ፈልግ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሠራዊት በ2014 ዓ.ም. ሰላማዊ ዜጎችን ከቤኒ ወደ ኮማንዳ አጅበው ሲወስዱ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሠራዊት በ2014 ዓ.ም. ሰላማዊ ዜጎችን ከቤኒ ወደ ኮማንዳ አጅበው ሲወስዱ   (AFP or licensors)

በዲ. ሪፐብሊክ ኮንጎ የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ

በምሥራቃዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምትገኘው ቤኒ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፥ 30ዎቹ ታግተው እንደተወሰዱ ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በምትገኘው ቤኒ እና በአካባቢው ባሉ በርካታ መንደሮች ባለፈው ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ማክሰኞ ዕለት ታጥቂ ሃይሎች በፈፅሙት ጥቃት ስምንት ሰላማዊ ሰዎችን በሰይፍ በመግደል አሳዛኝ ጥቃት እንዳደረሱ ተገልጿል።

ጥቃቱ የተፈጸመው እስላማዊ መንግሥት ተብሎ ከሚጠራው ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚጠረጠረው የዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት (Allied Democratic Forces) የታጣቂዎች ቡድን እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ጥቃቱ ከደረሰባቸው ውስጥ አምስቱ የብራንሃሚስት የጴንጤቆስጤ ማህበረሰብ አባል በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ላይ የነበሩ ናቸው።

በቤኒ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የኦይቻ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኒኮላስ ኪኩኩ እንዳብራሩት፥ “በዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት አማፅያን የተገደሉ፥ አምስቱን በጸሎት ላይ እያሉ የተገደሉትን ጨምሮ፥ የስምንት ሰዎች አስከሬን በኦይቻ ሆስፒታል አስከሬን ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ እንደተደረገ ገልጸዋል።

“ጠላቶች ገደሏቸው" ሲሉ በሃዘን ውስጥ ሆነው የተናገሩት ከንቲባው፥ ሌሎች በርካታ ሰዎችም እንደጠፉ ገልጸዋል።

የአካባቢው የሲቪል ማህበረሰብ ቃል አቀባይ የሆኑት ዳሪየስ ሲያሂራ ጥቃቱ መፈፀሙን ካረጋገጡ በኋላ፥ አስከሬኖቹ የአስከሬን ማቆያ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።

30 ሰዎች ታግተዋል

ሌሎች የአካባቢው ምንጮች እንዳስታወቁት፥ 30 ሰዎች በአጥቂዎቹ እንደታገቱ እና እነዚህ አጥቂዎች በተለያየ ጊዜ ወደ ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመግባት ቤቶችን በማቃጠል፣ ነዋሪዎችን በመግደል እና እቃዎችን በመዝረፍ ይታወቃሉ ብለዋል።

በሌላ ዜና ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰሜናዊ ምስራቅ በደረሰ ጥቃት 5 ምዕመናንን ጨምሮ 32 ሰዎች መገደላቸውን ሌሎች ምንጮች ዘግበዋል። እነዚህ ጥቃቶች የተወሰዱት በዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት እና በእስላማዊ መንግስት ቡድን ናቸው ተብሏል።

ከ 30 ዓመታት በላይ የቆየ አለመረጋጋት

የሰሜን ኪቩ እና ኢቱሪ አውራጃዎች ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፥ በዚህም እርምጃ የታጠቁ ቡድኖችን ለመዋጋት የሲቪል ባለስልጣናትን በወታደራዊ አስተዳደር በመተካት እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

ይህ በኡጋንዳ ሙስሊም አማፂያን የተቋቋመው የዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት፥ እ.አ.አ. ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደሚንቀሳቀስ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን እንደገደለም መረጃዎች ያሳያሉ።

እ.አ.አ. በ 2019 ዓማፅያኑ ለእስላማዊ መንግሥት (IS) በታማኝነት ለመስራት ቃል እንደገቡ እና አይ ኤስም በበኩሉ እነዚህን አማፂያን እንደ “መካከለኛው አፍሪካ ግዛት” እንደሚመለከታቸው ይነገራል።

እ.አ.አ. በ2021 መጨረሻ ላይ ካምፓላ እና ኪንሻሳ በዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት ላይ “ሹጃአ” የሚል ስም ያለው የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመሩ ቢሆንም፥ አማፅያኑ ጭካኔያቸውን በተለያየ ሁኔታ በማሳየት ቀጥለዋል።

ባለፈው ዓመትም በምዕራብ ኡጋንዳ ሁለት ጥቃቶችን ፈጽመው 13 ሰዎችን ገድለዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአስጨናቂው የምርጫ ጊዜ በመውጣት፥ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሥር የሰደደ አለመረጋጋት ባጋጠማቸው በምስራቅ አውራጃዎቿ ውስጥ ለጥቂት ሳምንታትም ቢሆን መረጋጋትን አሳይታ ነበር። ሆኖም ግን የዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ኅብረት ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በወሰደው ጥቃት አምስት ንፁሃን ዜጎች በተገደሉበት በቤኒ ግዛት ውስጥ ዘግናኝ ጥቃቶች አሁንም እንደገና ቀጥለዋል ተብሏል።

 

02 February 2024, 13:41