ የነበሩ ፀረ-መንግስት ሰልፎች መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም፥ ከቅርብ ጊዜያት በኋላ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቃቸው ተቃውሞው እንደገና እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ባለፈው የካቲት 9፣ ቅዳሜ ዕለት ማዕከላዊ ቴል አቪቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ባሰሙ የመንግስት ተቃዋሚዎች ተሞልታ ነበር ያሳለፈችው።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሃማስ ታጣቂዎች መሪነት በደረሰው ጥቃት 1,200 የሚሆኑ እስራኤላውያን የተገደሉበት እና 153ቱ የታፈኑበት ክስተት በኋላ፥ መንግስት ሰፊ የፍትህ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲገፋፉ የነበሩ መጠነ ሰፊ ሰልፎች ቆም ያሉ ይመስሉ ነበር።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለአስር ሳምንታት ያክል የዘለቀው ሰልፍ መንግሥት ሊያካሂድ ያቀደውን የሕግ ሥርዓት ማሻሻያ የሚቃወም ነበር።

አዲሱ የሕግ ማሻሻያ የተመረጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት የፍርድ ቤት ዳኛ የመምረጥ ኃይል እንዲኖራቸውና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጉልበት ይሰጣቸዋል።

ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረ አራት ወራት በኋላ በኔታንያሁ መንግስት ላይ የሚደረጉ ሰልፎች ተጠናክረው በመምጣት፥ እንደጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር እስከ 2026 ድረስ ስልጣን ላይ የሚቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ተቃዋሚዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የቀኝ ክንፍ ፓርቲያቸው ከስልጣን እንዲወርዱ የጠየቁ ሲሆን፥ ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን መንግስት የህዝቡን አመኔታ እንዳጣና ለህዝቡ የሚገባውን ማድረግ እንዳልቻለ በማንሳት በሰፊው ሲቃወሙ እንደነበር ተመላክቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመንግስት ላይ የተነሱት ተቃውሞዎች መስከረም 26 በሀማስ እና በሌሎች ቡድኖች የተያዙትን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ተብሎ እስራኤል በጋዛ ላይ በምትወስደው እርምጃ ላይ እየጨመረ ከሚሄደው ከፋፋይ ህዝባዊ ክርክር የተለየ ነው ተብሏል።

የእስራኤል የደህንነት አገልግሎት እንደገለፀው ከ 130 በላይ ታጋቾች አሁንም ታግተው እንደሚገኙ እና ከታገቱት ውስጥ ቢያንስ 30 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ገልጿል።

ሃማስ በእስራኤል ላይ ለወሰደው ጥቃት ምላሽ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ በወሰደው ታይቶ የማይታወቅ የአየር እና የምድር ጥቃት እስካሁን ወደ 29,000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እንደሞቱ እና ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የተገለፀ ሲሆን፥ በርካታ የዓለም መንግስታት የእስራኤልን ተግባር የዘር ማጥፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ተቃዋሚዎቹ የጋዛን ግጭት ለማስቆም እና ድርድር ለማድረግ ኔታንያሁ ተደራዳሪ ልኡካንን ወደ ግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ለመላክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንዳስቆጣቸውም ተናግረዋል።

እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ አቀረቡት የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ይዘት ለሕዝብ ይፋ ባይሆንም፥ ሂደቱ ሳምንታትን እንዳስቆጠረ፥ ነገር ግን ድርድሩ በእስራኤል እና በሃማስ ጥያቄዎች መካከል ሰፊ ክፍተት እንዳለ እየተነገረ ይገኛል።

ኳታር ቅዳሜ ዕለት ድርድሩ “የተጠበቀውን ያህል እየሄደ አይደለም” ስትል ገልፃለች።
 

20 February 2024, 14:56