ፈልግ

የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በራፋ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በራፋ  (ANSA)

እስራኤል በራፋህ ከተማ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ተገለጸ

በራፋህ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እስራኤል እወስዳለሁ ያለችውን የምድር ጥቃት በመፍራት ወደ ሰሜናዊ ዲየር አል ባላህ ከተማ እየሸሹ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሐማስ በጋዛ የታገቱ ሁሉንም እስራኤላውያን ካለቀቀ ከመጋቢት 01፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በራፋህ ላይ የምድር ጥቃት እንደሚከፈት የእስራኤል ጦር በማስጠንቀቁ ምክንያት በራፋህ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የእስራኤልን የምድር ጦር ጥቃት በመፍራት ወደ ሰሜናዊ ዲየር አል ባላህ ከተማ እየሸሹ እንደሆነ ተነግሯል። እስራኤል ሐማስ 130 የሚሆኑ እስራኤላውያንን በጋዛ አግቶ ይዟል ብላ ታምናለች።

እስራኤል በተፈናቃዮች በተጨናነቀችው የጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋህ ወታደሮቿ ሊገቡ እንደሚችሉ ስትገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሆኖም እስራኤል 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ ላይ ለመፈፀም ያቀደችው ጥቃት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቃውሞ ገጥሞታል።

‘መዲስን ሳን ፍሮንታይር’ የሚባለው ድንበር የለሽ የህክምና ባለሙያዎች ተቋም ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፥ ራፋህ የጋዛ ‘የመጨረሻ የድንበር ወሰን’ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ወዴትም መሸሽ አይቻልም በማለት አስጠንቅቋል። ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ በደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ ድንበር ላይ ያሉ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች የእስራኤል ጥቃት እንዲሁም ረሃብ እና በሽታ እንደሚገጥማቸው ገልጿል።

ያም ሆኖ የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል የሆኑት ቤኒ ጋንትዝ እንደተናገሩት ሁሉም ታጋቾች እስኪፈቱ ድረስ እስራኤል ጥቃቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በሆስፒታል ላይ ወረራ

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የሕብረተሰብ ጤና ኤጀንሲ እንደገለጸው እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት በጋዛ የሚገኘው ዋና ሆስፒታል ሥራ ማቆሙ ተነግሯል።

አርብ ዕለት የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ወደ ሚገኘው በዚህ ሆስፒታል ላይ ባደረገው ወረራ የሽብር ተጠርጣሪዎችን ማግኘቱን ገልፆ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሐማስ ታግተው የተወሰዱ እስራኤላውያን በሆስፒታሉ ውስጥ እንደሚገኙ የደኅነንት መረጃዎቼ አመልክተዋል በማለት ወደ ሆስፒታሉ በመግባት ጥቃት የከፈተው ሐሙስ ዕለት ነበር።

እስራኤል በካን ዮኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ላይ 'ትክክለኛ እና ወሳኝ' ዘመቻ እንደጀመረች ብትገልጽም፣ ከስፍራው የተገኘው መረጃ ግን የተለየ እንደሆነ ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛል።

በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት ከፍተኛ ግርግር እና ተኩስ እንደነበረ በመግለጽ፥ ቢያንስ አንድ ሰው እንደሞተ እና በርካቶች መቁሰላቸውን፣ ብሎም አከባቢውን ለቀው ለመሸሽ መገደዳቸውን ዘግበዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ የሆኑት ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ እንደተናገሩት መስከረም 26 በተፈጸመው የሃማስ ጥቃት ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች መያዛቸውን ገልጸው፥ ሃማስ ያገታቸውን ታጋቾችን ወደ ጋዛ ያጓጓዘውን የአምቡላንስ ሹፌር ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

የናስር ሆስፒታል በጋዛ ውስጥ እየሰሩ ከነበሩ ጥቂት ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ በእስራኤል ወታደሮች እና በሃማስ መካከል የተጠናከረ ጦርነት ሲካሄድ እንደቆየ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ተቀብሎ ሲያስተናግድ እንደነበር ተነግሯል።

የሰብአዊ ቀውስ

በሌላ ዜና ከጋዛ ጋር በድንበር የምትዋሰነው ግብፅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የሚፈናቀሉትን ፍልስጤማውያንን ለመቀበል መጠለያ እየገነባች ነው የሚለውን ዘገባ አስተባብላለች።

የፍልስጤም ስደተኞችን የሚረዳው የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ እና የስራ ኤጀንሲ ሃላፊ የሆኑት ፊሊፕ ላዛሪኒ እንዳስታወቁት እስራኤል ተቋሙን ለማጥፋት ያለመ የተቀናጀ ዘመቻ እያካሄደች ነው ብለዋል። ሃላፊው በማከል የስራ መልቀቂያ ጥያቄውን ያቀረቡበት ዋናው ምክንያት በእስራኤል መንግስት ግፊት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ስዊዘርላንድ ውስጥ ለሚገኘው 'ታሚዲያ' ለተባለ የሚዲያ ተቋም እንደተናገሩት “በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና የሥራ ኤጄንሲን ለማጥፋት ያለመ በእስራኤል የሚፈፀም የተስፋፋ እና የተቀናጀ ዘመቻ እያስተናገድን ነው” ብለዋል።

ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶም በአብዛኛው ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ28 ሺህ 400 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ68 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
 

19 February 2024, 12:43